ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ምክንያት የሐዘን መግለጫ መልእክት አስተላለፉ

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 2245

Patriarch Popeበትላንትናው እለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ ጳውሎስ በ76 ዓመት ድሜያቸው በአዲስ አበባ ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን ምክንያት በማድረግ ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የሐዘን መግለጫ ቴሌግራም ለቤተ ፓትሪያርክ ማስተላለፋቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታወቀ።

ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት የሓዘን መግለጫ መልእክት ብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ጳውሎስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል የጋራ ውይይት እንዲደረግ ያበረከቱትን ዓቢይ አስተዋጽዖ ጠቅሰው፣ እ.ኤ.አ. በ 2009 ዓ.ም. ቫቲካን ተካሂዶ በነበረው የመላው አፍሪቃ ብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በእንግድነት ተሳትፈው ያሰሙትን ንግግር በማስታወስ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ምክንያት ላዘኑት ሁሉ ቅርብ በመሆን ነፍሰ ኄር ብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ጳውሎስን እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበላቸው እንደሚጸልዩ መግለጣቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ያመለክታል።

ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ ጳውሎስ የቀብር ሥነ ስርዓትም አዲስ አበባ በሚገኘው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል።

ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ ጳውሎስ እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም. የብጹእ ዮሐንስ ዳግማዊ ሥርዓተ ቀብር ጊዜ በቫቲካን ተገኝተው የተሳተፉ ሲሆን በቅርቡም በአዲስ አበባ የምሥራቃውያት ኦርቶዶክስና ምሥራቃዊ ሥርዓት ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተደረገ ስብሰባን አስተናግደው እንደነበር ይታወሳል።

ምንጭ፡ ራድዮ ቫቲካን , http://www.news.va , ETV