አባ ተስፋዬ ታደሰ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና አፍሪቃዊ የኮምቦኒ ማኅበር 46ኛው ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመረጡ

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 2163

አባ ተስፋዬ ታደሰ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና አፍሪቃዊ የኮምቦኒ ማኅበር 46ኛው ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመረጡ

Abba Tesfaye Tadesseበመላ ዓለም ከሚገኙት የኮምቦኒ ልኡካነ ወንጌል ተጠሪ አለቆች፣ የማኅበር ጠቅላይ አለቃና አማካሪዎች በቅርቡ በሮማ 18ኛው ጠቅላይ ጉባኤ ያካሄዱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ተጋባእያኑ ማኅበሩ በጠቅላይ አለቃነትና እንዲሁም የጠቅላይ አለቃ መማክርት በመሆን ያገለገሉት የአገልግሎት ተልእኮ ዘመናቸውን የጨረሱትን የሚተኩ ጠቅላይ አለቃና መማክርት ለመምረጥ ባካሄደው የምርጫ ሥነ ሥርዓት በምልኣተ ድምጽ ኢትዮጵያዊው የማኅበሩ አባል ባለፉት ስድስት ዓመታት የማኅበር የመሠረተ ሕንጸት የመላ የአፍሪቃ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ጉዳይ አማካሪ በመሆን ያገለገሉትን አባ ተስፋዬ ታደስ ገብረሥላሴን መርጠዋል።

ኣባ ተስፋዬ ታደሰ በኢትዮጵያ ሐረር ክፍለ ሃገር እ.ኤ.አ. መስከረም 22 ቀን 1969 ዓ.ም. የተወለዱ በአዲስ አበባ ሰበካ ያደጉ እ.ኤ.አ. ነሐሴ 26 ቀን 1996 ዓ..ም. ማዕርገ ክህነት የተቀበሉና ሮማ በሚገኘው ጳጳሳዊ የሥነ ምስልምና የጥናት መንበረ ጥበብ ተምረው ሊቅነትን ያስመሰከሩ መሆናቸውን የገለጠው የቅድስት መንበር መግለጫ አክሎ አባ ተስፋዬ ታደስ የአረብኛ ቋንቋ በሚገባ ለማወቅ ወደ ግብጽ ከተላኩ በኋላ ከ 1997 ዓ.ም. ጀምረው ለሦስት ዓመት በካርቱም ያገለገሉ መሆናቸውንም ጠቅሷል። ክቡር አባ ተስፋዬ በማኅበሩ ታሪክ ለዚህ ስያሜ የመጀመሪያ ኢትዮጵያው ብቻ ሳይሆኑ የመጀመሪያው አፍሪቃዊ በመሆን የማኅበሩ 46ኛው ጠቅላይ አለቃ ሆነዋል።

አባ ተስፋዬ ለዚህ አዲስ ተልእኮ እንደተመረጡም ሚስና የዜና አገልግሎት ላቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ሲመልሱ፦ ዳንኤል ኰምቦኒ በሳቸው መመረጥ ሳይሆን ማኅበሩ የመጀመሪያ አፍሪቃዊ ጠቅላይ አለቃ በማግኘቱ ምክንያት ደስተኛ እንደሚሆን አስባለሁ ብለው ከእኔና ከምወክለው ተልእኮም አንጻር የተሰጠኝ ተልእኮ ትልቅ ኃላፊነት ነው፣ አፍሪቃውያን የማኅበሩ አባላት መሆን ከጀመሩ ቆይተዋል፣ ሆኖም ማኅበሩ ጠቅላይ አለቃ በማድረግ አንድ አፍሪቃዊ ሲመርጥ ለመጀመሪያ ጊዜው ነው። አሁን አፍሪቃ ቤተኛ ነች። የቅዱስ ዳንኤል ኮምቦኒ ልጆች ወንድሞቼ በእኔ ላይ ያላቸውን እምነት አድሰዋል፣ ኮምቦኒ ለአፍሪቃ ከነበረው ፍቅር አንጻር በእውነቱ ደስ እንደሚሰኝ ነው። ከአንዲት በአፍሪቃ የምትግኘት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውሁዳን የሆኑባት አገረ ኢትዮጵያ ዜጋ ነኝ። ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ትንሽ ብትሆንም መላዪቱን አፍሪቃ ለመወከል በቅታለች።

ኮምቦናውያን እንደመሆናችን መጠን በድኽነት ለተጠቁት ድኻ እንዲሆን ለተገደደው ለተናቀው የወንጌል ኃሴት ለማካፈል የተጠራን ነን፣ ይኽ የተልእኮው ባህል ዳግም ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ እያሳሰቡት ካለው የወንጌል ደስታ በሚል ርእስ ሥር ባቀረቡት ሐዋርያዊ ምዕዳን ዳግም በታደሰ ኃይለኛ መንፈስ የሚቀጥል ነው ብለው ማኅበሩ በኤውሮጳ በማከናወን ላይ ያለው ተልእኮ ምን እንደሚመስል ገልጠው የኮምቦኒ ማኅርረ አባላት በኤውሮጳ የሚገኙባቸውን አገሮች ጠቁመው ኤውሮጳ ልኡካነ ወንጌል የሚያስፈልጋት አገር መሆንዋ እየተካሄደ ያለው ስብሰባ እንዳሠመረበትም አስታውሰዋል። ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ለስድተኞችና ተፈናቃዮች በመስተንግዶ፣ በመጀመሪያ የእርዳታ አቅርቦትና በሕንጸት ዘርፍ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በማብራራት ያካሄዱት ቃለ ምልልስ አጠቃለዋል።

ምንጭ፡- ራዲዮ ቫቲካን