፩ - ስምህ ይቀደስ

    ፩ - “ስምህ ይቀደስ”

እዚህ ላይ “መቀደስ” የሚለው ቃል መወሰድ ያለበት በጥሬ ትርጉሙ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የሚቀድስ፣ ቅዱስ የሚያደርግ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ የቃሉ አጠቃቀም አንድን ነገር እንደ ቅዱስ ለማወቅ፣ በተቀደሰ መንገድ ለመያዝ በመመዘኛነት የተወሰደ ነው፡፡ ስለዚህ በአምልኮ ረገድ ይህ ልመና አንዳንድ ጊዜ እንደምስጋና አንደ ውዳሴ ሆኖ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እዚህ ላይ ይህ ልመና ፍላጐትን በቃላት ስለመግለጽ ከኢየሱስ የተማርነው ነው፤ ልመናው እግዚአብሔርና ሰው የሚሳተፉበት ምኞትና ተስፋ ነው፡፡ በዚህ ለአባታችን በማቅረብ የመጀመሪያው ልመና እኛ ከአምላክነቱ ጠልቅ ምሥጢርና የስብዕናችን መዳን ትዕይንት ውስጥ እንገባለን፡፡ ስሙ ይቀደስ ዘንድ አብን መማጸናችን በዘመን ፍፃሜ ወደሚሆነው ፍቅር የተመላ ቸርነቱ “በክርስቶስ ለማድረግ እንደወደደ” “በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ” ኤፌ 1፡9 ይስበናል፡፡

እግዚአብሔር በእቅዱ ወሳኝ ጊዜአት ውስጥ ስሙን ይገልጣል፡፡ ነገር ግን እርሱ ይህን የሚያደርገው ሥራውን ወደ ፍጻሜ በማድረስ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሥራ ስለእኛና በእኛ ውስጥ እውን የሚሆነው ስሙ በእኛና በእኛም አማካይነት ስሙ ሲቀደስ ብቻ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቅድስና የዘላለማዊ ምስጢሩ የማይደረስበት ውስጠት ነው፡፡ በፍጥረትና በታሪክ የተገለጸውን የዚሁን ውስጠት ክፍል ቅዱስ መጽሐፍ “ክብር” የጌትነቱ የግርማ ሞገሱ ብርሃን ይለዋል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአርአያው በመፍጠር “የክብርና የምስጋና አክሊል ጫነለት፣” ነገር ግን ሰው ኃጢአት በመሥራቱ “የእግዚአብሔር ክብር ጐድሎታል፡፡” ከዚያን ወዲህ ሰውን ወደቀድሞው የፈጣሪ አምሳልነቱ ለመመለስ እግዚአብሔር ስሙን በመግለጥና በመስጠት ቅድስናውን ይገልጣል፡፡ቆላ 3፡1ዐ

እግዚአብሔር ለአብርሃም በሰጠው ተስፋና ከዚያም በገባለት መሐላ ስሙን ሳያሳውቅ ቃል ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ስሙን መግለጽ የሚጀምረው ለሙሴ ሲሆን ከግብጻውያኑ ባዳናቸውም ወቅት “በክብሩ ከፍ ከፍ ብሎአልና፤” በመላው ሕዝብ ፊት እንዲታወቅ ያደርገዋል፡፡ በሲና ተራራ ላይ ከተከናወነው ቃል ኪዳን በኋላ ይህ ሕዝብ “የእርሱ ነው” ስለዚህም “ቅዱስ” ወይም “የተቀደሰ” ሕዝብ መሆን አለበት፤ /ቃሉ በእብራይስጥ ሁለቱንም ያሰማል/ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ስም በዚሁ ሕዝብ ውስጥ ይኖራልና፡፡

ቅዱስ አምላካችው በተደጋጋሚ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ የሚል የተቀደሰ ሕግ የሚሰጣቸው ቢሆንም፣ ስለስሙም ጌታ ትእግስትን ቢያሳይም ሕዝቡ ከእሥራኤል ቅዱስ ፊቱን በመመለስ በአሕዛብ መካከል ስሙን አርክሷል” በዚህም ምክንያት የብሉይ ኪዳን ጻድቃን ከስደት የተመለሱ ድኾችና ነቢያት በስሙ ፍቅር የተቃጠሉ ነበሩ፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ እግዚአብሔር ስም በሥጋ፣ በአዳኝነቱ በእርሱነቱ መገለጥ፣ በቃሉና በመሥዋዕቱ በኢየሱስ የተገለጠልን፤ ተሰጠንም፤ እርሱ ይህን ስም የገለጠው፣ በሥራዎቹ፣ በቃላቱና በመስዋዕቱ ነው፡፡ የክህነታዊው ጸሎቱ እምብርትም “ቅዱስ አባት … እነርሱን ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ የሚለው ቃሉ ነው፡፡” ዮሐ 17፡11፤19 ምክንያቱም እርሱ ስሙን “ይቀድሳል”፤ የአብንም ስም ይገልጥልናል፡፡ በክርስቶስ ፋሲካ ማብቂያ ላይ አብ “ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ይሰጠዋል፤ “ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው፡፡” ፊሊሞና 2፡9-11

“በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ በጥምቀት ውሃ ታጥበናል… ተቀድሰናል… ጸድቀናልም፡፡” 1ቆሮ 6፡11 አባታችን በሕይወት ዘመናችን ሁሉ ወደ ቅድስና ይጠራናል፡፡ እርሱ “ለእኛ ከእግዚአብሔር የተገኘ ጥበብ፣ እና … ቅድስና በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ለሆነው ሕይወታችን መገኛ” 1ቆሮ 1፡3ዐ፤ 1ተሰ 4፡7 ነውና ክብሩና ሕይወታችን በእኛ ውስጥና በእኛም አማካይነት የሚሆነው የሰሙ ክብር ይወሰናል፡፡ የመጀመሪያው ልመናችንም አስፈላጊነት ይህ ነው፡፡

“እርሱ ብቻ ቀዳሽ ሆኖ ሳለ፣ እርሱን ሊቀድሰው የሚችል ማነው? ነገር ግን እርሱ ራሱን “እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና … ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ” ሌዋ 2ዐ፡26 እንዳለው እና በምስጢረ ጥምቀት የተቀደስን መሆን የጀመርነውን በጽናት እንድንቀጥልበት እንሻለን፤ እንጠይቃለንም፡፡ ይህንንም በየዕለቱ እንለምናለን በየዕለቱ የምንወድቀው እና ያለማቋረጥ በመቀደስ ኃጢአቶቻችንን ለማንጻት ዕለት በዕለት መቀደስ ያሻናልና … ይህ መቀደስ በውስጣችን ይዘልቅም ዘንድ እንጸልያለን፡፡

በአሕዛብ መሐከል የእግዚአብሔርን ስም መቀደስ የማይነጣጠል ሁኔታ፤ በሕይወታችንና በጸሎታችን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

በቅድስናው ፍጥረትን ሁሉ የሚያድን የሚቀድስ ስሙን እግዚአብሔር ይቀድስ ዘንድ እንለምነዋለራ፡፡ ለጠፋው ዓለም ምሕረትን የሚያደርግ ይህ ስም ነው፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ስም በእኛ ውስጥ በድርጊቶቻችን እንዲቀደስ እንለምናለን፡፡ ምክንያቱም እኛ መልካም ሕይወት ስንኖር የእግዚአብሔር ስም ይባረካል፤ በክፋት ስንኖር ግን ስሙ ይሰደባል፡፡ ሐዋርያው እንደሚለው “በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል፡፡” ስለዚህም የአምላካችን ስም ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እኛም ደግሞ በነፍሳችን ቅድስናን እናገኝ ዘንድ እንለምናለን፡፡

“ስምህ ይቀደስ” ስንል በእርሱ ውስጥ በሆንን በእኛ ዘንድ እንዲቀደስ እንለምናለን እንደዚሁም ገና የእግዚአብሔር ጸጋ ለሚጠባበቃቸው ሌሎች ሰዎችም እንለምናለን፡፡ ይህንንም የምናደርገው ለሁሉም፣ ለጠላቶቻችንም እንኳን ሳይቀር እንድንጸልይ የሚጠይቀንን ትእዛዝ ለመፈጸም ነው፡፡ “ስምህ በእኛ ውስጥ ይቀደስ” የማንለው፡፡ በሰዎች ሁሉ ዘንድ እንደዚሁ እንዲሆን እንለምናለነና፡፡”

ህ ልመና ሌሎቹን ሁሉ ያጠቃልላላ፡፡ እደተከታዮቹ ስድስት ልመናዎች በክርስቶስ ጸሎት ፍጻሜን ያገኛል፡፡ በኢየሱስ ስም ከተጸለየ ለአባታችን የሚቀርብ ጸሎት የእኛ ጸሎት ነው፡፡ ኢየሱስ በክህነታዊ ጸሎቱ “ቅዱስ አባት ሆይ፣ እነዚህን የሰጠኸኝን በስምህ ጠብቃቸው” ዮሐ 17፡11 ሲል ይለምናል፡፡

/የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ከቁጥር 2807-2815/