ሊቀ ጳጳሳት ብ. አ. ብርሃነየሱስ የ2005 ዓ.ም ርእሰ ዐዉደ ዓመትን በማስመልከት ለምእመናን ያስተላለፉት መልእክት፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! 

Abatachin2"ሁሉም ነገር የተገኘው ከእርሱ፣ በእርሱና፣ በርሱ ስም ነው፤ ለዘለዓለም ክብር ለእርሱ ይሁን አሜን'' (ሮሜ 11፡ 36)

(ለማዳመጥ ይህን ጽሑፍ ይጫኑ) የተወደዳችሁ ምመናን

ክቡራን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች

በሀገር ውስጥና እንዲሁም ከአገር ውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖች"

በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሰዎች በሙሉ

ለመላው የአገራችን ህዝቦችና ለካቶሊካውያን ምዕመናን ወገኖች በሙሉ ከሁሉ በማስቀደም እንኳን ለ2005 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት አዲሱ ዓመት የሰላም የጤናና የፍቅር እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴን በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም አቀርብላችኃለሁ፡፡

ዛሬ የምናከብረው በዓል የአዲስ ዓመት በዓል ነው፡፡ዓመታት የእግዚአብሔር ናቸው በየዓመቱ የሚሰጠን ጊዜ ከእግዚአብሔር ምህረትና ፍቅር ነው፡፡ የሚሰጡንም ለእኛ በረከትና ለእርሱ ክብር ነው፡፡መዝሙረኛዉ ዳዊት ''በቸርነትህ ዓመትን ትባርካለህ፤ ምድረ በዳዉም ስብን ይጠግባል'' (መዝ 64(65)11) በማለት ለእግዚአብሔር አምላኩ ይቀኛል፡፡ ሰውም በተሰጠው ስጦታ በመጠቀምና ከእርሱም ላይ በመጨመር የእግዚአብሔርን ክብር ማመስገኛ አንዱ መንገድ ነው፡፡

ይህን አዲስ ዓመት ስንቀበል እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር በማመስገን ነው፡፡ በአንጻሩም ምንልባት አንዳንዶች ደስታ ላይኖራቸውና ለምሥጋና ላይበቁ ይችላሉ፡፡ እንደምናውቀው

ደስ አለመሰኘታቸው የውስጣዊ ሰላም የማጣታችው ምልክት ነው፡፡ ሰላም የሚመጣው ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ተቆራኝቶና ተሳስሮ በመኖር ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር ከእነርሱ የራቀ ቢመስላቸውም እግዚአብሔር ግን ከፍጡሩ ርቆ የሚኖር አምላክ አይደለምና አዲሱን ዓመት ሁላችንም በአዲስ ተስፋ መጀመር ይኖርብናል፡፡ ይህም እርስ በእርሳችን በመደጋገፍና በመረዳደት ሊሆን እንደሚገባ ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡

በዚሁ አዲስ ዓመት እያንዳንዱ ሰው እንደ እግዚአብሔር ፊቃድ ይዞ የሚጀምረው እቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ በመንፈሳዊነት የቀዘቀዘ ከሆነ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቅ መንፈሳዊ ሁኔታውን በማስተካከል ሕይወቱን በምን መንገድ ሊለውጥ እንደሚችል ማሰብና መጠየቅ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ሲሆን መንፈሳዊ ዕድገት፣ ባህሪያዊ ለውጥና በትምህርትም በሥራም ዕድገት ማምጣት ይቻላል፡፡

የአገራችን ህዝቦች ለረጅም ዘመናት በሃይማኖት ተቻችሎ የመኖር ባህል ደስታቸውንም ሆነ ሐዘናቸውን የሚገልጡባቸው መንገዶች ጥልቅ መሆን፣ በአገራችን ህዝቦች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ሕዝቦች ከፍ ያለ ግምት የሚያሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችን ጥንታዊት መሆኗን ሳንዘነጋ አባቶቻችንና እናቶቻችን ይህን የአብሮነትና የመቻቻል ባሕልን በመጠበቅ ብዙ የደከሙበትን በማስታወስ ዛሬም የአገራችን ትውልድና በተለይ ወጣቶች ይህን ልዩ የሚያደረገንን በእምነት ተቻችሎ የመኖር ልምዳችንንና ወጋችንን እንደዚሁም በርካታ ዕሴቶቻችንን በህብር አጥብቀን በመያዝ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ምስክር ሊሆን የሚችለውን የኢትዮጵያን ባህል በመጠበቅ ፣ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ዛሬም ይህን የኃይማኖቶችን የመቻቻል መንፈስ ይዞ ለመጉአዝ ከሁሉም አስቀድሞ አንዱ የሌላውን እምነት በማስተዋልና በማክበር የአብሮነት የመኖር ማህበራዊ ባህላችንን በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ኑሮአችን ውስጥ አጥብቀን መጔዝ ይኖርብናል፡፡

በተጨማሪም በዚህ በምንጀምረው 2005 አዲስ ዓመት ለተሻለ የአገራችን ዕድገት በቆራጥነት ልንሠራና ልንቀሳቀስ ይገባል፡፡ መንግሥት ሊሠራቸው ያቀደውንና እየሠራ ያለውን ዘርፈ ብዙ የልማትና የእድገት አውታሮችን በመደገፍና ህብረተሰቡም በባለቤትነት መንፈስ አጥብቆ በመያዝ ብሎም በመተሳሰብ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ለመልካም ኑሮና የአገራችን መልካም ገጽታ ለተሻለ ለውጥ መላው የአገራችን ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ሊንቀሳቀሱ ይገባቸዋል፡፡ ይህንንም በታታሪነት ከቀጠልን በድኅነት ላይ በአጭር ጊዜ ድልን መቀዳጀት እንድንችል እግዚአብሔር አምላክ አንደሚረዳን እናምናለን፡፡

