የአዲስ አበባ ኤጳርኪያዊ ሊ.ጳ. ብርሃነየሱስ ሱራፌልን ጨምሮ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ 20 አዳዲስ ካርዲናላትን ሠየሙ

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 3476

Cardinalateታኅሣሥ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተለመደው የእለተ ሰንበት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ጋር በማያያዝ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ሀያ አዳዲስ ካርዲናላትን የሠየሙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የአዲስ አበባ ኤጳርኪያዊ ሊ.ጳ. ብጹእ አባታችን ብርሃነየሱስ ሱራፌል እንደሚገኙበት ታውቋል።

እነዚህ ሀያ ካርዲናላት ከአምስቱም አህጉራት የተወጣጡና ከአሥራ አራት አገሮች የተመረጡ ሲሆን፤ መጪው የካቲት 7 ቀን በመንበረ ጴጥሮስ ይህንኑ ሥያሜ የሚያመለክተው ሥርዓት እንደሚከናወን ተገልጿል። ከሀያዎቹ ካርዲናሎች ውስጥ አምስቱ ከሰማንያ ዓመት እድሜ በላይ ያላቸውና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላላቸውሐዋርያዊ ሥራ ፍቅራቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የእውቅናና የክብር ሲሆን፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአዲስ ር.ሊ.ጳ. ምርጫ ቢካሄድ የመምረጥ መብት አይኖራቸውም። አሁን አዲሶቹን ሳይጨምር 110 ካርዲናላት እድሜያቸው ከሰማንያ ዓመት በታች የሆኑና በር.ሊ.ጳ. ምርጫ ወቅት የመምረጥ መብት ያላቸው ሲሆን ከየካቲት 7 በኋላ ይህ ቁጥር ወደ 125 ያድጋል።

የካርዲናልነት ሢመት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህን ለሆነ ሁሉ የሚሰጥ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ ምርጫ ሲታወቅ ካህኑ ወደ ጵጵስና ሢመት ከፍ እንዲል ሕገ ቀኖና ያዛል። በተያያዥነትም እጩው በቤተ ክርስቲያን አስተመህሮዎች ግንዛቤው፣ በመልካም ሕይወቱ፣ በአስተውሎቱና በተግባራዊ ነገሮቹ ላቅ ያለ ይሆን ዘንድም ይጠበቃል። ካርዲናልነት ር.ሊ.ጳጳሳትን ከመምረጥ ባሻገር በመንበረ ጴጥሮስ ላይ ለተቀመጡት ር.ሊ.ጳ. የቅርብ አማካሪነትንና አጋዥነትን የሚያመለክት ሲሆን፤ ይህም በጋራ ተጠርተው በመሰባሰብ ወይም በተናጠል በተፈለጉበት ወቅት የሚከናወን ነው። ከካርዲናሎች ውስጥ እዚያው ሮም ውስጥ እየኖሩ ቢሮ ተሰጥቷቸው በቅርብ ሆነው ር.ሊ.ጳጳሳትን በአገልግሎታቸው የሚያግዙ እንዳሉ ሁሉ በየአገራቸውም ሆነው ሃገረ ስብከታቸውን የሚያገለግሉ ነገር ግን አስፈላጊ አጀንዳዎች ሲኖሩ ለስብሰባ ወደ ቫቲካን የሚጠሩም አሉ።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ይህንን እወጃ ሲደመድሙም “እነዚህ አዳዲስ ካርዲናላት በክርስቶስ ፍቅር ይታደሱ ዘንድ፣ በመላው ዓለም የወንጌል ምስክሮች እንዲሆኑና በእረኛዊ ተሞክሯቸውም ሐዋርያዊ አገልግሎቴን በላቀ መልኩ ያግዙኝ ዘንድ እንጸልይ” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የካርዲናልነት ሢመት ለመጀመሪያ ጊዜ በ1977 ዓ.ም. ለስመ ጥሩው ነፍሰ ኄር ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ የተሰጠ ሲሆን፤ እንዲሁም ለዚህ ሁሉ ፈር ቀዳጆች የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ካቶሊካዊ ጳጳስ አቡነ ኪዳነ ማርያም ካሕሳይና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ካቶሊካዊ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ዓሥራተ ማርያም የምሩ መሆናቸው ይታወቃል።

 KidaneMariam Kahsay AsrateMariam Yemiru  Paulos 
 አቡነ ኪዳነ ማርያም ካሕሳይ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ዓሥራተ ማርያም የምሩ  ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ

ዋነኛ ምንጭ፡- http://press.vatican.va/content/salastampa/it/bollettino/pubblico/2015/01/04/0006/00008.html