“ለደስታ ብርታት ይኑራችሁ”

የአገልጋዮች አገልጋይ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ ለሆሳዕና በዓል ለ30 የዓለም ወጣቶች ቀን “ለደስታ ብርታት ይኑራችሁ” ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክት

pope Hosanna 2007ecበዚህ ዓመት የምናከብረው ሆሳዕና፣ የወጣቶች በዓል ዐብይ የአስተንትኖ ርእስ እንዲሆን በማሰብ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ካደረገው ስብከት “ንጹሕ ልብ ያላቸው ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና”(ማቴ 5፡8) የሚለውን ቃል መርጠናል፡፡

በዚህ የተራራው ላይ ስብከት “ደስ ይበላቸው” የሚለው ቃል ለዘጠኝ ጊዜ ያህል ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ይህ ድግግሞሽ በበርካታ የሕይወት ፈተናዎች መካከል ከጌታ ጋር በምናደርገው ጉዞ ወደ ኋላ እንዳንቀር የሚያበረታታን አዝማች የድል መዝሙር ሆኖ የጥሪያችንን ታላቅነት ያስታውሰናል፡፡

የተወደዳችሁ ወጣቶች ይህ እውነተኛ ደስታን የመፈለግ ሰብአዊ ዝንባሌ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ሁሉ ሕያው ሆኖ የሚስተዋል እውነታ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ልብ ውስጥ “እውነተኛ ደስታን” እና ምአዓትን የመፈለግ ጥማት አኑሯል፡፡ ልባችሁ ዕረፍት እንደሌለው አላስተዋላችሁምን? የሰው ልብ ዘላለማዊ እርካታ የሚሰጠውን ነገር ሳያቋርጥ ይፈልጋል፡፡

በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመርያዎቹ ክፍሎች የሰው ልጅ ለደስታ ሕይወት እንደተፈጠረ ያሳየናል፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው አንድነት ውስጥ ከራሱ እና ከተቀረው ፍጥረት ሁሉ ጋር በሰላማዊ የፍቅር እና የደስታ ሠንሠለት ተያይዞ ነበር፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን ፊት ያለገደብ የመመልከት እና በእርሱ ሕልውና ውስጥ የመመላለስ ነፃነት ስለነበረው ከእውነት ጋር ተስማምቶ በግልፅነት ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን በአዳም እና በሔዋን መሳሳት ምክኒያት ይህ ሰላማዊ፣ ግልጽ እና ንጹሕ የሆነው ወዳጅነት ሲደፈርስ፣ ኃጢአት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ገባ (ዘፍ 3)፡፡ ከዚህም የተነሳ ከፈጣሪያቸው ጋር፣ እርስ በእርሳቸው እና ከተፈጥሮ ጋር የነበራቸው መልካም ጉርብትና ተቋረጠ፤ ክስ እና አለመተማመን ሰፈነ፡፡ በዚህም አዳም እና ሔዋን ተፋፈሩ፣ ገላቸውን ሸፈኑ፤ እግዚአብሔርን እንዲያዩ የሚያስችላቸውን ብርሃን በማጣታቸው ማየት የቻሉት በዙርያቸው ያለው ሁሉ ብልሹና ምቾትን የማይሰጥ አሳፋሪ ሆነባቸው፡፡ በውስጣቸው የነበረው የሕይወት ኮምፓስ አቅጣጫውን ሳተ፤ ወደ እውነተኛ ደስታ፣ ሰማያዊ ኃብት፣ ሥልጣን እና ዘላለማዊ ወራሽነት በመምራት ፈንታ ወደ ኃዘን እና ወደ መከራ አመጣቸው፡፡

በመዝሙረ ዳዊት ሰው የሚያማውን የሰቆቃ ልመና እንሰማለን “መልካሙን ነገር ማን ያሳየናል? ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ! በርኅራኄ ተመልከተን፡፡(መዝ 4፡7) በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ መልበስ በሕይወቱ፣ በሞቱ እና ትንሣኤው ምክንያት ሰውን ከኃጢአት እስራት ነፃ አውጥቶ በብዙ በረከቶች የተሞላ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እና አድማ አጎናጸፈው፡፡

