የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰበካዊ ጉባዔ - ሲኖዶስ ተጠናቀቀ

1በክርስቶስ በጋራ መጓዝ በሚል ርእስ የተካሄደው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰበካዊ ጉባዔ - ሲኖዶስ ተጠናቀቀ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሐዋርዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ የእምነት ዓመት መዝጊያን ተመርኩዞ ያዘጋጀው ሰባከዊ ጉባዔ ከኅዳር 26 እስከ 28 ቀናት 2006 ዓ.ም. የሴቶች እድገት ማዕከል ከተናወነ በኋላ ኅዳር 29 ቀን 2006 ዓ.ም በክርስቶስ ንጉሥ በዓል በልደተ ማርያም ካቴድራል በመስዋዕተ ቅዳሴ በታላቅ ድምቀት ተጠናቋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የሰበካውን ጉባዔ ይዘትና ዓላማ አስመልክተው ባስተላለፉት ጋዜጣዊ መግለጫ "ይህ ሰበካዊ ጉባኤ በራሱ መጨረሻ ሳይሆን የሥራው ጅማሮ ነው፡፡ በክርሰቶስ በጋራ የምናደርገው ጉዞም በሰብአዊ ፣በአእምሯዊ፣ በመንፈሳዊ፣ እና በሐዋርያዊ ማንነታችን በሙላት ለመታነጽ ነው፡፡" ካሉ በኋላ አክለውም "ይህ እውነታ የሀገረ ሰብከታችንን ጉዞ በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር የታጀበ ያደርገዋል፡፡ ሲኖዶስ የሚካሔደው በጋራ በሚደረግ ጸሎት፣ አስተንተኖ እና ምክክር ወደ መንፈሳዊ ተሐድሶ ለመድረስ ነው፡፡ ይህንን ጉዟችንን እና ሀገረስ ብከታችንን በሙሉ ለኪዳነ ምሕረት እናታዊ ምክር እና ጥበቃ አሳልፈን እንሰጣለን፡፡" ብለዋል፡፡
ሰበካዊ ጉባዔው ባለፈው ዓመት

ነሐሴ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ሐዋርያዊ ጥሪ በይፋ የተከፈተ ሲሆን ከመክፈቻው ዕለት አንሥቶ በርካታ የቅድመ ሲኖዶስ መርሐ ግብሮች ተነድፈው ተግባራዊ ሆነዋል፡፡
በብፁዕ አቡነ ልሳነ ክርስቶስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ በሚመራውና የእምነት ዓመት አከባበር መርሐ ግብርን እንዲያስተባብር ኃላፊነት በተሰጠው ኮሚሽን ሥር ሌሎች ዐሥራ ሁለት ኮሚቴዎች የተቋቋሙ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚሁ ኮሚቴዎች ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ሠነዶች በተመረጡና ከሀገረ ስብከታችን ሐዋርያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው ርእሳነ ጉዳዮች ላይ እንዲሠሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ለሲኖዶሱ ግብዓት የሚሆኑና በቤተክርስቲያን ምሁራን ሰፊ ትንታኔ የተሰጠባቸውን የተለያዩ ዐውደ ጥናቶች በማዘጋጀትና በማስተባበር የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በትጋት ተወጥተዋል፡፡
በተዘጋጁት ዐውደ ጥናቶች ላይ በርካታ ካህናት፣ መነኰሳት ወንድሞች፣ እኅቶችና ምእመናን በንቃት ተሳትፈዋል፡፡ በቤተክርስቲያን ምሁራን ትንታኔ የተሰጠባቸውን የሁለተኛውን የቫቲካን ጉቤዔ ሠነዶች በሀገረ ስብከታችን ወደ ተግባር ለመለወጥ በሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦች ዙሪያ ሠፊ ውይይት በማድረግ ወደፊት ልንከተላቸው የሚገቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ተጠቁመው ለሰበካዊ ጉባዔው በግብዓትነት ቀርበዋል፡፡
ዐውደ ጥናቶቹም በሚከተሉት ርእሳነ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
1. የቤተክርሰቲያን ባሕርይ፣ መዋቅርና አስተዳደር፦ በምሥራቁ እንዲሁም በምዕራቡ ሕገ ቀኖና በመታገዝና ባለፉት 50 ዓመታት የሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ድንጋጌዎችን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎችን በመመልከት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ምን ያህል መመሪያዎቹ ወጥነት ባለው መልክ ተተግብረው የቤተክርስቲያናችን መዋቅር የዚያ ነጸብራቅ እንደሆነ፤ አስተዳደሯም ከዚያ እንደሚፈስስ በጋራ ማየት እንድንችል የሚጋብዝ የመመካከሪያ አጋጣሚ ሆኖ ተገኝቷል።
