በ"እምነት ክህደት" ሞት ተፈርዶባት የነበረችው ሱዳናዊት ክርስቲያን ሚርያም ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ጋር ተገናኘች

Meriam Popeየክርስትና እምነቷን ትታ ወደ እስልምና እንድትለውጥ ተጠይቃ እምቢ በማለቷ የሞት ፍርድ ተፈርዶባት የነበረችው ሚሪያም ኢብራሂም ትላንትና ሐሙስ ጠዋት ወደ ጣልያን ገብታ በቫቲካን ከር.ሊ.ጳ. ጋር ተገናኝታለች። በዚህም ወቅት ቤተሰቦቻ ማለትም ባለቤቷ ዳንኤል ዋኒ፣ የአንድ ዓመት ተኩል እድሜ ያለው ልጃቸው ማረቲን እና ከሁለት ወር በፊት በእስር ቤት ሳለች የወለደቻት ማያም አብረው ተገኝተዋል።

የሚርያምን ጉዳይ በካርቱም ከማስፈጸም ጀምሮ ወደ ሮም አብሮ በመጓዝ ከር.ሊ.ጳ. ጋርም በተደረገው ግንኙነት የጣልያኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላፖ ፒስቴሊ ይህን ቤተሰብ አጅበዋል። እኚሁ ባለሥልጣን ከዚህ ግንኙነት በኋላ ሲናገሩ የመንግሥታቸው ተልእኮ መሳካቱን ግልጠዋል። በተጨማሪም ምክትል ሚኒስትሩ ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ንግግር የእምነት ክህደት ሕጉ "እንደሚሻሻል ወይም እንደሚሰረዝ" እንደገለጹላቸው ተናግረዋል። {jathumbnail off}

የቫቲካን ማስታወቂያ ክፍል ኀላፊ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ የር.ሊ.ጳ. እና የሚሪያም ቤተሰብ ግንኙነት በጣም የተረጋጋና ደስ የሚል እንደነበረ አውስተው፤ ር.ሊ.ጳ. ላደረገችው "ብርቱ በእምነት የመጽናት ምስክርነት" ሚርያምን ማመስገናቸውን እንዲሁም ሚርያምም በበኩሏ ር.ሊ.ጳጳሳትን ጸሎታቸው ስለፈጠረላት ትልቅ ድጋፍና ብርታት ማመስገኗን ገልጸዋል።

ሚሪያም እናቷ ክርስቲያን ቢሆኑም /ኢትዮጵያዊት/ እንኳ አባቷ ሙስሊም በመሆናቸው ምክንያት በእምነት ክህደት ምክንያት ከዛሬ አራት ወራት በፊት ክስ የተመሠረተባት ሲሆን ከሦስት ዓመታት በፊትም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ክርስቲያን ባል ማግባቷም ይታወቃል። በነበረው የችሎት ሂደትም ሙስሊም ከሆነች በነጻ እንደምትለቀቅ ካልሆነ ግን ግርፋትና የሞት ቅጣት እንደሚፈረድባት ቢነገራትም ለችሎቱ እሷ ከመጀመሪያውኑም ክርስቲያን እንደነበረችና አሁንም ወደ እስልምና እንደማትቀይር አስረግጣ መልስ በመስጠቷ ግርፋቱና የሞት ፍርዱ ጸድቆባት ነገር ግን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር ስለሆነች ሕጻኑን ከወለደች በኋላ ሁለት ዓመት ሲሞላው ቅጣቱ እንዲተገበርባት ፍርድ ቤቱ ወስኖ እንደነበር ይታወሳል። ሕጻኗን በዚያው በእስር ሳለች የተገላገለች ሲሆን ከዚያ ወዲህ በነበረው ሂደት የሞት ፍርዱን መንግሥት አንሥቶላት የነበረ ሲሆን በመ?ጨረሻም በተለያዩ ጣለቃ ገብነቶች ወደ ጣልያን የመጓዟ ሁኔታ ተሳክቷል።

አባ ሎምባርዲ እንደገለጹት ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ከሚርያም ቤተሰብ ጋር የተገናኙት ስለ እምነታቸው ከሚሰቃዩት ሁሉ በተለይም ክርስቲያን በመሆናቸው ለሚሰደዱ ወይም የእምነት ነጻነታቸው ከተገደበባቸው ጋር ያላቸውን "ቅርበት፣ አሳቢነትና ጸሎት" ለማሳየት መሆኑን ገልጸዋል።

ሚሪያም ከሁለት ቀናት የጣልያን ቆይታዋ በኋላ መኖሪያዋ ወደ ሚሆነው አሜሪካ ጉዞዋን ታቀናለች።

ዋነኛ ምንጭ፡- http://www.news.va/en/news/sudanese-christian-meriam-ibrahim-meets-pope-franc

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።