የብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የ2005 ዓ.ም የጌታችን ትንሣኤ በዓል መልእክት

abunብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት የ2005 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤን በዓል በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

 "እርሱ ግን እንዲህ አላቸው አይዞአችሁ አትደንግጡ እናንተ የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስ እንደሆነ አውቃለሁ እርሱ ተነስቶአል፤ እዚህ የለም የተቀበረበት ቦታ ይኸውላችሁ ተመልከቱ" (ማር 16፡ 16)፡፡

 የተወደዳችሁ ምዕመናን፣

ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ በሀገር ውስጥና እንዲሁም ከአገር ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች፣ በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ፡-

ከሁሉ በማስቀደም እንኳን ለ2005 ዓ. ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴም ስም መልካም ምኞቴን እገልጽላችኃለሁ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ፍጡሩን ከፈጣሪው የለየውን የሰውን ኃጢአት ስላስተሰረየ ለሰውም የተገባውን ፍርድ ራሱ ተቀበሎ ስላስወገደና ኃጢአተኞችን ከኃጢአት አንጽቶ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው ስለቻለ እኛም በመስቀል ላይ ሞቶ ከአምላክ ጋር ያስታረቀንን እስከ ዛሬ ከኛ ያልተለየውን ኃጢአት ካላስወገድን በቀር ከእግዚአብሔር ጋር መራመድ አይቻለንም፡፡ ኃጢአትን በመውደድና ከምንሠራው ክፋት ለመራቅ ባለመፍቀድ ከእግዚአብሔር ተለይተን ብንኖር የተቀበልነውን ፀጋ ያጠፋብናል ስለሆነም ክርስቲያን የሆነ ሰው ባለበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር መኖሩን በማወቅ ትንሣኤያችን የሆነውን ክርስቶስን ተቀብለን እምነታችንንም በእርሱ አድርገን ልንጓዝ ይገባናል፡፡

እግዚአብሔር በጌታችን ትንሣኤ አማካይነት ለእኛ ለክርስቲያን ወገኖቹ ያቀደልንና የወሰነልን ዕቅድ አለው ለሕይወታችንም መንገድ አለው በዚህም የፈጠራቸውን ሁሉ ወደ እርሱ ግብ የሚያደርሰው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በፈፀመው ሥራ በኩል ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ሞትን ለመቀበል የመጣው እግዚአብሔር አብ ከመጀመሪያ ጀምሮ የወሰነውን ዕቅድ ለመፈፀም አስቦ ስለላከው ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ የእግዚአብሔርን ተቃዋሚዎች ስላሸነፈና ከሁሉም በላይ ስለሆነ ፍጡራን ሁሉ ለእግዚአብሔር አብና ለእርሱ ይገዛሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ያደረገውን ጳውሎስ ሲናገር "አለቆችንና ባለሥልጣኖችን በመስቀሉ ድል ነስቶ ትጥቃቸውን ካስፈታ በኋላ ምርኮኞች ሆነው በይፋ እንዲታዩ አደረጋቸው" ይላል (በቆላ 2 ፡ 15)፡፡

በዮሐንስ ወንጌል (3 ፡ 33) ላይ ደግሞ "ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረ ሁሉ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደሆነ ያረጋግጣል" ይላል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ይህንን በመመስከር የምንፈልገውን ዕርዳታ በእርሱ አማካይነት ስላገኘን ወደ ክርስቶስ ስንቀርብ በፍቅሩ ሙላትም ደስ ሲለን በፊቱ ብርሃን ጨለማችንና መጠራጠራችን ይወገዳል፡፡

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሁላችንም በክርስቶስ መኖር መቻል አለብን ምክንያቱም ከእርሱ ጋር መኖር ዕረፍት የሞላበት ኑሮ ነው፡፡ ተስፋችንን የምናገኘው ከክርስቶስ ነው፡፡ መታመኛችንም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ሀሳባችንን በክርስቶስ ላይ ማድረግ አለብን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ መስጠቱና መዋረዱ ለኛ ለሰው ልጆች ያሳየንና የገለጠልን ወደር የሌለው ፍቅር ነው፡፡ እርሱን መምሰል የሚገኘው ደግሞ እርሱን በመውደድና ፈጽሞ እርሱን መስሎ በእርሱ ዘንድ በመገኘት ነው፡፡