2. ሥርዓተ አምልኮ እና ቅዱሳት ምሥጢራት፦ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ሥርዓተ-አምልኮ እና ቅዱሳት ምሥጢራት በቤተክርስቲያን ሕይወት ያለቸውን ሚና በተመለከተ ያሰተላለፈውን አስተምሕሮ ማስገንዝብ፤ የቫቲካን ሁለተኛ ጉባዔ ሠነዶች በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዐውድ ተግባራዊነታቸውን መመዘንና ለወደፊት ሊጡርጊያን እንዴት በቤተክርስቲያን ሕይወት ውሰጥ የበለጠ ማዳበርና ሕይወት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻል አመላካች ሐሳቦችን ለማግኘት በዚህ ሰበካዊ ጉባዔ ምክክር ተደርጓል፡፡
3. ትምህርተ ክርስቶስ እና ስብከተ ወንጌል (በተለይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የሕፃናት፣ የወጣቶች፣ የጐልማሶች እና የመላው ምእመናን ትምህርተ ክርስቶስ ሊዘጋጅና ተግባር ላይ ሊውል እንደሚገባ ተጠቁሟል) ተከታታይ ስልጠናዎችና ሴሚናሮችና በማዘጋጀት በስብከተ ወንጌል ዙሪያ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ ጠቋሚ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
4. የካህናት እና የምእመናን ሁለንተናዊ ሕንጸት በተለይ በፍልስፍና እና በነገረ መለኮት ትምህርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል ከዚህ በተጨማሪ በሰብአዊ፣ በመንፈሳዊ፣ በአእምሯዊና በሐዋርያዊ ሕንጸት ዙሪያ ቀጣይነት ያላቸው ዕቅዶች በማውጣት መሥራት እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል፡፡
5. መንፈሳዊ ማኀበራት እና እንቅስቃሴዎች ፦ምእመናን በክርስቲያናዊ/ካቶሊካዊ መንፈሳዊነትና ሥነምግባር ታንጸው ማደግ እንዲችሉ እና ለሌሎችም አገልግሎታቸውን ማበርከት እንዲችሉ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች የታቀፉ መሆኑ ያታወቃል። ይህ ደግሞ ቤተክርስቲያን ለተጠራችበት የወንጌል አገልግሎት ቁልፍ መሣርያ ነው። ሰበካችን በዚህ ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመፈተሽ የወደፊት አቅጣጫ ለመተለም ውይይቶች ተደርገዋል።
6. የወጣቶች ሐዋርያዊ አገልግሎት፦ ወጣቶች የሃገር ተስፋ እንደሆኑ ሁሉ የቤተክርስቲያንም ተስፋ ናቸው፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያሉ ወጣቶችን ማዘጋጀት እና ማሠልጠን አስፈላጊ ነው፡፡ ወጣቶች በሰብአዊ፣አእምሮአዊ፣ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ማንነታቸው በብቃት መቀረጽ አለባቸው። ስለዚህ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ድንጋጌዎች በመነሣት ይህንን የወጣቶች አገልግሎት ማሻሻል የሚቻልባቸው መንገዶች በዐውደ ጥናቱ ተቃኝቷል።
7. የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት፦ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ስለ ካቶሊክ የትምህርት ተቋማት ባሕርይ፣ አወቃቀር እና አስተዳደር ያወጣውን ድንጋጌ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተስማሚ በሆነ መልክ እንዴት መተርጐም እንደሚቻል ተወያይቷል። ለካቶሊካውያን ልጆችም ቅድሚያ በመስጠት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ምክክር ተደርጎበታል፡፡
8. ማኅበራዊ አገልግሎት፦ እንደሚታወቀው ሁሉ ቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ትሰጣለች። በጤና፣ በትምህርት፣ በመሠረተ ልማት እና በልዩ ልዩ መስኮች የምታበረክተው አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት እሙን ነው። ይህ አገልግሎት "ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውሃ ብቻ...የሚያጠጣ...ዋጋው አይጠፋበትም።" (ማቴ.10፡42) በሚለው የወንጌል ቃል ላይ የተመሠረተው ነው። በዚህ ዘርፍም ቤተክርስቲያን ምን ያህል የወንጌሉን ጥሪ ተግባራዊ እንዳደረገች በዚህ ጉባዔ ገምግማለች።
