የኢ/ያ ካቶሊካዊት ቤ/ያን ሊ.ጳ. ብ. ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ 2008 ዓ.ም የዘመን መለወጫ መልእክት

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ 2008 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

"እናንተ ግን አሰቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግስትና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ፈልጉ፤ ሌላውም የቀረው ነገረ ሁሉ ይጨመርላችኋል፡፡" (ማቴ.6፡33)

2008 EC messageብፁዓን ጳጳሳት
ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ካህናትና ደናግል"
የተከበራችሁ ምዕመናን፤
በሀገር ውስጥና ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖች"
መላው የአገራችን ሕዝቦች በሙሉ፤

ከሁሉ በፊት በክርስቶስ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደዚሁም ለመላው የአገራችን ሕዝቦች በሙሉ የእግዚአብሔር አምላክ መልካም ፍቃዱ ሆኖ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ የዘመን መለወጫ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ በማለት በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያ ስም መልካም ምኞቴን አቀርብላችኋለሁ፡፡

ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሆነኸናል“ (መዝ 90፤1)

እንዳለው ከዘመናት እስከ ዘመናት መጠጊያ ሆኖን ያለፈውን 2007 ዓ/ም አስጨርሶን ወደ 2008 ዓ/ም አዲስ ዓመት ያሻገረን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

አንዱ ዘመን አልፎ ሌላው አዲስ ዘመን ሲተካ በዓመተ ምህረት ውስጥ እኛ ሰዎች በእግዚአብሔር የምህረት ስጦታ ውስጥ እንዳለን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ እርሱ በፈጠረልን ዓለምና እርሱ በሰጠን ዘመን የእርሱ ሆነን በመንፈሳዊነት በበለጠ በማደግ የእርሱ ታማኝ ልጆች ልንሆን ይገባል፡፡
ክርስቲያኖች የሆንን የክርስትና ሕይወታችንን በእግዚአብሔር በመታመንና በመልካም ምግባር እስከ መጨረሻው የሕይወት ዘመናችንን ጠብቀን እንድንጓዝ ያስፈልጋል፡፡ መልካም አርአያነታችንም ለቤተሰባችን፤ ለምዕመናንና ለህብረተሰብ ሁሉ ማሳየት ይኖርብናል፡፡ (1ጴጥ 3፡16)

እኛ ሰዎች እግዚአብሔር በሰጠን ጊዜ ልንጠቀምበት እንጂ በከንቱ ልናሳልፈው አይገባም፡፡ በቤተሰባችን ውስጥና በተሠማራንበት የሥራ መስክ › በተሰጠንም ሃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት በተግባር መልካም ዜጎች ሆነን በመኖርና በመታነጽ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት ይኖርብናል፡፡ ሁላችንም እግዚአብሔር በሰጠን ዓመት ልንደሰት ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን ጊዜ በሥራ ላይ እናውለው፡፡ ባቀድነውና በምንሠራው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን እናስቀድም፡፡ የምናስበውን ዕቅድና ሥራዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ከመሠረትን ተሰፋችን ይለመልማል ውጤቱም ያማረ ይሆናል፡፡

ባለፈው 2007 ዓ/ም በዓለማችን ብዙ አሳዛኝ ነገሮች አይተናል፤ ሰምተናል፤ በተለይ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን ግፍ አንረሳውም፡፡ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውጤቱ እንዴት አስከፊና አሳዛኝ መሆን እንደቻለ የተገነዘብንበት ዓመት ነበር ፡፡ የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን በዘነጉ የራሳቸውን ጊዜያዊ ጥቅም በማስቀደም በሰው ልጅ ችግር በመጠቀም ግፍ እየሠሩ የሚገኙ ወገኖች ከዚሁ ድርጊታቸው እንዲታረሙ ቤተ ክርስቲያን በጥብቅ ትጠይቃለች ፡፡ ወገኖቻችንም በሚቻላቸው ሁሉ በሕጋዊ መንገድ ላይ የተመሰረተ የጉዞ ሰነድ ብቻ ይዘው አንዲገለገሉ እንመክራለን ፡፡ ከሀገር ውጪ ያለ ሕይወት ሁሉ ጥሩ ጎን እንዳለው ሁሉ የእዚያን የህል እጅግ አስቸጋሪና ውስብስብ በአደጋ የተሞላ ሕይወት እንዳለው ሳንታክት ማስተማር አለብን፡፡ ደግሞም በአገር ላይ መሥራትና መለወጥ መቻሉን አንርሳ ፡፡ ብዙ ጊዜ ውጭ ተሄዶም የሚሠራው ሥራ በአገርም ላይ አለ ፡፡ የሥራ ክቡርነትን ቤተክርስቲያን ሁልጊዜ ታስተምራለች (2 ተሰ 3፡6-15) ፡፡ የሚያስከብረው ሥራን ሳይንቁ መሥራት ነው ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በድህነትና በረሃብ የምትታወቅበትን ስም ከመላው ዜጎቿ ጋር በቁጭት በመነሳት በትምህርት፤ በጤና፤በመንገድ ሥራና በተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በመንቀሳቀስ ለዕድገቷ ተፈጻሚነት የምታከናውናቸው እንቅስቃሴዎች በአዲሱ ዓመትም በበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታችን የጸና ነው፡፡ በአዲሱ 2008 ዓ/ም የምንጀምረው ሁለተኛው የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በእግዚአብሔር ቡራኬና እርዳታ እንዲሁም በኛ ንቁ ተሳትፎ እንዲካሄድ ሁላችንም እንድንጸልይና ተግባራዊም እንድናደርገው አደራ እላለሁ፡፡

