የር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ የጰራቅሊጦስ በዓል ሐዋርያዊ መልእክት

ብፁዕ ወቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ የጰራቅሊጦስ በዓልን በማስመልከት ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልእክት

Pentecosteየመንፈስ ቅዱስ በዓል ወደጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን ይመልሰናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደተገለጸው “ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፡፡ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው… በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው” ሐዋ. 2፡1-4፡፡

ከዚህ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ ሐዋርያቱ ሙሉ በሙሉ ተለወጡ፡፡ ፈሪ እና ዓይን አፋር የነበረው ደፋር ምስክር ሆነ፡፡ በሩን ዘግቶ የነበረውም ወንጌሉን ለማብሰር በሩን ከፍቶ ወጣ፡፡ ተጠራጣሪ የነበረውም በእምነት እና በፍቅር ተሞላ፡፡  ቤተክርስቲያንም በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቃ በዓለም ላይ የምስክርነት ጉዞዋን ጀመረች፡፡

ይህ የሐዋርያትን ሕይወትና ልብ የለወጠ አጋጣሚ ተሰብስበው ከነበሩበት ቤት ውጪ ተገለጠ፡፡ ለአርባ ቀናት ተዘግተው የነበሩት በሮች በመጨረሻ ተከፈቱ፡፡ ሐዋርያትም ሁሉ በውጪ ለተሰበሰበው ሰው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤና እግዚአብሔር ስለሠራቸው ድንቅ ነገሮች በሁሉም ሀገር ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ቀድሞ በባቢሎን ጠፍቶ የነበረውን የሰው ልጆች የቋንቋ ተግባቦት ክህሎት አደሰው፡፡ ይህም የሐዋርያትን አጽናፋዊ ተልእኮ የሚያሳይ ሆነ፡፡ አንዲት፣ ቅድስት፣ ካቶሊካዊት እና ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያን ሁሉንም ያለልዩነት የምታቅፍ ሆና ተወለደች፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን እናት ቤተክርስቲያን በመሆኗ በማንም ላይ በሯን አትዘጋም! ምንም ያህል ኃጢአተኛ ልጆች ቢኖሯትም በፍጹም በሯን አትዘጋባቸውም! ይህ ጥንካሬዋ እና ቻይነቷ መንፈስ ቅዱስ የሰጣት የጸጋ ስጦታ ነው፡፡ እናት ቤተክርስቲያን እናት ስለሆነች በሯን ለሁሉም ከፍታለች፡፡

በጰራቅሊጦስ በዓል በሐዋርያት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ የአዲስ ዘመን ጅማሮ ነው፡፡ ይህ አዲስ ዘመን የምስክርነት እና የወንድማማችነት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን ከላይ ከሰማያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣ እና በእሳት አምሣል በእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ራስ ላይ የወረደ ቅባት ነው፡፡ ይህ የፍቅር እሳት መራራውን የሚያጣፍጥ፣ ሰዎች የከለሉትን ድንበር ሰብሮ የሚያልፍ፣ የእያንዳንዱን ሰው ልብ የሚዳስስ የወንጌል ቋንቋ ነው፡፡ ይህ የወንጌል ቋንቋ አንድ ብቻ በመሆኑ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ጾታ እና የተወሰነ ቋንቋ የማይለይ ኩሏዊ ስጦታ ነው፡፡ በጰራቅሊጦስ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ በቤተክርስቲያን ላይ ይወርዳል፡፡ በእርሷም ውስጥ በእያንዳንዳችን ላይ ይወርዳል፡፡ እኛም ይህንን ስጦታ ተቀብለን ለራሳችን ከከለልነው የምቾት አጥር ወጥተን ለዓለም ሁሉ በምኅረት የተሞላውን የጌታን ፍቅር እንመሠክራለን፡፡ የእኛ ተልእኮ ይህ ነው! እኛም የመንፈስ ቅዱስን እሳትና የወንጌል ቋንቋ ስጦታን ተቀብለናል፡፡ በመሆኑም ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን በቃልና በተግባር እየመሰከርን በመካከላችን ሕያው እንዲሆን በመፍቀድ የብዙኀንን ልብ በዚህ የፍቅር እሳት በማቃጠል ወደ ክርስቶስ እናቀርባቸዋለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነው፡፡

ይህንን ተልእኮ ስንጀምር በእናትነቷ በሐዋርያት መካከል የተገኘችውን  የእመቤታችን ድንግል ማርያምን እናታዊ አማላጅነት እንለምናለን፡፡ እርሷ የክርስቶስና የቤተክርስቲያን እናት ነች፡፡ በዛሬይቱ ቤተክርስቲያን ላይ መንፈስ ቅዱስ በሙላት እንዲወርድ እና በእያንዳንዱ ምእመን ልብ ውስጥ የፍቅሩን እሳት እንዲያቀጣጥል በእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት እንለምናለን፡፡

መልካም የጰራቅሊጦስ በዓል ይሁንላችሁ፡፡ ለእኔም ደግሞ መጸለይ አትርሱ፡፡

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቼስኮስ

ሮም ቫቲካን

ትርጉም፡- ወጣት ሳምሶን ደቦጭ ከቅ. ዮሴፍ ዘሲታውያን ቁምስና አ.አ. 

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።