በክርስቶስ ትንሣኤ ሰዎች ያገኙትን የብርሃን ጸጋ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች በእምነታቸው መልሰው ሊያሳዩአቸው ይገባል፡፡ ይህም ማለት ሁላችንም በእምነታችንና በክርስትናችን መልካም ምሳሌ መሆን ይገባናል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በመነሳቱ ለዘላለዓም ህያው ነው፣ እኛም ደግም ከእርሱ ጋር ከሞት ከተነሳን ወደ ኃጢአት ባለመመለስና በመንፈስ ሳንደክም ፀንተን እንኑር የክርስቶስ ትንሣኤ የሰጠንንም ሰማያዊ ብርሃንና ሰላም የተቀበልነውን የድኅንነት ሀብት ሳናጠፋ ሐሳባችንና ጥረታችን ወደ ሰማይ ከፍ እናድርግ፡፡

የተወደዳችሁ የአገራችን ህዝቦች፣ ዛሬ አገራችን ከድህነት ለመላቀቅ የተያያዘችውን የዕድገት ጎዳና በተለያየ መስኮች አጠናክራ በመሥራት ላይ የምትገኘበትን ዘርፈ ብዙ ዕቅዶች ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ መሥራታችሁ ያስመሰግናችኋል፤ በመሆኑም በሃሳብ በጉልበት በገንዘብ በሥራ በማገዝ በየተሰማራችሁበት መስክ ጠንክራችሁ በመስራት የአገሪቱን ዕድገት እንድታፋጥኑና ለተፈጻሚነቱም የተቻላችሁን ያህል ርብርብ በማድረግ የልማቱን ጐዳና ከፍጻሜ ይደርስ ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡ ከዚህም ጋር ጎን ለጎን መታየት ያለበት የዕድገት ማነቆ የሆኑትን የመልካም አስተደዳደር ጉድለቶችንና ግድፈቶችን በማስተካከል የዜጎች መብት ይከበር ዘንድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲያስተገብርና የአፈጻጸም ዕቅዶች የያዘውን ለመከወን ቤተክርስቲያናችን የምትደግፈው መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡

እንደዚሁም አሁን አሳሳቢ ሆኖ እየመጣ ያለው የሰዎች ፍልሰት በአገር ውስጥ በሚደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች ሰዎች በከተማና በክልላቸው ተደራጅትው ለአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚሠሩበት መንገድ በበለጠ እንዲቀየስና ለዚህም በመገናኛ ብዙሃን የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡

በዚህ ዓመት የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ የወርቅ ኢዩቤልዩ ዓመት ይከበራል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነትና ሕብረት ያበረከተችው አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ ለመሆኑ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ አዲስ አበባም የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት ከተማ ስለሆነች የአፍሪካ መናገሻ ተብላለች፡፡ ይህም ያኮራናል፡፡ ለዚህም ላበቃን ለቸሩ እግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይድረሰው፡፡ አሁንም ሆነ ወደፊት የእንግዳ አቀባበላችንና ሥነ ምግባራችን ልቆ መገኘት ይኖርበታል፡፡ የአፍሪካ ሕብረትም ተጠናክሮ የአፍሪካውያን ሁሉ የሰላም፣ የፍትህ፣ የዕድገት መሰረትና አለኝታ እንዲሆን በጸሎት አምላካችንን አንለምነው፡፡ እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ!

የተወደዳችሁ ምዕመናን በጌታችን በመድኃኒታችን ትንሣኤ ሁላችንም ከቸርነቱ ተቀባዮች ብቻ ሳንሆን ያለንን ለድሆችና አቅመደካሞች ለሆኑት አስተዋሽ ላጡና ለጎዳና ተዳዳሪዎች በመስጠትና በማካፈል ከጌታ ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር እንደዚሁ በእርሱ ዙሪያ ተሰባስበን በክብርና በድል ሞትን ያሸነፈውን የአምላካችንን የትንሣኤ በዓል በደስታ ለማክበር ያብቃን እላለሁ፡፡

በመጨረሻም በአደረባችሁ ሕመም ምክንያት በሆስፒታሎችና በየቤቱ በሕመም ላይ የምትገኙ ሁሉ የምሕረት አባት ምሕረቱን ያውርድላችሁ" በከባድ ሀዘን ውስጥም ያላችሁትን እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣችሁ" በየማረሚያ ቤቶችም ሆናችሁ ይህን ክብረ በዓል የምታከብሩትንም እግዚአብሔር በምህረቱ ይፍታችሁ" በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻችሁ ርቃችሁ ለምትገኙ፣ በየጠረፉና የአገራችንን ድንበሮች በመጠበቅ ላይ ለምትገኙ ሁሉ፣ እንዲሁም በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ በማለት በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም መልካም ምኞቴን አስተላልፍላችኃለሁ፡፡

በጌታ ትንሣኤ እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!!

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።