እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

“እኔ ያመንኩትን አውቃለሁ” 2ጢሞ. 1፡2

Emnet 1ጥቅምት ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም. ቅዱስ አባታችን ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ ፲፮ኛው ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ በእምነታችን ላይ በተለየ ሁኔታ በማስተንተን አናኗራችንን እንድንመዝንና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም የመላው ዓለም ታሪክና የግል ሕይወታችን ማእከል መሆኑን ዳግም አሜን እንድንል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት አማኞችን ሁሉ ጋብዘዋል። እግዚአብሔርን ለዚህ ጥሪው እያመሰገንን ከለብ ያለና አምላኩን ከረሳ ሕይወት እየራቅን ዘወትር በእርሱ ወደሚመካ ግለሰብነት እናድግ ዘንድ በመለመን ስለእምነት አንድምታና ጠቃሚነት የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

እምነት፡- ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ምላሽ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ፣ የማይታየው እግዚአብሔር ከፍቅሩ ምልአት የተነሣ ሰዎችን ሁሉ እንደ ባልንጀሮቹ ሊያናግራቸው፣ ሊጠራቸውና ወዳጆቹ ሊያደርጋቸው በመካከላቸው ይመላለሳል፡፡ ለዚህ አምላካዊ መገለጥ የሰው ተገቢው ምላሽ እምነት ነው፡፡

በእምነት ሰው ልቡናውንና ፍቃዱን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ያስገዛል፡፡ በሙሉ እርሱነቱ ለገላጩ ለእግዚአብሔር እሺታውን ያሰማል፡፡ የግልጸት ደራሲ ለሆነው ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን ይህንን ሰብአዊ ምላሽ መጽሐፍ ቅዱስ “በእምነት ታዛዥነት” ይለዋል፡፡

አምናለሁ

፩- በእምነት መታዘዝ

መታዘዝ ማለት /በላቲንኛ/ መስማት ወይም ማዳመጥ ማለት ሲሆን በእምነት ታዛዥነት ማለት ለተደመጠው ቃል ራስን በሙሉ ፈቃደኝነት ማስገዛት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም እውነኛነቱ ራሱ እውነት በሆነው በእግዚአብሔር ተረጋግጧል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አብርሃም ለዚህ ዓይነት ታዛዥነት አርአያ ነው፡፡ ድንግል ማርያምም ለዚህ ታዛዥነት ፍጽምት መገለጫ ናት፡፡

ዕብራውያን ስለ እስራኤል ቅድመ አያቶች በሚያወሳው ታላቅ መወድስ ውስጥ ለአብርሃም እምነት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፤ “አብርሃም በርስትነት ወደሚረከበው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ትእዛዙን ተቀበለ፤ ምንም እንኳን ወዴት እንደሚሔድ ባያውቅም፣ ጉዞውን ቀጠለ፡፡” ዕብ. 11፡8 እንግዳና መጻተኛ ሆኖ በተስፋ በእምነት ኖረ፡፡ የተስፋ ፍሬ የሆነውን ወንድ ልጅ ሣራ በእምነት ጸነሰች፡፡ እናም በእምነት አብርሃም አንድያ ልጁን ለመሥዋዕት አቀረበ፡፡

ስለዚህ አብርሃም ስለ እምነት በዕብራውያን ምዕራፍ 11፡1 ያሰፈረውን ፍች ያሟላል፡፡ “እምነት ማለት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፡ የማናያቸውን ነገሮች ስለ መኖራቸው የሚያስረዳን ነው፡፡”ዕብ.11፡1 “አብርሃም በእግዚአብሔር ስላመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት፡፡” ሮሜ 4፡3 እምነት ብርቱ ስለነበር አብርሃም “የሚያምኑ ሁሉ አባት” ሮሜ 4፡11 ሆነ፡፡

ብሉይ ኪዳን ለዚህ እምነት ያሰፈረው ምስክርነት እጅግ ሰፊ ነው፡፡ በእብራውያን “መለኮታዊ ተቀባይነትን ስላገኙ” አበው የእምነት አርአያነት መወድስ ቀርቧል፡፡ “የእምነታችን ቀያሽና ፈጻሚ” በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የማመንን ጸጋ እንድንጐናጸፍ “እግዚአብሔር የተሻለ ነገር አቅዶልናል፡፡” ዕብ. 11፡4ዐ፤ 12፡2

ማርያም  - “ያመነችው እርሷ ብፅዕት ናት”