በሚቀጥለው ጥቅምት 2008 ዓ/ም የሚካሄደው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ በቤተስብ ላይ ያተኩራል፡፡ ስለዚህም ሰለቤተሰብ ጸሎት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልም ሆነ የቤተክርስቲያን አስተምሮ አይቀየርም፡፡ ቤተክርስቲያናቸንም ለቤተሰብ ልዩ ክብርና ተኩረት ተሰጣለች፡፡ ቤተሰብ የኀብረተሰብና የቤተክርስቲያን መሠረት ነውና፡፡ ክርሰቲያናዊ ጋብቻ የሚመሠረተው በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል ብቻ ነው (ማቴ 19፡4-6)፡፡ በወንድና በሴት መካከል ከሚመሰረት ጋብቻ ውጭ ሌላ ጋብቻ የለም፡፡ ልጆችም የእግዚአብሔር ውድ ስጦታዎችና የጋብቻም ፍሬዎች ናቸው፡፡ የባልም ሆነ የሚስት የትዳር ሕይወት መሰረቱ በምሰጢረ ተክሊል ውስጥ የሚገቡት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ስለዚህ በካቶሊካዊ ጋብቻ ፍች የለም፡፡ ነገር ግን በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያናዊ ቤተሰቦች ልንጸልይ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱና በምሕረቱ እንዲጎበኛቸው ልንለምንላቸው ይገባል ፡፡

ሰላም የልማትና የብልጽግና መሠረት ነው ፡፡ ከከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም መኖር ጥቅሙ የጋራ ነው፡፡ አሁንም ተስፋ ሳንቆርጥ ለሰላም የምናደርገውን ጸሎትና ጥረት ከጎረቤቶቻችን ጋር በኅብረት በመሆን እንድንቀጥል አደራ እላለሁ፡፡ ለዚህም የሰላሙ ንጉሥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን ለኛም ለጎረቤቶቻችንም ሁሉ አንዲሰጠን እንጸልይ ፡፡

በዚህ በዓል ላይ የእኛ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በችግር ላይ የሚገኙ አቅመደካሞች፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች፤ የአልጋ ቁራኛ ሕሙማን ለሆኑ ሁሉ ርኀራኄያችንንና እርዳታችንን በመለገስ ከእነርሱ ጋር በመሆንም በዓላችንን በደስታ አብረን እንድናከብር አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

በሆስፒታልና በቤታችሁ በሕመም የምትገኙ ወገኖች እግዚአብሔር ምህረቱንና ጤንነቱን እንዲሰጣችሁ፤ በየማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የህግ ታራሚዎች እግዚአብሔር ከእሥራታችሁ እንዲፈታችሁ፤ በተለያዩ ምክንያቶች በሥራ፣ በትምህርት፣ እንዲሁም የአገራችንን ድንበር ለመጠበቅ በየጠረፉ የምትገኙና ሰላም በማስከበር ላይ ላላችሁ የመከላከያ ሠራዊት በሙሉ ፤ ከዘመድ ርቃችሁ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖች በሙሉ አዲሱ ዓመት የሰላም፤የጤናና የፍቅር እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ፡፡

በዐውደ ዓመቱ እግዚአብሔር አገራችንንና ህዝቦቻችንን ሁሉ ይባርክ፡፡

+ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።