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ! የደስታችሁ ዘላለማዊ እርካታ እና መልስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሐሰት ደመና ምክር ለተዋጠው ውስጣዊ ጥማታችሁ እውነተኛውን ምልዓት የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ዳግማዊ፣ በቶር ቬርጋት እ.ኤ.አ. ነሐሴ 19 ቀን 2000ዓ.ም. በተደረገው የጸሎት ዋዜማ ላይ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት ፣ “እሱ የተማረካችሁበት ውበት ነው፣ ለእሱ ያላችሁን ከፍተኛ ዘላለማዊ ጥማታችሁ ሳትደራደሩ እንድታርፉ የሚቀሰቅሳችሁ እርሱ ነው፡፡ የሐሰት ሕይወት ጽንብላችሁን እንድታስወግዱት የሚያነቃቃችሁም እርሱ ነው፤ ሌሎች ያፈኑትን የልባችሁን ከፍተኛውን እውነተኛ ምርጫ/ መሻትም የሚያነበው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ በሕይወታችሁ ልታከናውኑ የምትመኙትን ታላቅ ነገር ማከናወን እንድትችሉ የሚያነሳሳችሁ ነው፡፡

2. ልበ ንጹሐን ደስ ይበላቸው

አሁን ደግሞ ይህ በልብ ንጽሕና የሚገኝ ደስታ እንዴት እንደሚገኝ አብረን እንይ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ ለሰው ልብ ሲናገር ጠንከር ያለ አንድምታ አለው፡፡ ልብ የሁሉ ነገር ማዕከል ነው፡፡ ስሜታችን፣ ፍላጎታችን እና ሐሳቦቻችን ሁሉ በልብ ውስጥ ተይዘዋል፡፡ ልብ የሰው ልጅ ማንነትን ጨምሮ የያዘ አካል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን እግዚአብሔር ከውጪ ያለንን መልክ ሳይሆን የሚያየው ልባችንን ነው (1ሳሙ 16፡7) እኛም እንዲሁ እግዚአብሔርን የምናየው እነደ ልባችን ቅንነት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ልብ የሰውን ልጅ ሥጋ እና ነፍስ ጠቅልሎ የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ ልብ የማፍቀርን እና የመፈቀርን ኃይል የያዘ አካል ነው፡፡

በወንጌላት እንደምናየው ልብ ንጹሕ፣ ያላደፈ እና ያልተበከለ ተፈጥሮአዊ ማንነት ያለው ነው፡፡ አይሁድ በርካታ ውጫዊ የመንፃት ሥርዓቶች ያሏቸው እንደመሆኑ መጠን ውጫዊ የሰውነት ክፍላቸውን በንጽሕና የመጠበቅ ልማድ ነበራቸው፡፡ በለምፅ በሽታ የተያዙትን እና ሥጋ ደዌ ያለባቸውን ሰዎች ሁሉ ከማኅበረሰቡ ያገልሉ ነበር፤ ኢየሱስ ግን በግልፅ እንዲህ አላችው

“ሰውን የሚያረክሰው ከሰው የሚወጣው ነገር ነው እንጂ ከውጪ ወደ ሰው የሚገባውስ አያረክስም፡፡ ወደ ሆድ ገብቶ ወደ እዳሪ ይወጣል እንጂ ወደ ልብ አይገባምና … ሰውን የሚያረክሰው ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ …. ይህ ከውስጥ ይወጣልና ሰውን ያረክሰዋል”

ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከንጹሕ ልብ የሚመነጨው ደስታ የሚገኛው የት ነው? ኢየሱስ ንጽሕናን ያጎድፋሉ ብሎ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል ከሁሉ የሚበልጠው ከሌሎች ጋር ያለን የግንኙነት ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው የልቡን ንጽሕና የሚያጎድፍበትን ነገር መርምሮ  ማወቅ እና በቅን ሕሊና

“የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎ እና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ፈተናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህንነ ዓለም አትምሰሉ” (ሮም 12፡2) ፡፡

ከዚህ ቀደም “ገንዘባችሁ እና አለኝ የምትሉት ነገር የት አለ?” ልባችሁ ማረፍያውን የት ያገኛል? ብዬ ጠይቄያችሁ ነበር፡፡ “ልባችሁ ዕረፍት የሚያገኘው በምንድነው?” ልባችን ከእውነተኛ ወይም ከሐሰተኛ ሀብት ጋር ተጣብቆ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት ልባችንን ያሳረፍንበት ነገር እውነተኛ ደስታን የሚያስገኝ አልያም ብስጭትን፣ ስንፍናን እና ዕረፍት ማጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በሕይወታችን ሊኖሩን ከሚችሉት ነገሮች ሁሉ ትልቁ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው፡፡ በዚህ ታምናላችሁ? በእግዚአብሔር ዓይኖች ውስጥ ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳላችሁ ታውቃላችሁ? ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሁን ባላችሁበት ዓይነት ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዳችሁ እና በልቡ ቦታ ያላችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ? ኢየሱስ ከሀብታሙ ወጣት ጋር ውይይት ያደረገበትን ክፍል ቅዱስ ማርቆስ ሲተርክልን እንዲህ ይላል “ኢየሱስም ወጣቱን ተመለከተውና ወደደው” (ማር10፡21) ፡፡ እውነተኛ ሀብት ያገኝ ዘንድ እንዲከተለው ጋበዘው፡፡ ወጣቶች ሆይ! ይህ የክርስቶስ የፍቅር እይታ ዘወትር በሕይወት ጉዟችሁ ሁሉ ከእናንተ ጋር ነው፡፡

ወጣትነት እጅግ ጨዋ፣ ውብ እና የተወደደ የፍቅር ግንኙነት በልባችን የሚወለድበት የደስታ ጊዜ ነው፡፡ ይህ የማፍቀር እና የመፈቀር ችሎታ ምን ያህል ኃይለኛ ነው! ይህ ውድ የወጣትነት ሥጦታ እንዲጠወልግ በቸልተኝነት አትተዉት ወዳጆቻችንን ለግል ጥቅማችን እና  ለጊዜያዊ ደስታ መጠቀም ስንጀምር ፍቅር የመሥጠት እና የመቀበል ኃይላችን ይጠወልጋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ልቦች ይሰበራሉ፣ የኀዘን ማረፍያ መሆን ይጀምራል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ለመስጠት እና ለመቀበል አትፍሩ ይህ ፍቅር ኢየሱስ ያስተማረን እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ታጋሽ እና ደግ” በማለት የገለጸው ፍቅር “አይመቀኝም፣ አይኮራም፣ ይታገሳል፣ አይቀናም፣ ቸርነትን ያደርጋል፣ አይመካም፣ አይታበይም፣ የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱን አይፈልግም፣ አይበሳጭም፣ በእውነት ደስ ይለዋል እንጂ ስለዓመፃ ደስ አይለውም” (1ቆሮ 13፡4-8) ፡፡

ወጣቶች ሆይ! የሰውን ልጅ የማፍቀር ጥሪ እውነተኛ መልክ ፈልጉ ብዬ አበረታታችኋለሁ፤ ፍቅር ጊዜያዊ፣ የፆታ ግንኙነት የሚገለጽ በማስመሰል እውነተኛ መልኩን አበላሽቶ የሚያቀርብልንን ዘመን ዋጁት! ፍቅር በባሕርዩ ውብ፣ አንድነት የነገሠበት፣ በመተማመን የበለጸገ፣ በኃላፊነት የተሞላ ነው፡፤

