፪ - "መንግሥትህ ትምጣ"

    ፪ - መንግሥትህ ትምጣ

በአዲስ ኪዳን basileia /ባዚሌያ/ የሚለው ቃል “ንጉሥነት” /የነገር ስም/ መንግሥት /ተጨባጭ ስም/ ወይም “ግዛት” የድርጊት ስም ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ያለችው ከፊታችን ነው፡፡ ሥጋ በሆነው ቃል አማካይነት ወደ እኛ ቀርባለች፤ በመላው ወንጌል ውስጥም ተሰብካለች፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤም ወደ እኛ መጥታለች፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ከጸሎት ሐሙስ ጀምሮ በቅዱስ ቁርባንም አማካይነት በመካከላችን ናት፡፡ መንግሥቱ ክርስቶስ ለአባቱ በሚያስረክባት ጊዜ በክብር ትመጣለች፡፡

እንዲያውም … የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት በእየዕለቱ እንዲመጣ የምንሻውና አመጣጡም በፍጥነት እንዲገለጥልን የምንመኘው ክርስቶስ ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ ትንሣኤያችን ነውና፤ በእርሱ እንነግሣለንና እርሱ የእግዚአብሔር መንግሥትም ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ St.Cyprian, De Dom. Orat. 13 PL 4. 528A.

ይህ “ጌታ ሆይ! ና!” /ማራናታ/ የሚለው ልመና “ና! ጌታ ኢየሱስ” እያሉ የሚጮኹት የመንፈስና የሙሽራይቱ ጥሪ ነው፡፡

ለመንግሥቱ መምጣት እንድንጸልይ የታዘዘ ባይሆንም፣ ተስፋችንን ለመጨበጥ ጉጉት ስላለን፣ ይህንን ጥሪ በሙሉ ፈቃደኛነት ባሰማን ነበር፡፡ የሰማዕታት ነፍሳት ከመሠዊያው በታች ሆነው “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከመቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትበቀልም? እያሉ በታላቅ ድምፅ ይጮኻሉ /ዮሐ. ራዕይ 6፡1ዐ/፡፡ “ፍርዳቸው የሚሰጣቸውማ  በዓለም መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታዬ ሆይ በተቻለ ፍጥነት መንግሥትህ ትምጣ”፡፡ Tertullian, De orat. 5 PL 1. 1159A

በጌታ ጸሎት ውስጥ “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለው ሐሳብ የሚያመለክተው በይበልጥ በክርስቶስ መመለስ የሚመጣውን የእግዚብሔር መንግሥት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ያላትን ተልእበኮ ከማከናወን አያናዳትም፤ ይልቁንም በትጋት እንድተቀጥልበት ይገፋፋታል፡፡ ከጴንጤቆስጤ ጀምሮ የዚያ መንግሥት መምጣት “በዓለም ላይ ሥራውን ላይ የሚፈጽመውና ለእኛም የጸጋና ምላት የሚያስገኘው” የጌታ መንፈስ ሥራ ነው፡፡

“የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ ነው፡፡” ሮሜ 14፡17 የምንኖርበት የዘመን መጨረሻ መንፈስ የሚፈስስበት ዘመን ነው፡፡ ከዕለተ ጴንጤቆስጤ ጀምሮ በ”ሥጋ” እና በመንፈስ መካከል ወሳኝ እየተደረገ ነው፡፡

“መንግስትህ ትምጣ” በማለት በድፍረት መናገር የምንችለው ንጹሕ ነፍስ ብቻ ናት፡፡ ስለዚህም “በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ” በማለት ጳውሎስ የሚያስተላልፈው ትምህርት የሰማ በሥራ፣ በሐሳብና በቃል ራሱን ያነፃ “መንግሥትህ ትምጣ” ሲል እግዚአብሔርን መለመን ይችላል፡፡

ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በሚለግሳቸው እውቀት በመደገፍ በእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋትና እነርሱ በሚሳተፉበት ሕብረተሰብ ባህል ዕድገት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አለባቸው፡፡ ሆኖም ይህ ልዩነት መነጣጠል አይደለም፡፡ ወደ ዘላለም ሕይወት ይገባ ዘንድ ለሰው የቀረበው ጥሪ ፍትሕንና ሰላምን ለማገልገል ከፈጣሪ የተሰጠውን ኃይልና ብልሃት በዚህ ዓለም ላይ በተግባር የማዋል ሃላፊነቱን የሚጫን ሳይሆን ይልቁንም የሚያጠናክር ነው፡፡

ይህ ልመና የሚቀርበውና ተቀባይነት የሚያገኘው ፍሬውንም የሚያፈራው ብፅዕናዎችን በአዲስ ሕይወት በመጠበቅ በማክበር ነው፡፡ በመስዋዕተ ቅዳሴ ህልው በሆነውና በሚሠራው በኢየሱስ ጸሎት ነው፡፡

/የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከቁጥር 2816-2821/