“እነዚህ ሰለባዎች ካቶሊክ፣ ቅብጥ፣ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት መሆናቸው ምንም የሚፈጥረው ልዩነት የለም፤ ክርስቶስን በመመስከር የሁሉም ደም አንድና ተመሳሳይ ነው”

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 3962

Ethiopian martyrsር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በሊቢያ በአይ ኤስ (ISIS) ተገድለዋል ስለተባሉት ኢትዮጵያውያን ኀዘናቸውን በመግለፅ ሞታቸውም ቸል መባል እንደሌለበት ገለፁ።

“የክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደም አሁንም ጥሩውን ከክፋት ለመለየት ብቃት ያላቸው ሰዎች ያዳምጡ ዘንድ የሚጮኽ ደም ነው። ይልቁንም ይህ ጩኸት የሕዝብ ኀላፊነት ባላቸው ሰዎች መደመጥ አለበት” ብለዋል። አያይዘውም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት መልእክት የጌታችንን ሰላም በመመኘት የተሰማቸውን ልባዊ ኀዘን ገልፀዋል።

“ምንም ባልፈጸሙ ክርስቲያኖች ላይ በሊቢያ ውስጥ የተፈጸመውን ዘግናኝ የጥቃት ወንጀል በታላቅ ስቃይና ኀዘን ሰማሁ፤ ብፁእነትዎም የጌታችን አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ መሆን ብቸኛ ምክንያት በመሆን የልጆችዎ መገደል ጥልቅ ልባዊና አእምሯዊ ስቃይ እንደሚኖረዎት አውቃለሁ” ብለዋል ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በመልእክታቸው “እነዚህ ሰለባዎች ካቶሊክ፣ ቅብጥ፣ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት መሆናቸው ምንም የሚፈጥረው ልዩነት የለም፤ ክርስቶስን በመመስከር የሁሉም ደም አንድና ተመሳሳይ ነው” ብለዋል። ክርስቶስ ከሞት የመነሣቱ እውቀት በጨለማ ውስጥም ቢሆን ተስፋ እንደሚያፈነጥቅም ገልፀው “ይህ የትንሣኤ ደስታ በዚህ ዓመት ከጥልቅ ኀዘን ጋር ተጣምሯል፤ ሆኖም ግን በእግዚአብሔር ምሕረታዊ ፍቅር የምንኖረው ሕይወት ክርስቲያኖች ሁሉና በየትኛውም ሃይማኖታ ውስጥ ያሉ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ከሚሰማቸው ስቃይ የላቀ ጠንካራ ነው” በማለትም የክርስቶስ ትንሣኤ ከስቃይና ኀዘን የበረታ መሆኑን ተናግረዋል።

በመጨረሻም ር.ሊ.ጳ. ከልብ የሆነ መንፈሳዊ ትብብረንና በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአንዳንድ የእስያ አገሮችም ቀጣይ የሆነ በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው ሰማዕትነት በጸሎት አብረው መሆናቸውን በመልእክታቸው አስተላልፈዋል።

ምንጭ፡ http://www.catholicnewsagency.com/news/pope-on-isis-killings-blood-of-ethiopian-christians-cries-out-to-be-heard-52878/