 “ዛሬ መደሰት” የሚል ስብከት በየቦታው ይሰማል፤ ዘላቂ ውሳኔዎችን ማድረግ፣ ለሕይወት ሙሉ ታማኝ ለመሆን መወሰን ወዘተ… ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ ሳናውቅ የምናደርገው የሞኝ ተግባር መሆኑ ይነገራል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በተቃራኒው ለዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እምቢተኞች እንድትሆኑ አበረታተችኋለሁ፤ ይህንን መንፈስ ተቃወሙት፣ ይህንን የጊዜያዊነት መንፈስ እንድታሸንፉት እለምናችኋለሁ፡፡ ወጣቶች ሆይ! እናንተ ኃላፊነት ለመውሰድ እና በእውነት ለማፍቀር አቅሙ እና ሥጦታው አላችሁ፡፡ እኔ በእናንተ እተማመናለሁ፣ እጸልይላችኋለሁ፡፡ ይህንን መንፈስ ለመቃወም ደፋሮች ሁኑ፣ ደስተኛ ለመሆን አትፍሩ፡፡

እናንተ ወጣቶች ጀግኖች መሆናችሁን አስታውሱ! ቤተክስቲያናችሁ በፍቅር ዙርያ የምታስተምረውን ትምህርት ለመቅሰም ፈቃደኛ ከሆናችሁ ክርስትና “አታድርግ፣አትሁን” በሚል ነገሮች የተሞላ ሳይሆን ልብን የሚማርክ የአስደሳች ሕይወት መንገድ መሆኑን ማስተዋል ትችላላችሁ፡፡

“ፊቴን ፈልጉ” (መዝ 27፡8) የሚለው የጌታችን ግብዣ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ደጋግሞ ያስተጋባ፡፡ ይህን ግብዣ ስንቀበል ኃጢአተኞች መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡ በመዝሙረ ዳዊት እንደምናነበው “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? እጆቹ የነጹ፣ ልቡም ንጹሕ የሆነ” (መዝ 24፡3-4) ይላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ተሥፋ መቁረጥ እና ወደ ኋላ ማፈግፈግ አይገባንም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደምናስተውለው እና በእያንዳንዳችን ግለ ታሪክ እንደምናስታውሰው ሁልጊዜ ወደ ራሱ የሚጠራን እግዚአብሔር ነው፤ የመጀመርያውን እርምጃ የሚራመደው እርሱ ራሱ ነው፡፡ ወደ እርሱ ሕልውና እንገባ ዘንድ እግዚአብሔር ያነፃናል፡፡

ነቢዪ ኢሳይያስ በእግዚአብሔር ስም ይናገር ዘንድ በተጠራ ጊዜ በኃጢአቱ በመፍራት “ እኔ ከንፈሮቼ የረከሱብኝ፣ … የሠራዊቱን ጌታ እግዚአብሔርን ስላየሁ ጠፍቻለሁና ወየውልኝ” አለ፡፡ ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር በመላእኩ በኩል “በደልህ ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ” (ኢሳ6፡5-7) በማለት ከንፈሮቹን በመዳሰስ አነፃው፡፡ በአዲስ ኪዳን በጌንሴሬጥ ባህር አጠገብ ኢየሱስ ሐዋርያቱን በጠራበት እና መረባቸው እስከሚቀደድ ድረስ ከባህር ዓሣ በሰጣቸው ጊዜ ስምኦን ጴጥሮስ በኢየሱስ እግር ሥራ ወድቆ “ጌታ ሆይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከእኔ ወድያ ራቅ” (ሉቃ 5፡8) ብሎ በተናገረው ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል የመለሰለትን ማታወሱ ጠቃሚ ነው፤ “አትፍራ፤ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” (10)፡፡ ሌላኛው ሐዋርያ ደግሞ “ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል” ባለው ጊዜ ጌታ ኢየሱስ መልሶ “እኔን ያየ አብን አይቷል” (ዮሐ 14፡8-9) በማለት ማንነቱን ገልጦ ያሳያቸዋል፡፡