ድንግል ማርያም እጅግ ፍጹም የሆነ የእምነት ታዛዥነት ማሳያ ናት፡፡ መልአኩ ገብርኤለ ያመጣላትን መሥራችና ተስፋ ማርያም በእምነት ተቀብላለች፤ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” ብላ በማመን እሽታዋን ገለጸች፡፡ “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፤ አንተ እንዳልክ ይሁንልኝ፡፡” ሉቃ. 1፡37-38 ኤልሳቤጥም ስትቀበላት “እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን በማመንሽ የተባረክሽ ነሽ” ሉቃ. 1፡45 ተብላለች፡፡ ስለዚህ በእምነቷ ነው ትውልዶች ሁሉ ማርያምን ብፅዕት የሚልዋት፡፡

በሕይወትዋ ሙሉና ልጅዋ  ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት እስከ ደረሰባት እስከ መጨረሻው ሰቄቃ  ድረስ፣ የማርያም እምነት ጨርሶ አልወላወለም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል መፈጸም የነበራት እምነት ምን ጊዜም የጸና ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን የማርያምን የላቀ እምነት ታወድሳለች፡፡

፪- “እኔ ያመንኩትን አውቃለሁ” 2ጢሞ. 1፡2

በእግዚአብሔር ብቻ ማመን

እምነት በሁሉም በላይ ግላዊ የእግዚአብሔር ተከታይነት ነው እንደዚሁም ሁሉ ከዚህ ባልተለየ መልኩ፣ እግዚአብሔር ለገለጠው እውነት ሁሉ የሚሰጥ ነጻ ስምምነት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ግላዊ ተከታይ እንደመሆናችን ለእሱነቱ መስማማታችንን እንደ መግለጣችን ክርስቲያናዊ እምነት በማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ላይ ካለን እምነት ይለያል፡፡ ራሳችንን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ማስረከብና የሚለውን ሁሉ በሙሉ ማመን ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ በፍጡር ላይ የዚህ ዓይነት እምነት መጣል ከንቱና ስሕተት ይሆናል፡፡

በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን

ለአንድ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ማመን፣ በአንድ እርሱ በላከው እግዚአብሔር እንድንሰማው በሚመክረን “አብ እጅግ በተደሰተበት” “በተወዳጁ ልጅ” ከማመን ውጭ ሊሆንም አይችልም፡፡ ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሎአል፡፡ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ፡፡”ዮሐ 14፡1 በእየሱስ ክርስቶስ ማመን እንችላለን፤ ምክንያቱም እሱ ራሱ እግዚአብሔር ሥጋ የሆነ ቃል ነውና፡፡ “እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለው አንድያ ልጁ ብቻ ገልጦታልና፡፡” ዮሐ. 1፡18 “አብን ስለአየው” እርሱን የሚያውቀውና ሊገልጸው የሚችለው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡

በመንፈስ ቅዱስ ማመን

ከመንፈሱ ሳይካፈሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን አይቻልም፡፡ የኢየሱስን ማንነት ለሰዎች የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ምክንያቱም “ማንኛውንም ነገር፣ የእግዚአብሔርን ጥልቀት እንኳን በሚመረምረው” በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር “ማንም ኢየሱስ ጌታ ነው ማለት አይችልም፡፡ …” 1ቆሮ 12፡3 እንዲሁም ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር የእግዚአብሔር አሳብ የሚያውቅ ሌላ ማንም የለም፡፡” 1ቆሮ. 2፡1ዐ-11 እግዚአብሔር ብቻ ነው እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ የሚያውቀው፤ በመንፈስ ቅዱስ የምናምነው፤ እሱ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአንድ እግዚአብሔር፣ በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ያላትን እምነት ከማወጅ ፈጽማ አትታቀብም፡፡

፫- የእምነት ባሕርያት

እምነት ጸጋ ነው

ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ፣ ክርስቶስ ነው ብሎ በመሰከረ ጊዜ ኢየሱስ ይህንን “የገለጸልህ በሰማይ ያለው አባቴ ነው እንጂ ሥጋና ደም አይደለም፡፡” ማቴ.16፡17 እምነት ከእርሱ መለኮታዊ ቸርነት የሚፈስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ “ይህ እምነት ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት፣ ሰው የሚቀሰቅሰውንና የሚረዳውን የእግዚአብሔር ጸጋ ማግኘት አለበት፤ ልቦናውን አነቃቅቶ ወደ እግዚአብሔር የሚመልሰውን፣ ዓይነ ሕሊናውን ከፍቶ እውነትን በቀላሉ እንዲቀበልና እንዲያምን የሚያስችለውን የመንፈስ ቅዱስን ውስጣዊ እርዳታ ማግኘት አለበት፡፡”

