የገዛ ራስህን ድካም መገንዘብ

ቫቲካን ሬድዮ - “የገዛ ራስህን ድካም መገንዘብ ከሁሉ መቅደም ያለበት ተገቢ ነገር ነው”፣ ይህን ያሉት ቅዱስ አባታችን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ ሮማ  በሚገኘው የቅድስት ሳቢና ባዚሊካ በሥርዓተ ላቲን የጾም ጅማሬ የቅዳሴ ሥርዓተ በመሩበት እና ባሰሙት ስብከት ነው። አያይዘውም ሰው ዳግም ፍትሐዊ መሆን የሚችለው በክርስቶስ በኩል በተገለጠው የእግዚአብሔር ፍትሕ እና ምሕረት መሆኑ አስገንዝበዋል።

በዚሁ ጾመ አርባን በምንጀምርበት ጊዜ አንድ ፍትሐዊ ኅብረተ ሰብ ለመገንባት እና የሰው ግርማን የጠበቀ ሕይወት ለማሳለፍ ቤተክርስትያን ግላዊ እና ማኅበረ ሰባዊ መቀየር ወይም መለወጥ እንደሚያሻ ትጠይቃለች ብለዋል። የሰው ልጅ በየዕለቱ በሚያጋጥሙት አሉታዊ ነገራት ሲሰላችም አሁን ካለው የተሻለ ፍትሕ ያለው ዓለም እንደሚመኝ አመልክተዋል።

በመቀጠል ለሰው ልጅ ድኅንነት ሞቶ በተነሣው ክርስቶስ ሰው ከሚሰጠው ፍትሕ የተለየ ግልጸት መለኮታዊ ፍትሕ መከሰቱ አስረድተዋል። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ፍትሕ የፍቅርና የምሕረት ፍትሕ በመሆኑ ዘለዓለማዊ ፍትሕ እንደሆነ ቅድስነታቸው ገልጸዋል።

ቅድስነታቸው ቀጥለው ፡ በጾም ግዜ መጾም መጸለይ እና ማስተንተን፡ ከልብ የፈለቁ ካልሆኑና ከልብ የመጸጸት ምልክት ከሌላቸው በእግዚአብሔር ዘንዳ ተቀባይነት እንደሌላቸው አስገንዝበዋል። እውነተኛነት የሌለው እና ተጸጽቶ የመቀየር ውሳኔ የሌለው ጾም እና ተጋድሎ ከንቱና ውጤቱም ብላሽ እንደሆነ ያመለከቱት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ ከሁሉም የባሰ ደግሞ ለይምሰል የሚድረግ ጸጸት እና ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ራስህን ማታለል እና ፋይዳ ቢስ መሆኑ ገልጠዋል።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ የንባበ መለኮት ምሁር መሆናቸው የሚታወስ እና ጥልቅ የቤተክርስትያን ትምህርትን ለዓለም ምእመናን እያበረከቱ መሆናቸው የማይዘነጋ ሲሆን አያይዘው፡ ክርስቶስ በምድረ በዳ ለአርባ ቀናት ያደረገው ቆይታ ፡ ሰው በጾም ግዜ ምን ማድረግ እንዳለበት በምን ዓይነት እኳኀን መጾም እንዳለበት ያመላክታሉ ብለዋል።

በእግዚአብሔር ፈቃድ ክርስቶስ በምድረ በዳ ሲቆይ በፈቃዱ የጠላት ጥቃት ሰለባ ለመሆን ስለፈለገ ነው ካሉ በሁዋላ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት፤ አዳም ፈተና ላይ ወድቆ መሞቱም የሞት ጅማሬ መሆኑን አመልክተው፡ ክርስቶስ ለጠላት ሲጋለጥ የከሃሌ ኩሉ እግዚአብሔር ፍቅርን እና ፍላጎትን ለማሟላት መሆኑን አስረድተዋል። ሆኖም የክርስቶስ ትንሣኤ ተሳታፊ ለመሆን ክርስቶስ በምድረ በዳ የተወጣውን ተጋድሎ በመከተል ሞትን ማሸነፍ እንደሚገባና ሞት ማለትም ዘለዓለማዊ ጥፋት ነው እና ሞትንም ማሸነፍ እንደሚቻል አስገንዘበዋል።

በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሰው በፈጸመው ኃጢአት የራሱን ንጽሕና እንዳጠፋ የጠቀሱት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ፡ በእግዚአብሔር መሐሪነት እና ሐቀኛ ፍትህ ንጽሕናውን መልሶ ለመቀዳጀት እንደሚችል ገልጸዋል።

ቅድስነታቸው ስበከታቸውን በማያያዝ እግዚአብሔር ሰውን እንዲጠፋ በኃጢአቱ ተጨማልቆ እንዲኖር ስላልፈለገ ምሕረቱን ሰጠው ጸጋውንም አፈሰሰለት። ጾም አመለካከታችንንና አስተሳሰባችንን እንድናሰፋ፣ ፊታችንን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንድናቀና እና በዚች ዓለም እንግዶች መሆናችንን ያስረዳናል ብለዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ፡ ቅዱስ አባታች ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔነዲክቶስ ፊታችን መጋቢት አስራ አራት ቀን ሮማ ውስጥ የምትገኘውን ወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስትያን እንደሚጐበኙ የቫቲካን መግለጫ አስታውቀዋል። የቤተክርስትያኒቱ ክቡር ቄስ ጂንስ ማርቲን ክሩሰ እንደገለጡት፡ የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጉብኝት ለኤኩመኒካዊ (ለክርስትያን አንድነት)እጅግ ጠቃሚ ይሆናል ፡ ወንጌላዊት ሉተራዊት ቤተክርስትያንም ጉብኝቱ በጉጉት ትጠባበቀዋላች ብለዋል።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።