የብ.አ. ብርሃነየሱስ የ2004 ዓ.ም. የአርባ ጾም መልእክት

Abatachin"እንግዲህ አሁን በፍፁም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ ጹሙ አልቅሱ እዘኑ" /ኢዮ 2፡12/

የተከበራችሁ ምዕመናን ከሁሉም አስቀድሜ እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ጾም

ደረሳችሁ በማለት በክቡራን ቆሞሳችሁ በኩል ይህን ሐዋርያዊ መልዕክቴን ላስተላልፍላችሁ እወዳለሁ፡፡

የጾም ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ፀጋና በረከት ነው፡፡ ከዚህም ጋር ራሳችንን ከክፉ ነገር በመጠበቅ በመግዛትና በመታጠብ በንሰሐ በመመለስም ወደ እግዚአብሔር ደጅ የምንጠናበትና እርሱንም አቤቱ ማረን ይቅር በለን እያለን ወደ እርሱ የምንበረከክበትና ምህረቱን ለማግኘት የምንዘጋጅበት ነው፡፡

በዚህ የጾም ጊዜ ከሥጋዊ ሥራ ይልቅ ወደ መንፈሳዊ ሥራ በማድላት የነፍሳችንን ዋጋ የምናበዛበት ነው፡፡ ለዚህም ነው የአርባ ጾም ለመንፈሳዊ ነገር ትኩረት የሚንሰጥበት ጊዜ የሆነው፤ ስለሆነም የጾማችንን ዓላማ እግዚአብሔርን ማድረግ አለብን፡፡

የጾም ጊዜ ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት፤ መንፈሳዊ ተጋድሎዎች የምናደርግበት፤ ሰው ከአምላኩ ጋር ያለውን ቤተሰብነትና ቅርበት የሚያጐለብትበት፤ ወደ እግዚአብሔር የሚመለስበት፤ ስለራሱና ስለወገኖቹ የሚያዝንበት፤ ከአምላኩ ጋር ደግሞ በይበልጥ በጸሎት የሚገናኝበትና የሚነጋገርበት ጊዜ በመሆኑ በጣም የተቀደሰ ጊዜ ነው፡፡

ቅዱስ አባታችን ቤነድክቶስ 16ኛ ከፊታችን ጥቅምት 2005 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ዓመት "የእምነት ዓመት" ብለው ሰይመውልናል፡፡ ይህም እያንዳንዳችን በእምነት ውስጥ የታመቀውን ታላቅ ኃይል ለመመልከት እንዲያስችለን ነው፡፡ የዚህም መሠረት /ማቴ. 19፡26/ እንደምናገኘው "በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቸላል" የሚለውንና /ማር. 9፡23/ "ለሚያምን ሁሉ ይቻለዋል" የሚለውን ተገንዝበን ለእግዚአብሔር የሚቻለው ሁሉ በእምነት ለእኛም እንደሚቻለን ለማሳሰብ ነው፡፡ ስለሆነም እምነት ምንም መለኪያ እንደሌለው ተረድን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የምንችለው በእምነት መሆኑን አውቀን፤ ስለ እምነታችን አብልጠን እንድንቀሳቀስና እንድንሠራ እንድንጸልይ አደራ እላለሁ፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን በዚህ መሠረት በያዝነው አርባ ጾም ጊዜ ከክቡራን ቆሞሶቻችሁ ጋር በመሆን በይበልጥ እንድንጸልይባቸው የሚከተሉትን ሃሳቦች ላስተላልፍ እፈልጋለሁ፡፡

በዚሁም መሠረት፡-

1. ስለ ካቶሊካዊ እምነታችን

2. ስለ ቤተክርስቲያንና ስለ ሃይማኖታችን መስፋፋት

3. ስለ ዓለም ሰላም

4. ስለ ካቶሊካዊ ቤተሰብ

5. በቤተክርስቲያናችን ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ካህናትና ማህበራት አንድነታቸውን ጠብቀው የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆች መሆናቸውን የሚመሰክሩበት እንዲሆን

6. ስለ ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ተልዕኮ መሳካትና በሌሎችም የተቀደሱ ሃሳቦች በመመርኮዝ እንድትጸልዩ አሳስባለሁ፡፡

በመጨረሻም ሰው በእምነቱ መልካም ነገር ሲሠራና ሲጸልይ ማየት ለሰይጣን መሸነፊያው ስለሆነ በተለያየ መልኩ ሊያሸንፈን ቢሞክርም እኛም በሃይማኖታችን፣ በጸሎታችን፣ በጾማችንና በሱባኤያችን መንግስቱን ለመውረስ የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ የሆነው እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን፡፡

እግዚአብሔር ጾማችንንና ቤተክርስቲያናችንን ይባርክ

ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

አርባ ጾም 2ዐዐ4 ዓ.ም

አዲስ አበባ

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።