ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ቱርካዊ ከማረምያ ቤት ወጣ

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 1870

alg_pope_agcaIndependent Catholic News - Tuesday, January 19, 2010 - በ1973 ዓ.ም. በር.ሊ.ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ላይ የግድያ ሙከራ ያደረገው ቱርካዊ ከእስር ተለቀቀ። ግለሰቡ ከዚህ በኋላ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ግዳጁን እንደሚፈጽምም የቱርክ መገናኛ ብዙኀን ዘግቧል።

በአሁኑ ሰዓት 52 ዓመት ዕድሜ ያለው መህሜት አሊ አጅካ በር.ሊ.ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ላይ ባደረገው የግድያ ሙከራ በጣልያን 19 ዓመታትን በእስር ያሳለፈ ሲሆን፤ በመቀጠል ደግሞ ከዚያ በፊት የአንድ ጋዜጣ አርታዒን በመግደሉ ሌላ 10 ዓመታትን በመታሰሩ በድምሩ 30 ዓመታት በእስር ቤት ማሳለፉ ታውቋል።

ምንም እንኳ በወቅቱ በቁጥጥር ሥር ሲውል ከማንም ጋር ትብብር የሌለው ግላዊ ድርጊት መሆኑን ቢገልጽም፤ ር.ሊ.ጳጳሳትን ለመግደል ለአጅካ ምክንያት የሆነው ነገር እስካሁን ምስጢር እንደሆነ ቀርቷል። በአንድ ወቅት የቱርክ አንድ አገራዊ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን፤  በሌላ አጋጣሚም በቡልጋርያ የደኅንነት አገልግሎት እንደሚመራ ገልጾ የነበረ ቢሆንም እንኳ በ1970ዎቹ በጣልያን 22 ወራትን የፈጀው ምርመራ መረጃ ሳያገኝለት ቀርቷል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ር.ሊ.ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1975 ዓ.ም. ከአጅካ ጋር ከተገናኙ በኋላ ይቅር ማለታቸው ይታወቃል።

በተደጋጋሚ የሚታዩት ኃይለኛ ቁጡነቱና "አዲስ መሲሕ ነኝ" የሚሉት ንግግሮቹ ስለአጅካ የአእምሮ ጤነኝነት ጉዳይ ቀጣይ የሆነ ጥያቄ አስነሥተዋል። ትላንትና ከእስር ሲለቀቅ ባደረገውም ንግግር "የዓለምን ፍጻሜ አውጄያለሁ፤ በያዝነው ክፍለ ዘመን መላው ዓለም ይወድማል፤ ሁሉም ሰውም ይሞታል። እኔ ዘላለማዊው ክርስቶስ ነኝ" ሲል ተደምጧል።