በአገራችን እየተካሄደው ያለው የሰው ልጅች ሕገውጥ የዝውውርን መንገድ በተመለከተ መንግሥት ትኩረት ስጥቶ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ዜጐቹን ለመታደግ እየሠራ ያለው ሥራ በማድነቅ ይህንንም በማጠናከር የአገርን ገፅታ ከመለወጥ አንፃር ዜጐች በአገራቸው ሰርተው የመኖር በህልን እንዲያበረታታ እያስገነዘብን በቅርቡ በአስቃቂ ሁኔታ ውድ ሕይወታቸውን በህገወጥ የስደት ጉዞ ላለፈው ወገኖች እግዚአብሔር ነፍሳቸውን እንዲምር ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይሰጥ ዘንድ እንመኛለን፡፡

አዲስ ዘመን ሁልጊዜ አዲስ ተስፋ ስለሚያመጣ ሁላችንም በእግዚአብሔር በመተማመን ተስፋችንን በአምላካችን ላይ እናደርገው፡፡ ተማሪዎችም ወላጆቻቸውን በመውደድና በማክበር እንዲሁም ለመምህራን በመታዘዝና በሥነ ምግባር በመመራት በአዲሱ ዓመት በየትምህርት ቤቶቻቸው የሚሰጠውን ትምህርት በትጋት እንዲከታተሉ አደራ እላለሁ፡፡ ይህንንም በዓል ስናከብር የመረዳዳት ባህላችንን ባለመርሳት ያለው ከሌላው ጋር አቅሙ የቻለውን በማካፈል የዐውደ ዓመት በዓላችንን ደስታና ፍቅር የተሞላበት አድርገን እንድናከብረው የአደራ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም፤ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕረዝዳንት፤የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕረዝዳንትን ድንገተኛ ሞት የሰማነው በከባድ ሐዘን ነው፡፡ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመላው ኢትዮጵያ አባት ከመሆናቸውም በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ በጣም ታዋቂ የሃይማኖት መሪና የሰላም አምባሳደር ነበሩ፡፡ በመሆኑም ለመላው ዓለም የሀገራችንን መልካም ገጽታ በተደጋጋሚ ያሳወቁ አሳቢና ተቆርቋሪ አባት ነበሩ፡፡

በተለይ ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያላቸው በጎ አመለካከትም ሆነ ቀረቤታ ምንግዜም በሕሊናችን ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር ብፁዕ ወቅዱስ አባታችንን በገነት ተቀብሎ ያኖርልን ዘንድ እየጸለይን ለሲኖዶስ፣ በአገራችንም ሆነ በውጭ አገር ለሚገኙ ምዕመናንና ቤተሰቦቻቸው ይጽናኑ ዘንድ በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳትና ምዕመናን ስም መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁን መሪያችንን የክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ-ሕይወት የሰማንው በጣም አስደንጋጭና ጥልቅ በሆነ ሀዘን ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለራዕይ፣ ጠንካራ ሠራተኛና ቁርጠኛ መሪ ነበሩ፡፡ በሕይወት ዘመናቸው ከለጋ ዕድሜያቸው ጀምሮ ዕውቀታቸውንና ችሎታቸውን ለሀገራቸው ያበረከቱ ጀግና ሰው ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ታላቅ መሪ፣ የአፍርካ ደግሞ በዓለም መድረክ ተቆርቋሪ፣ ጠበቃና ወኪል ነበሩ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በመሪነት ዘመናቸው ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከድህነት አረንቋ ለማላቀቅና ለቀጣዩ ትውልድ የልማት ራዕይ ለማስጨበጥ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ታታሪ መሪ ነበሩ፡፡ ይህም ራዕያቸው ዕውን ይሆን ዘንድ ትልቅ መሠረት ጥላዋል፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አገራችን ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጋር እንትደመር ያቀዱትን ዕቅድ እያደነቀች ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የበኩሏን ጥረት ታደረጋለች፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነፍስን እግዚአብሔር አምላክ ተቀብሎ በገነት ያኖርልን ዘንድ እንጸልያለን፡፡ ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ መንግሥት፣ ለባለቤታቸው ለክብርት ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን እና ልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመድ ወዳጆቻቸውና እንዲሁም ለመላውየኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ይሰጥልን ዘንድ በራሴና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፤ ካህናት፤ ገዳማውያን፤ መነኮሳትና መላው ካቶሊክ ምእመናን ስም መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

በመጨረሻም በአደረባችሁ ሕመም ምክንያት በሆስፒታሎችና በየቤቱ በሕመም ላይ የምትገኙ ሁሉ የምሕረት አባት ምሕረቱን ያውርድላችሁ በከባድ ሀዘን ውስጥም ያላችሁትን እግዚአብሔር መጽናናትን ይስጣችሁ" በየማረሚያ ቤቶችም ሆናችሁ ይህን ክብረ በዓል የምታከብሩትንም እግዚአብሔር በምህረቱ ይፍታችሁ"በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከቤተሰቦቻችሁ ርቃችሁ ለምተገኙ፣ በየጠረፉና የአገራችንን ድንበሮች በመጠበቅ ላይ ለምትገኙ ሁሉ እንዲሁም በውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ መልካም አዲስ አመት እንዲሆንላችሁ መልካም ምኞቴ ነው፡፡

አዲሱ ዓመት የሰላም የጤና የፍቅር የበረከት የብልጽግናና የደስታ ዘመን ይሁንልን፡፡ አሜን

ምንጭ ድምጽ ከቫቲካን ራድዮ ጽሑፍ E.C.S. ድረ ገጽ።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።