በየትኛውም ዓይነት ሕይወት ውስጥ ብትሆኑ ይህ የኢየሱስ ግብዣ በየጊዜው ይደርሳቸኋል፡፡ ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት ጉዞ መጀመር አለብን፤ አልያም እርሱ ወደ እኛ ይመጣ ዘንድ ፈቃደኝነቱ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም በጌታ በኢየሱስ መንፃት የሚያስፈልገን ኃጢአተኞች ነን፡፡ በተለይም በምሥጢረ ንሰሐ በኩል ከኢየሱስ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር እና በየጊዜው በዚህ ምሥጥር መታደስ አለብን፡፡ በዚህ ምሥጢር የማያልቀውን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ምኅረት እንለማመዳለን፡፡

የተወደዳችሁ ወጣቶች ሆይ! ጌታ ሊያገኘን ይፈልጋል፤ እኛ እንድናየው ራሱን ሊገልጥልን ይፈልጋል፡፡ ይህ እርስ በእርሳችን የምንተያይበት መንገድ የጸሎት ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ የፍቅር ግንኙነት እንመሠርታለን፡፡ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ፤ ጸሎት ታደርጋላችሁ? የጸሎት ሕይወት ልምምድ አላችሁ? በዚህ የጸሎት ሕይወት ውስጥ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን አድማጮችም ጭምር ነን፡፡ በመንበረ ታቦት ፊት ለፊት በምንጸልይበት ጊዜ እኛ እግዚአብሔርን እናየዋለን፣ እግዚአብሔርም እኛን ያየናል፡፡ እኛ ወደ እግዚአብሔር እንመለከታለን፣ እግዚአብሔርም ወደ እኛ ይመለከታል፡፡

በዚህ በጸሎት ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እና ቅዱሳት መጽሐፍትን በማንበብ ስለ ጌታችን እና ስለራሳችን ሕይወት የበለጠ ማወቅ እንችላለን፡፡ በኤማሁስ መንገድ ላይ እንደነበሩት ደቀመዛሙርት (ሉቃ 24፡13-35)  የጌታ ድምፅ በውስጣችን ልባችንን ያቃጥለዋል፡፡ ሕልውናውን እንድናውቅ ዐይኖቻችንን ከፍቶ በእኛ ላይ ያለውን ዓላማ ያስታውቀናል፡፡

አንዳንዶቻችሁ በተቀደሰው የጋብቻ ሕይወት ለመኖር በልባችሁ ይሰማችሁ ይሆናል፣ ሌሎቻችሁ ደግሞ ራስን ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ ክህነታዊ አገልግሎት የመስጠት ስሜት ይሰማችሁ ይሆናል፡፡ ጥሪ ጊዜው ያለፈበት ፋሽን አይደለም፤ ቤተ ክርስትያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስለጥሪ የምታስብበት ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ስለዚህ እናንተም የምንኩስና ወይም የክህነት ጥሪያችሁን እንድታስቡበት እና እንድትጸልዩበት አደራ እላችኋለሁ፡፡ በንጹሕ ልብ ምን እንደሚሰማችሁ አስቡ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ የሚፈልገውን ለእርሱ ለመስጠት አትፍሩ፡፡ ለእግዚአብሔር ጥሪ “እሺ” በማለት በቤተክርስትያን እና በማኅበረሰቡ ውስጥ አዲስ የተሥፋ ዘር እንሆናለን፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ደስታችን መሆኑን አትርሱ!

እጅግ ንጽሕት እና ውብ የሆነችው፣ በጸጋ የተሞላች የቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃ በጉዞአችን ሁሉ ከእኛ ጋር ይሁን!

ቫቲካን -  ቅድስት መንበር

የዮሐንስ (ዶን) ቦስኮ መታሰብያ በዓል ዕለት

ጥር 2015 ዓ.ም እ.ኤ.አ. - ትርጉም መ/ር ሳምሶን ደቦጭ ከቅ. ዮሴፍ ዘሲተውያን አ.አ. ወጣት ማኅበር

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።