በእጁ ይዞ እንዲመራችሁና እንዲያጅባችሁ ፍቀዱለት

Category: ዜናዎች Written by Super User Hits: 1706

ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው ግንቦት 28 እና 29 2003 ዓ.ም. ባደረጉት የሁለት ቀናት የክሮሺያው ጉብኝታቸው ወቅት በታሪካዊው ጆሲፕ ዠላቺች አደባባይ ከ50 ሺህ በላይ ለሚገምተው ለአገሪቱ ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል መሪ ቃል ሲሰጡ፣ ወጣቱ አታላይ በአቋራጭና በቀላል መንገድ ስኬታማ ለመሆን ትችላለህ በሚለው በእውነት ላይ ካልጸናው ባህል እራሱን እንዲጠብቅና ከዚህ አታላይ ባህል የላቀውን እውነት የእግዚአብሔር ፍቅር ሳይጠራጠር እንዲሻ በማሳሰብ፣  በእጁ ይዞ እንዲመራችሁና በጉዞአችሁ እንደ ጓደኛ የሚሸኛችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር እንዲጓዝ ፍቀዱለት፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ቀርባችሁ እንድታውቁት ያደርጋችኋል እንጂ፣ አያሳፍራችሁም አያታልላችሁም። ለሁሉም መልካም የሆነውን የሚሻ፣ በፍቅሩ በፈጠረን እና

ባዳነን እግዚአብሔር አርአያ እና አምሳያ የተፈጠርን ስለሆንን እውነተኛው ደስታ የሚረጋገጠው ከእርሱ ጋር ከሚመሠረተው ጥብቅ ወዳጅነትና ከእርሱ ጋር በሚደረገው ጉዞ ብቻ ነው። ስለዚህ ዕለታዊው ኑሮ በሚጋርጥብን ችግር እና ድካም ሳንበገር የሃሰት ባህል በመቃወም እውነተኛው የሕይወት ትርጉም እለት በእለት ኑሩ መስክሩም እንዳሉ የቅድስት መንበር መግለጫ ይጠቁማል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያታልል የሚያደናግር ሳይሆን  ከእርሱ ጋር መጓዝ ጽናትን እና መሥዋዕት የሚጠይቅ መሆኑን ሳይደብቅ እውነታውን በግልጽ ነበር ደቀ መዛሙርቱን ያስተማራቸው፡፡ ችግር እና መከራ ቢፈራረቅብንም ይኸንን እውነት መኖር ይበጃል። ስለዚህ የማንነት መለያ የሆነውን ጥልቅ እና ውስጣዊ የአናኗር ዘይቤን ወደ ጎን በማድረግ ክፋትን ብቻ ከሚያጎላውና መሠረተ ቢስ ከሆነው ባህል ተቆጠቡ፣ ተቃውሙትም። ተስፋህን በሚበነው የዓለም ሃብት ላይ ገንባ እያለ የእውነት ምንጭ ውሃ ከሆነው ክርስቶስ ጋር እንዳትጓዙ የሚያሰናክለውን ባህል በመቃወምና በመታቀብ የእግዚአብሔርን ታላቅነት በመረዳት ከእርሱ ጋር መሆንን ትወዱ ዘንድ ፍቃዳችሁ ይሁን ካሉ በኋላ የሰው ልጅ ሕይወት ፍቅር ወደ ሆነው እግዚአብሔር የሚጓዝ ነው በማለት ሁሉንም ወጣት በአባታዊ ፍቅራቸው በመመልከት ሐዋርያዊ ቡራኬ በመስጠት እንደሸኙዋቸው የቅድስት መንበር መግለጫ ይጠቁማል።

ምንጭ፡ ራድዮ ቫቲካን