እምነት ሰብአዊ ድርጊት ነው

ማመን ሊኖር የሚችለው በጸጋና በመንፈስ ቅዱስ ውስጣዊ እርዳታ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ማመን በትክክልና ሰብአዊ ድርጊት መሆኑም እውተኛ ነገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ማመንና የገለጣቸውን እውነቶች አጥብቆ መያዝ ሌሎች ሰዎች ስለ እራሳቸውና ስለ ዓላማቸው የሚነግሩንን ወይም የሕይወትን ሱታፌ እርስ በርስ ለመጋራት /ለምሳሌ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ትዳር ሲመሠርቱ/ የሚገቡትን ቃል ማመን ክብራችንን አይነካም፡፡ እንዲህ ከሆነ “ሁሉን ለሚገልጥ ለእግዚአብሔር አዕምሯችንንና ፈቃዳችንን ሙሉ ለሙሉ ማስገዛት” እና ጸጋውን መካፈል እንዳውም ከዚያ እንኳ ባነሰ ደረጃ ክብራችንን የሚቃረን አይሆንም፡፡

በእምነት ሰብአዊ አዕምሮና ፈቃድ ከመለኮታዊ ጸጋ ጋር ይተባበራሉ፤ “ማመን በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት በተቀሰቀሰ ፈቃድ ትእዛዝ አዕምሮ የሚከውነው ለመለኮታዊ እውነት የመታዘዝ ድርጊት ነው፡፡”

እምነትና እውቀት

እንድናምን የሚገፋፋን የተገለጡልን እውነቶች ትክክልና ተጨባጭ መስለው ለተፈጥሮአዊ ሕሊናችን ጎልተው በመታየታቸው አይደለም፡፡ “የምናምነው እነርሱን በገለጣቸው፣ ሊያሳስትም ሊሳሳትም በማይችለው በራሱ በእግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡” “የእምነት ተገዥነታችን ትክክለኛ እንዲሆን እግዚአብሔር የእርሱ መገለጥ ውጫዊ ማረጋገጫዎች ከውስጣዊ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ጋር እንዲገጥሙ ፈቀደ፡፡” ስለዚህም የክርስቶስን የቅዱሳን ተአምራት፣ ትንቢቶች፣ የቤተ ክርስቲያን እድገትና ቅድስና፣ እንዲሁም ፍሬያማነትዋና ጽናትዋ “ለሁሉም ግንዛቤ እንዲስማሙ የተደረጉ የመለኮታዊ መገለጥ እርግጠኛ ምልክቶች ናቸው፡፡” እነዚህ ምልክቶችም እምነት በምንም አኳኋን ጭፍን የአእምሮ ግፊት አለመሆኑን የሚያሳዩን የመታመን ምክንያቶች ናቸው፡፡

እምነት እርግጠኛ ነው፡፡ ሊዋሽ በማይችለው በእግዚአብሔር በራሱ ቃል ላይ የተመሠረተ ነውና እምነት ከሁሉም ሰብአዊ እውቅት የበለጠ እርግጠኛ ነው፡፡ የተገለጡ እውነቶች ለሰብአዊው አስተሳሰብና ልምድ በእርግጥም ስውር ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን መለኮታዊ ብርሃን የሚሰጠው እርግጠኛነት ባሕርያዊ የማሰብ ኃይል ከሚፈነጥቀው ብርሃን የሚገኘው እርግጠኛነት የበለጠ ነው፡፡ ዐሥር ሺህ ችግሮች አንድ ጥርጣሬ አይሆኑም፡፡

እምነት እውቀትን ይሻል፡፡ አማኝ ያመነበትን እርሱም የበለጠ ለማወቅና እርሱ የገለጠውንም በተሻለ ለማወቅ መፈለጉ የእምነት አካል ነው፤ የበለጠ ጥልቅ የሆነ እውቀት ደግሞ በተራው በፍቅር የሚቀጣጠል የበለጠ እምነትን ይጠይቃል፡፡ የእምነትን ጸጋ የመገለጥን ቁም ነገሮች የሚያስደስት ሁናቴ ለማስጨበጥ፤ ማለትም የእግዚአብሔርን አጠቃላይ ዕቅዱና የእምነት ምስጢራት እርስ በርሳቸውና፣ የተገለጠውን ምስጢር መሠረት ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በውል ለመገንዘብ “ዓይነ ልቡናችሁ” ኤፌ 1፡18 ይከፍታል፡፡

መገለጥ በጥልቀት ግልጽ ይሆን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ያለማቋረጥ እምነትን ፍጹም ያደርጋል በቅዱስ አጉስጢኖስ አባባል “አውቅ ዘንድ አምናለሁ፤ በበለጠ ለማመን ደግሞ አውቃለሁ”