9. በይነ ክረስቲያናዊ (Ecumenical)እና በይነ ሃይማኖታዊ (Interreligious) ግንኙነቶች፦ በእነዚህ ሁለት ዐበይት ርእሳነ ጉዳዮች ላይ የተከናወነው ውይይት የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባዔ መርሕዎች በመተግበር በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የክርስቲያኖች እና የሌሎች እምነቶች ተከታዮች ወንድማማችነት እና ጠንካራ ትስስሮችን ጠብቆ ለማቆየት እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚቻልባቸውን መንገዶች በማመላከት ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
10. ማኅበራዊ ግንኙነት እና የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች፦ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መገናኛ ብዙኀን ያላቸውን ሚና በተመለከተ የሀገረ ስብከታችንን ነባራዊ እውነታ በመንተራስ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
11. የፍትሕና ሰላም፡- ጉባዔው በሕዝቦች መካከል ባለው መስተጋብር ፍትሐዊ እና ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲዳብር፣ ምግባረ ብልሹ የሆኑ አመለካከቶች እና አሠራሮች እንዲወገዱ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ያወጣውን ድንጋጌ መመዘኛ በማድረግ ተወያይቷል። በተያያዥም በማኅበረሰብና በተቋማት መካከል ፍትህ የግንኙነቶች ሁሉ መሠረት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

12. የዐቅም ግንባታ፦ ከላይ የተጠቀሱትን ሐዋርያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በተገቢው መንገድ ለማስቀጠል የሰው ኃይልና የኢኮኖሚ የዐቅም ግንባታ መፍጠሩ አስፈላጊ በመሆኑ የቤተክርስቲያናችንን በተለይም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የሰው ኃይልና የኢኮኖሚ ዐቅም ግንባታ አወቃቀር የእስካሁን ሂደት እና የወደፊት የጉዞ አቅጣጫ ወዘተ መዳሰሱ ግድ የሚል ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከሦስት ወራት ለሚበልጡ ጊዜያት ከፍተኛ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰበካዊ ጉባዔ የማጠናቀቂያ ሂደት በቅድመ ሲኖዶስ ወቅት በተናጠል የተዳሰሱ ርእሳነ ጉዳዮችን ተዛማጅነትና ትስስር ለመመልከትና ለሀገረ ስብከቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ የወደፊት ጉዞ ብሩህ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እገዛ ያደረገ ነበር፡፡
ለሦስት ቀናት በቆየው በዚህ ሰበካዊ ጉባዔ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኰሳት ወንድም፣ እኅቶች እንዲሁም በርካታ ምእመናን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽ/ቤትና የሌሎች ሀገረስብከቶች ጠቅላይ ጸሐፊዎችና ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪዎች በታዛቢነት ተገኝተዋል፡፡
በብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ መሪነትና ብፁዕ አቡነ ጸጋዬ የሶዶ ሀገረ ስብከት ተተኪ ጳጳስ እንደ ጳጳስ የመጀመሪያ ቅዳሴያቸውን በገባሬ ሰናይነት ባሳረጉበት የ2006 ዓ.ም. የክርስቶስ ንጉሥ በዓል በይፋ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የእምነት ዓመትና ሰበካዊ ጉባዔ - ሲኖዶስ ከሌሎች ወንድምና እኅት አብያተ ክርስቲያናት የተጋበዙ የሃይማኖት አባቶችና የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
ክቡር አባ ጴጥሮስ የአዲስ አበባ ካቶሊካዊ ሰበካ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ በመዝጊያው ላይ ወገነ ክህነት፣ ገዳማውያንና ምእመናን በቅድመ ሲኖዶስ ወቅት ያሳዩትን እጅግ ቀና ተሳትፎና ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉና ለሀገረስብከታችን ሐዋርያዊ ተሐድሶ መሳካት በጸሎት እንዲበረቱ በአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።