ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ የባህርዳር-ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስነት ሥርዓት ተከናወነ።

Abune Lisaneሚያዝያ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ የባህርዳር-ደሴ ሀገረስብከት ጳጳስነት ሥርዓት ተከናወነ። ለዕለቱ መታሰቢያ ከተዘጋጀው መጽሔት መግቢያ ላይ ያገኘነውን ጽሑፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል

ብፁዕ ወቅዱስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ ቀዳማዊ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት መመሥረቱን እ.ኤ.አ ጥር 19 ቀን 2ዐ15 በሮም በይፋ ያበሰሩ ሲሆን ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስ የሀገረስብከቱ ጳጳስ ሆነው መሰየማቸውን በዚሁ ቀን አውጀዋል፡፡ የዚህ አዲስ ሀገረስብከት መቋቋም የኢትዮጵያ ከቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተልዕኮዋ የሆነውን ሁለንተናዊ የሰው ልጆች ዕድገት በተጠናከረ መልኩ ለማከናወን ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ እግዚአብሔር አምላካችን ስለደረገልን መልካም ነገር ሁሉ ክብርና ምስጋና ለእሱ ይሁን፡፡

የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የተቋቋሙትን ሀገረስብከቶች ሐዋርያዊ አስተዳደሮች ቁጥር ወደ 13 ከፍ አድርጐታል፡፡ ሀገረስብከቱ በይፋ ራሱን ችሎ እስከተቋቋመበት ድረስ የአዲስ አበባ ሀገረስብከት አካል ሆኖ የቆየ ሲሆን 22435ዐ ስኩየር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋትና 18484ዐዐዐ ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል፡፡

የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት እንደ ሀገረስብከት ከመቋቋሙ በፊት የበተለያዩ የዕድገት ሂደቶች ውስጥ አልፏል፡፡ ቀደም ሲል እ.ኤ.አ በ2ዐዐ5 በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ጠቅላይ ጽ/ቤት ሥር የተቋቋሙት የባህር ዳር እና የደሴ ኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሂደቱ መነሻ ምዕራፍ ተደርጐ ሊመሰድ ይችላል፡፡ በመቀጠልም እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2ዐ1ዐ የባህር ዳር ሐዋርያዊ አስተዳደር በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ ሀገረስብከት ስር ሆኖ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶች በብፁዕ አቡነ ልሣነ ክርስቶስ ኃላፊነት እየተመራ ከቆየ በኋላ እነሆ አሁን በእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቃድ ወደ ሀሃረስብከት ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡

ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት ክልል የተለያዩ የቁምስና  ቤተክርስቲያናት፣ ገዳማት ተቋማት አማካኝነት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በርካታ የሐዋርያዊ ፣ የማህበራዊ አገልግሎትና የልማት ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች፡፡  እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች ለህብረተሰቡም ሆነ  ለቤተክርስቲያኒቱ አማንያን ያበረከቱት ጉልህ ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ወደፊት ሀገረስብከቱ በመንፈሳዊም ሆነ በማህበራዊ አገልግሎትና በልማት ሰፊ ሥራ መሰራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ እውን ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ፀጋና በረከቱን እንዲያበዛልን እንለምናለን፡፡ የባህር ዳር-ደሴ ሀገረስብከት ተልዕኮውን በስኬታማ መልኩ ይፈፀም ዘንድ ሁላችንም የተቻለንን ድጋፍና አስተዋጽኦ እንድናደርግም ይጠበቅብናል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን አዲሱን የባህርዳር-ደሴ ሀገረስብከትና አገልጋዩን ብፁዕ አቡነ ልሳነክርስቶስ ማቴዎስን ይባርክልን፡፡ አሜን፡፡

የእግዚአብሔር አገልጋየች አገልጋይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘላለማዊ መታሰቢያ

ቤተክርስቲያን ለምዕመናን የምታበረክተው አገለግሎት ፍሬአማነት ሁላችንንም የሚያሳስበን ዐብይ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀረገ ስብከት የቆዳ ስፋት ከፍተኛ በመሆኑ ለምዕመናን የምናበረክተውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት አንዳንድ የሀገረ ስብከቱን ክልሎች እንደ አንድ ሰበካ ማቋቋም ትልቅ ሐዋርያዊ ፋይዳ ያለው ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የመንጋው እረኛ የምዕመናንን አገልግሎት ከፍ ወዳለው ደረጃ ለማድረስ ካለው ጥልቅ ሐዋርያዊ ፍላጐት የተነሳ ከዚህ የሚከተለውን ሐዋርያዊ ድንጋጌ አስተላልፈዋል፡፡

ለምዕመናን ነፍስ የምናበረክተውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ የቅዱስ  ጴጥሮስ ተተኪ የኩላዊቷ ቤተክርስቲያን አባት በሰጡት ሐዋርያዊ ትዕዛዝ እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ካርዲናል ባቀረቡት ሐዋርያዊ ምክር በመመራት ቤተ ክርስቲያን በሰጠችን ሐዋርያዊ ስልጣን መሠረት የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከትን መመሥረት አውጃለሁ፡፡

ይህ የባህር ደር ደሴ ሀገረስብከት ተብሎ የሚጠራው ሰበካ በምሥራቅ ቤተክርስቲያን ሕገ ቀኖና መሠረት መብቶችን እና ግዴታዎችን አጠቃልሎ የያዘ ራሱን የቻለ ጳጳስ ያለው ሰበካ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በባህር ዳር ደሴ ከተማ የሚቆመው ካቴድራል በመንበረ ጳጳስ ሆኖ መጠርያው ለ "እግዚአብሔር አብ" የተሰጠ ነው፡፡ ለዚህ አዲስ ሰበካ ጠባቂ እና ባልደረባ ይሆን ዘንድ ቅዱስ ፍሬሚናጦስ አባ ከሳቴ ብርሃንን መርጠናል፡፡

አዲሱ የባህር ዳር ደሴ ሀገረስብከት በውስጡ ሦስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን ክልሎች ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ክልሎች ሥር የሚከተሉት ቀጠናዎች የሰበካው ቀጠናዎች ሆነው ተጠቃልለዋል፣ እነዚህም መተከል፣ ሰሜን ጐንደር፣ ደቡብ ጐንደር፣ ምሥራቅ እና ምዕራብ ጐጃም፣ አገው እና አዊ ዞን፣ ዋግምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ የኦሮማያ ቀጠና አንድ፣ አራት እና አምስት ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሥርዐቱ እንዲፈፀም እና ሰነዶቹም ወደ ቅድስት መንበር መዝገብ ቤት እንዲላኩ ይህ አዋጅ ያዛል፡፡ በዚህ አዋጅ ያወጣናቸው መመርያዎች በሙሉ ተፈፃሚ እንዲሁኑ ወደፊትም ተጠብቀው እንዲቀጥሉ ወስነናል፡፡ የጌታ ዓመት ተብሎ በሚጠራው በ2ዐ15ዓ.ም በጵጵስናዬ ሁለተኛ ዓመት ጥር ዘጠኝ ቀን በሮም ቅድስት መንበር ተሰጠ፡፡