“የድምፅ አልባዎቹ ድምፅ” ሊ.ጳ. ኦስካር ሮሜሮ ብፅእና ታወጀ

blessed Romeroበ1972 ዓ.ም. መሥዋዕተ ቅዳሴ ሲያሳርጉ የተገደሉት ኤልሳልቫዶራዊው ሊ.ጳ. ኦስካር ሮሜሮ ያለፈው ቅዳሜ ከ200 ሺህ ሕዝብ በላይ በተገኘበት ሥርዓተ ቅዳሴ በዋና ከተማዋ ሳንሳልቫዶር ብፅእናቸው ታውጇል።

በር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ መልእክተኛ ካርዲናል አንጄሎ አማቶ የብፅእናው መልእክት ሲታወጁ በትልቁ የተሳለው የሊቀ ጳጳሱ ሮሜሮ ስእል የተገለጠ ሲሆን መዝሙርና ታላቅ የደስታ ድምጽ ከተለያዩ አገራት ከተሰበሰበውና የከተማዪቱን ዐቢይ አደባባይ ካጨቀው ሕዝብ ተስተጋብቷል።

በ1909 ዓ.ም. በኤልሳልቫዶር የተወለዱት ሊ.ጳ. ኦስካር ሮሜሮ የንኡስና ዐቢይ ዘርአ ክህነት ዝግጅታቸውን አጠናቀው በሮም የግሬጎሪያና ዩኒቨርስቲም ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በ1934 ዓ.ም. ሢመተ ክህነትን ተቀብለዋል። በቆሞስነት፣ በአገረስብከት ጸሐፊነትና የንኡስ ዘርአክህነት ኃላፊ በመሆን ለዓመታት ካገለገሉ በኋላ ረዳት ጳጳስ ለመሆን በ1962 ዓ.ም. ተመረጡ፤ ከዚያም በ1969 ዓ.ም. የሳንሳልቫዶር ሊቀ ጳጳሳት ተብለው ተሠየሙ።

“የድምፅ አልባዎቹ ድምፅ” በመባል የድኾች የተጨቆኑት ተሟጋችነታቸው ጎልቶ የሚነገርላቸው ብፁእ ሮሜሮ መጋቢት 15 ቀን 1972 ዓ.ም. ነበር በአንድ የሆስፒታል ቤተ ጸሎት ውስጥ በቅዳሴ ወቅት ደረታቸው ላይ ተተኮሶባቸው የተገደሉት። ኤልሳልቫዶር በእርስ በእርስ ጦርነት በነበረችበት በዚያ ወቅት ፍትሕ ካጡትና ከተጨቆኑት የአገራቸው ዜጋዎች ጋር በመወገን የወንጌልን ትምህርትና እውነት በታላቅ ድምፅ ስላስተጋቡ ግድያው ቢፈጸምባቸውም በወቅቱ የግድያውን ኀላፊነት የወሰደ ወገን አልተገኘም ነበር። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት የመራው ቡድን ባደረገው ማጣራትና ድምዳሜ በጊዜው በነበረው የመንግሥት አካል የመከላከያ ባለሥልጣን ትእዛዝ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

የብፁእ ሮሜሮን ብፅእና እወጃ ተከትሎ የአሜሪካኑ ርእሰ ብሔር ኦባማ “ስለ ድኻውና የተጨቆነው የኤልሳልቫዶር ሕዝብ ሲሉ የታዘቡትን ክፋት ያለምንም ፍርሃት የተጋፈጡ፣ ከግራም ሆነ ከቀኝ ክንፎች ሳይሆኑ በጽናት የቆሙ አስተዋይና ብርቱ እረኛ” በማለት ሃሳባቸውን ገልፀዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስም በመልእክታቸው “ሮሜሮ ለወንጌል ታማኝ በመሆንና ከቤተክርስቲያንም ጋር በመተሳሰር በሥራቸው ያሉትን መንጋዎች መርተዋል፣ ጠብቀዋል፣ ተከላክለዋልም። ጭቆናን አይተው የልጆቻቸውን የስቃይ ጩኸት ሰምተው ከጭቆና ወደ አዲስና ወደ ፍሬያማ ምድር ነፃ ለማውጣት አግዘዋል። ሊ.ጳ. ሮሜሮ በፍቅር ኃይል ሰላምን ገንብተዋል፤ የእምነታቸው ምስክርነትንም ሕይወታቸውን ሰጥተዋል” ብለዋል።

የብፅእና እወጃ ለአንድ ክርስቲያን በቤተክርስቲያን ታወጀ ማለት የዚያ ሰው ሕይወት ለክርስቲያኖች አብነታዊ የሆነና በቅዱሳን ሱታፌም ሆኖ የእግዚአብሔር ጸጋና ትስስር መሳሪያ መሆኑ በይፋ የሚታወጅበት፤ ቀን ተወስኖለትም /የእወጃው እለት/ ዓመታዊ በዓሉ የሚከበርበት ሲሆን ይህም በነበረበት አገረ ስብከት የተወሰነ ይሆናል። በሂደትም ቅድስናው ሲታወጅ ለዓለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን ተመሳሳይ ነገሮች ይፈቀድላታል።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።