የክርስቶስ ልደት የኛ ልደት ነው፡፡

ልደተ ክርስቶስ ታኅሣሥ  2002 ዓ.ም.

የክርስቶስ ልደት የኛ /የሰውልጆች/ ልደት ነው፡፡

ቃል በመጀመሪያ ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ፡፡ (ዮሐ.1:1)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ፍጹም አምላክ ማለት ደግሞ ስለ እግዚአብሔርነቱ ምንም የማይጎደለው ማለት ነው፡፡

የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ መወለድ ፍጹም ስጦታ ነው፤እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለኛ ይሰጣል፡

ክርስቶስ ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ምልአት ነው፡፡ስለዚህ ነገር ኢየሱስ እንዲህ በማለት ይናገራል፤ “እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ አንዳለ አታምንምን?” (ዮሐ.14፡10)፡፡ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ (ዮሐ. 14፡11)፤ የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃለችሁ፤ እኔ አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል…ምክንያቱም እርሱ ከእንናተ ጋር ስሚኖርና በውስጣችሁም ስለሚሆን ነው፡፡ (ዮሐ.14፡17) …እኔ ሕያው ስለሆንኩ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤እኔ በአብ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፤ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ፤ (ዮሐ.14፡23)

ከነዚህ ጥቅስች የምንረዳው አብ ባለበት ወልድ እንዳለ፤ አብና ወልድ ባሉበት መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ነው፡፡

ስለዚህ ክርስቶስ በምልአት “በአባቱ ፈቃድ፤ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ በራሱም ፈቃድ ነው ሰው በመሆን መጥቶ ያዳነን (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ-ማክሰኞ የሚነበብ ውዳሴ ማርያም)፡፡ ውልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ለሰው ልጅ ስጦታ ሆኖ ወደ ዓለም የመጣው በዚህ መልኩ ነው ፡፡

ከእግዚአብሔር በላይ የበለጠ ሰጭና ተሰጭም / ስጦታ/መቼውም መች የትም የለም፡፡ ልደት ማለት እንግዲያውስ መሰ’ጠት ማለት ነው፡፡

ስለዚህ የክርስቶስ ልደት ማለት የኛ ልደት ማለት ነው፤ እኛ የሰው ልጆች ተወልደናል አዲስ ልደት ስንል መላ ማንነታችንን ለፈጣሪያችን መልሰን በመስጠት ላይ ነን ማለታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደየመቀበል ችሎታችን በየጊዜው ማንነቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚሰጠን ሁሉ እኛም እንዲሁ እንድናደርግ ራሱ ነጻ ጥሪ ያቀርብልናል፡፡ እንግዲያውስ ልደት ማለት ከፍጡራዊ ሕይወት ወደ ፈጣሪ ሕይወት መወለድ ማለት ነው፡፡ ፍጡራዊ ሕይወት ምድራዊ ነው፤ መለኮታዊ ሕይወት ሰማያዊና ዘላለማዊ ነው፡፡

ልደት ሙሉ እግዚአብሔር ያልተጨማመረ፤ ያልተቀናነሰ እግዚአብሔር ሁለንተናውን፤ ማንነቱን ሙሉ በሙሉ ራሱን ለሰው ልጅ መስጠት ማለት ነው፤ ስለዚህ ራሱን ለኛ ስጦታ ሆኖ ሲሰጠን ከዚህ በላይ ያልሰጠን ምንም ነገር የለም፡፡መድኃኔዓለም ክርስቶስ የቅድስት ሥላሴ ምልአት ነው፡፡

እኛም በእግዚአብሔር የምናምን የሰው ልጆች በየወቅቱ በንስሓ ሕይወት ስንወለድ ሙሉ ማንነታችንን ለሰጠን ፈጣሪ ራሳችንን መልሰን መስጠት ያስተማረን እራሱ ነው፡፡

አበው ሲመስሉ-እፍኝ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ፤ ማለትም ትንሽ ነገርን ምክንያት አድርጎ ትልቅ ነገርን ለማግኘት…የማይረባውን ነገር ምክንያት በማድረግ…እንደማለት ነው፤ ጊዜያዊውን፤ ውሱንን…ሰጥቶ ዘላለማዊውን መቀበል/ማግኘት/ማለት ነው፡፡

ሆኖም ግን እግዚአብሔር ሁሉ ሞልቶት ሳለ ባንሰጠው ኖሮ ባዶ እጁን ይቀር ይመስል ሁሉ የኛን ስጦታ እሱ ምንም ነገር እንደሌለው አድርጎ ነው የሚቀበለን፡፡

እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከተወለደ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬ የክርስቶስ ልደትን ማክበር ማለት የኛ ልደት ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ብቻ ነው የአምላክ መወለድ ትክክለኛ ትርጉም የሚያገኘው፤ በመሠረቱ የኛ መወለድ በዓመት አንዴ ወይንም በዓመታት አንዴ…ሳይሆን በየቀኑ ነው መሆን ያለበት፤ ምክንያቱም መወለድና መመገብ ተመሳሳይ ባሕርይ ነው ያላቸው፤ ማለትም የሞቱ ሕዋሳታችን/ሴሎቻችን/ሲሞቱ ካልተተኩ ምድራዊ ሕይወት አይታሰብምና፤ እንዲያውም አዋቂዎች በየሰባት ዓመቱ ሕዋሳቶቻችን ሙሉ በሙሉ አዲስ እንደሚፈጠሩና አሮጌውን እንደሚተኩ ይናገራሉ። እውነትም ነው፤ አዋቂ ሰው ያለው ሰውነትና ሕጻንን ስንመለከት እናት ናሙና ብቻ እንደወለደች ያህል ነው፤ ሌላው ሁሉ ከነጭራሹ አዲስ ክምችት ነው፤ ከማንም ሰው የተሰወረ አይደለም፡፡ለምሳሌ አንዲት እናት ከልጇዋ በትንሽነቱ ብትለየው ወይም ልጇ በትለያትና ከአሥር…ዓመታት በኋላ ቢገናኙ ደንበኛ ባእዳን እንጂ እናትና ልጅ የሚላቸው የለም…ስለዚህ ቁሳዊ አካላችን ይህን ያህል ለውጥ ከተገባው የአምላክ ተምሳሌት የሆነው መንፈሳዊ ሕይወታችን /ማንነታችን/ ከዚህ በበለጠው እንዴት ወደ ሰማያዊ አባቱ ባሕርይ መመሳሰል አይገባውም? ሰማያዊ ውበቱን መጠበቅ/ለመጠበቅ/ መጣር ምድራዊ የቤት ሥራችን ነው፡፡ ይህን ይመስለኛል ትክክለኛው ልደት በተለይም እግዚአብሔርን አውቃለሁ አምናለሁም ለሚል ሰው፡፡

አባ ገብረወልድ ወርቁ - ሲታዊ

ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን። አዲስ አበባ

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።