የኩባው መሪ ራውል ካስትሮ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስን ጎበኙ።

Written by Super User on . Posted in ዜናዎች

Raul Castroየኩባው መሪ ራውል ካስትሮ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስን ጎበኙ።

“አባታዊ ምክርዎ እና ትኅትናዎ ወደ ቤተክርስቲያን ስለመመለስ እንዳስብ አድርጎኛልና አመሰግንዎታለሁ”

የኩባው መሪ ራዉል ካስትሮ በቫቲካን ተገኝተው ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስን ከጎበኙ በኋላ በር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ ትሕትና እና አባታዊ ምክር መማረካቸውን ገልጸዋል። ር.ሊ.ጳ. አሜሪካ ለበርካታ ዘመናት በኩባ መንግሥት ላይ ጥላው የነበረው ሁለንተናዊ ማዕቀብ እንዲነሳ እና በሁለቱ ሃገራትና ሕዝቦቻቸው መካከል አዲስ ምዕራፍ እንዲከፈት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረጋቸው ፕሬዝደንት ካስትሮ ምስጋናቸዉን በርሳቸውና በመላው የኩባ ሕዝብ ስም ለር.ሊ.ጳ. አቅርበዉላቸዋል። 

የኩባው ፕሬዝዳንት ከር.ሊ.ጳ. ጋር የነበራቸዉን ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ “ ር.ሊ.ጳ. በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠሉ እኔም በበኩሌ እንደገና ጸሎት ለመጸልይ እና ወደ ቤተክርስቲያን ለመመለስ መንፈሳዊ ጉዞዬን እጀምራለሁ፣እኚህ አባት ያስተላለፏቸውን መልእክቶች ሁሉ አድምጫለሁ፣ በአባታዊ ምክራቸው እና በትሕትናቸው ተማርኬያለሁ” በማለት መግለጫ ሰጥተዋል።  ከዚሁ ጋር አያይዘው የኩባ ሕዝብ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መስከረም ወር ላይ ር.ሊ.ጳ. ወደ ኩባ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ ጉብኝት በታላቅ ናፍቆት እየተጠባበቁ እንደሆነ ለር.ሊጳ. ፍራንቸስኮስ ገልጸዉላቸዋል። የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ለ50 ደቂቃ የዘለቀ ሲሆን በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ ካስትሮ በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና የሚገኘው ካቴድራል 200ኛ ዓመት ማስታወሻ የሆነ የብር ሜዳሊያ ልር.ሊ.ጳ. ያበረከቱ ሲሆን ሜዳልያው ለካቴድራሉ ማስታወሻ ከተሰሩት የብር ሜዳልያዎች በአሁኑ ወቅት ከሚገኙት የመጨረሻዎቹ 25 ሜዳልያዎች መካከል አንዱ መሆኑም ታውቋል። ፕሬዝዳንቱ ከአሥር የሃገራቸው የልዑካን ቡድን አባላት መካከል  ስለስደት አስከፊ ገጽታ የሚያሳየዉ ስዕል ሰዓሊ የሆነውን የሰዓሊ ኮቾ (KOCHO) የስዕል ሥራ ጨምረው ለር.ሊ.ጳ. ያበረከቱ ሲሆን ይህ የስዕል ሥራ በባህር ውስጥ የተሰበረች ጀልባ ውስጥ በሞት እና በሕይወት መካከል የሚገኝ ሰው በተቆረጠ መስቀል ፊትለፊት ሆኖ ሲጸልይ የሚያሳይ ስዕል ነው።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በበኩላቸው በቅርቡ ያወጡትን “የደስታ ወንጌል” የተሰኘውን ሃዋርያዊ መኣእክታቸውን እና ቅዱስ ማርቲን ልብሱን ለድሆች ሲያካፍል የሚያሳየዉን ስዕል ለፕሬዝዳንቱ አበርክተውላቸዋል።