ሞት አሻግረን እንዳንመለከት እንደሚከለክል ግድግዳ ነው

ቅዱስ ኣባታችን ር.ሊ.ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ እሁድ ሚያዝያ 2 ቀትር ላይ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከማሳረጋቸው በፊት የዕለቱን ቃለ ወንጌል በመጥቀስ ትምህርት ሰጥተዋል። እንደ ላቲኑ ሥርዓተ አምልኮ ግጻዌ የእለቱ የወንጌል ቃል ጌታ የማርታና የማርያም ወንድም አልአዛርን ከሞት ያስነሣበት ተአምራት የሚተርክ እና ኢየሱስ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን የሚገልጥ ነበር፡፡  ዮሐ. 11፡17-37

ቅዱስ አባታችን ስለ ትንሣኤ ሲገልጡ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣት ለእኛ ለሰው ልጆች የሰጠንና ለእኛ በመጠባበቅ ላይ ላለነው ትንሣኤ ታላቅ የምስራች  ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለማክበር ሁለት ሳምንታት ብቻ በቀረን ወቅት ቅዱስ አባታችን ሞት በክርስቲያኖች አመለካከት ምን ዓይነት ትርጉም እንዳለው እንዲህ ሲሉ ገልጠዋል፤ ሞት አሻግረን እንዳንመለከት እንደሚከለክል ግድግዳ ነው፤ ሆኖም ግን ልባችን ከዚህ ግድግዳ ባሻገር ያለውን በእምነት ዓይን ያየዋል፤

እዛ ላይ ተደብቆ ያለውን ምሥጢራዊ ይዞታውን ሙሉ በሙሉ ባናውቀውም ለዘለዓለማዊ ሕይወት ያለንን ፍላጎት በተለያዩ ምልክቶች በመግለጥ ስለእርሱ ከማሰብና ከማሰላሰል አንቦዝንም፤ ዛሬ ከትንቢተ ህዝቅኤል 37፡12 በተነበበው፤ ዕብራውያን ከምድረ እስራኤል ተሰደው በነበሩበት ወቅት እግዚአብሔር የስደተኞቹን መቃብር በመክፈት ሕይወት እንደሚሰጣቸው ወደ ሃገራቸው በመመለስም ሰላም እንደሚያሰፍንላቸው እንዲህ ሲል ተናግሯል፤ ስለዚህ ትንቢት ተናገር እንዲህም በላቸው ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡-ሕዝቤ ሆይ!  እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፥ ወደ እስራኤልም ምድር አስገባችኋለሁ። ሕዝቤ ሆይ! መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ ከመቃብራችሁም ባወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ይህ በትውልድ አገር  ከወላጆች ጋር የመቀበር ፍላጎት ከዚህ ዓለም ኣድካሚ የህይወት ጉዞ የሚቀበል ሌላ አገር እንዳለ ያመለክታል፡ ይህ ኣስተሳሰብ የትንሣኤን ተስፋ ያመለክታል፤ ይህንንም በብሉይ ኪዳን በመጨረሻ ገጾች እናገኘዋል፤ ሆኖም ግን በኢየሱስ ጊዜም ይሁን አይሁዶች በሙሉ በዚህ አስተሳሰብ አይስማሙም ነበር፡ በክርስትያኖች መካከልም ቢሆን ስለ ትንሣኤ ሙታንና ዘለዓለማዊ ህይወት በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ክርክሮችና ጥርጣሬዎች ታይተዋል፤ ምክንያቱም ምሥጢረ ትንሣኤ በሰው ልጅ አስተሳሰብ  ልንረዳውና ልትገልጠው አስቸጋሪ በመሆኑ የግድ ጥልቅ የእምነት  ያስፈልጋል። የዚህ ዓይነት እምነት በዛሬው ወንጌል በማርታ አንደበት ሲነገር እንሰማለን፤ “ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስ ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ አውቃለሁ አለችው። ኢየሱስም ኢየሱስም “ወንድምሽ ከሞት ይነሣል” አላት፡፡ ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ አለችው”። ኢየሱስም ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን  ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በእኔም የሚያምን ሁሉ ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን? አላት። እርስዋም “አዎን ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው።

እውነተኛው አዲስ ነገር ይህ ነው፤ ክርስቶስ የሞት ግድግዳን አፍርሶታል፤ እርሱ ራሱ ዘለዓለማዊ ሕይወት በመሆኑ የእግዚአብሔር ሙላት በእርሱ ላይ ይኖራል፤ ለዚህም ነው ሞት በእርሱ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ያልቻለው፤ በእግዚአብሔር ፊት እንደ እንቅልፍ የነበረው የአልኣዛር ሞትና  ከሞት መነሣት ጌታ በሞት ላይ የነበረውን ሥልጣን ያሳያል።” ሲሉ ስለ ሥጋዊ ሞትና ጌታ በሞት ላይ ያለውን ሥልጣን ከገለጡ በኋላ ስለ ሌላው የባሰ ሞት ማለትም  የነፍስ ሞትና ስለ ኃጢኣት የሚከተለውን ብለዋል፡- ለጌታ  እስከ በመስቀል ላይ ሞት የዳረገው ሌላ ዓይነት ሞት መንፈሳዊ ሞት ነው ይህም ኃጢአት  ነው። ኃጢአት የሰው ልጅ ህልውናን የሚፈታተን ጠላት ነው። ይህንን ሞት ለመሻር ክርስቶስ ሞተ፡፡ የጌታ ትንሣኤ ወደ ነበርንበት ህይወት መመለስ ሳይሆን ለአዲስ ህይወት ክፍት መሆንና ለአዲስ አገር መዘጋጀት ነው፤ ይህም ኣዲስ አገር  መንግሥተ ሰማያት ነው፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮማውያን በጻፈው መልእክት ‘ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።’ በማለት የሚያስተምረው።” ሲሉ ከዚህ መንፈሳዊ ሞት መነሣት ያለብን ጊዜ አሁን መሆኑን አብራርተዋል።

በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን የዚህ ትንሣኤ ተሳታፊ ለሆነችው እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ አልአዛር እኅት ማርታ በእምነት አዎ ጌታ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ ለማለት ብቃት እንዲኖረን ጸጋ ታስገኝልን ዘንድ እንድንማጠናት አደራ ሲሉ በመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አሳርገው ምእመናኑና ነጋድያኑን በተለያዩ ቋንቋዎች በማመስገን ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል ።

ምንጭ - ራድዮ ቫቲካን

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።