ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የመንበረ ጴጥሮሳዊ አገልግሎታቸውን እንደሚያቋርጡ አስታወቁ።

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 2072

12pope 1-articleLargeየካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. - ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የመንበረ ጴጥሮሳዊ አገልግሎታቸውን ከየካቲት 21 2005 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚያቋርጡ ዛሬ ጠዋት አስታወቁ።

በቫቲካን ለተሰበሰቡ ካርዲናሎች ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው ካሰሙት ንግግር ውስጥ "በእግዚአብሔር ፊት በተደጋጋሚ ኅሊናዬን ከመረመርኩ በኋላ ከእድሜዬ እርጅና የተነሣ የመንበረ ጴጥሮስ ኀላፊነቴን ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌለኝ ርግጠኛ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ" የሚል ይገኝበታል።

ስለዚህ አገልግሎት መንፈሳዊ ጎን ሲናገሩም "ይህ አገልግሎት ከቃላትና ከድርጊቶች በተጨማሪ መሠረታዊ መንፈሳዊ ተፈጥሮ ያለው መሆኑንና በመሰቃየትና በጸሎትም እንደሚከናወን ጠንቅቄ አውቃለሁ፤ ሆኖም ግን በፈጣን ለውጦችና የእምነትን ሕይወት በጥብቅ የሚሹ ጥያቄዎች በተሞላች ዓለም መንበረ ጴጥሮስን ለመምራትና ወንጌልን ለማወጅ የአእምሮም ሆነ የአካል ጥንካሬ አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም ከቅርብ ወራት ወዲህ በአደራ የተሰጠኝን አገልግሎት ለመወጣት ብቁ ያለመወሆኔን እስገነዘብ ድረስ እነዚህ ጥንካሬዬዎቼ ተዳክመዋል።" በማለት ከስምንት ዓመታት በፊት የተረከቡትን የአገልግሎት መንበር ከየካቲት 21 2005 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ጀምሮ  እንደሚለቁና ከዚያም ወጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ የአዲስ ር.ሊ.ጳ. ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በቦታው ለተገኙት ካርዲናሎች በዚህ የአገልግሎት ዘመን ስላደረጉላቸው ትብብር አመስግነው እሳቸውም በበኩላቸው ለነበራቸው ጉድለቶች በሙሉ ይቅርታን ጠይቀዋል።

በመጨረሻም "ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ዋና እረኛዋ ለሆነው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠባቂነት እናማጽናለን፤ እንዲሁም ቅድስት እናቱን ማርያምን ካርዲናል አበውን አዲስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትን ለመምረጥ በሚያደርጉት ሂደት በአሳቢነቷና በጥንቃቄዋ እንድትረዳቸው እንለምን። እኔንም በተመለከተ የእግዚአብሔርን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት በተሰጠ ሕይወት አገለግል ዘንድ ምኞቴ ነው።" በማለት ደምድመዋል።

በቤተ ክርስቲያናችን ሕገ ቀኖና (ላቲናዊው) ቀኖና 332 አንቀጽ 2 ላይ "የሮማው ርእሰ ሊቀ ጳጳሳት የአገልግሎት መንበራቸውን ከለቀቁ ይህ ውሳኔ ብቃት ይኖረው ዘንድ በነጻነት የተደረገና በተገቢ ሁኔታ የተገለጸ መሆን ይገባዋል እንጂ ከሌላ ከማንም ተቀባይነትን (መጽደቅን) አይፈልግም" የሚል መብት አለ። ከ 6 ክፍለ ዘመናት (ከ600 ዓመታት) ወዲህ ይህን መብት ለመጠቀሙ የመጀመሪያው ሲሆኑ ለመንበረ ጴጥሮስ ሢመት ሲመረጡም በጣም እድሜያቸው ከገፉ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አንደኛው ናቸው።

እኛም ከላይ የተገለጸው ጸሎታቸውና ምኞታቸው እውን ይሆን ዘንድ እንጸልይ።