እምነትና ሳይንስ፡- “ምንም እንኳን እምነት ከማሰብ ኃይል በላይ” ቢሆንም፣ በእምነትና በማሰብ ኃይል መሐል መሠረታዊ ልዩነት ሊኖር አይችልም፡፡ ምስጢራትን የሚገልጠውና እምነትን የሚያሠርፀው ያው አምላክ እስከሆነ ድረስ ለሰብአዊ አእምሮ የማሰብን ብርሃን የለገሰ እግዚአብሔር ራሱን ሊክድ አይችልም፤ እውነትም እውነትን ሊቃረን አይችልም፡፡” “ስለዚህም በሁሉም በዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ሥርዓትን የተከተለ ምርምር፣ በትክክለኛ ሳይንሳዊ መንገድ እስከ ተካሄደና ምግባራዊ ሕግን እስካልጣሰ ድርስ ከእምነት ጋር ጨርሶ ሊጋጭ አይችልም፤ ዓለማዊና እምነታዊ ጉዳዮች የመጡት ከዚያም አንድ አምላክ ነውና፡፡” ትሑትና ታታሪ የሆነ የተፈጥሮ ምስጢር ተመራማሪ፣ ከራሱ ፍላጐት ባሻገር፣ በእግዚአብሔር እየተመራ ነው፤ ነገሮችን የሆኑትን አድርጐ የፈጠራቸው፣ የሁሉም ጠባቂ እግዚአብሔር ነውና ፡፡

የእምነት ነፃነት

ሰብአዊ እንዲሆን፣ “በእምነት አማካይነት ሰው ለእግዚአብሔር የሚሰጠው ምላሽ ነጻ መሆን አለበት፣… ስለዚህም ማንም ቢሆን ከፈቃዱ ውጭ እምነት እንዲቀበል መገደድ የለበትም፡፡ እምነት በተፈጥሮው ነጻ ድርጊት ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሰዎችን በመንፈስና በእውነት እንዲያገለግሉት ይጠራሉ፡፡ ስለዚህም በኅሊና ከእርሱ ጋር ይተሳሰራሉ፤  ነገር ግን አይገደድም ይህ ሐቅ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም መግለጫ አግኝቶአል፡፡” በእርግጥ አላስገደዳቸውም፡፡ “ምክንያቱም ስለ እውነት መሰከረ እንጂ ተቃውመው በተናገሩት ላይ በኃይል ለመጫን አልፈለገም፡፡ መንግሥቱ… የምትሰፋው ሰዎችን ወደ ራሱ ለመሳብ ሲል በመልዕልተ መስቀል በተሠዋው በክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡”

የእምነት አስፈላጊነት

በኢየሱስ ክርስቶስና ለድኅነታችን እራሱን በላከው ማመን ድኅነታችንን ለመቀዳጀት አስፈላጊ ነው፡፡ “ያለ እምነት እግዚአብሔር ማስደሰትና የልጆቹን ኅብረት ማግኘት አይቻልም፤ ስለዚህ ያ እምነት ማንም ጽድቅን ከቶ አግኝቶ አያውቅም፤ “እስከ መጨረሻ ከሚጸናው በቀርም” ማንም ዘላለማዊ ሕይወትን አይወርስም፡፡

በእምነት መጽናት

እምነት እግዚአብሔር ለሰው ዘር የለገሰው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ ስጦታ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ እንዳመለከተው ይህንን ዋጋና የማይገመት ስጦታ ልናጣው እንችላለን፡፡ “ትንቢቱን በመከተል መልካም ጦርነትን ተዋጋ፤ እምነትና መልካም ኅሊና ይኑርህ፤ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፡፡” ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ተናግሯል፡፡ በእምነት ለመኖር፣ ለማደግና እስከ መጨረሻው ጸንቶ ለመቆየት በእግዚአብሔር ቃል ልናበለጽገው ይገባል፤ እምነት እንዲጨምርልን ጌታችንን መማፀን አለብን፤ ይህንን እምነት “በፍቅር አማካይነት የሚሠራ”፣ በተስፋ የተሞላና በቤተ ክርስቲያን እምነት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል፡፡

 እምነት - የዘላለማዊ ሕይወት መጀመሪያ

እምነት የዚህ ምድራዊ ጉዟችን ግብ የሆነውን የቅድስና ብርሃን ራዕይ እንድናጣጥም ያደርገናል፡፡ በዚያን  ጊዜ እግዚአብሔርን እንዳለ “በግልጥ እናያለን” ሰለዚህ እምነት የዘላለማዊ ሕይወት መጀመያ ናት፡፡

ልክ በመስታወት ውስጥ ምስላችንን እንደምናስተውል ሁሉ፣ አሁን ስንኳ የእምነትን በረከቶች ስናሰላስል እምነታችን አንድ ቀን ያስገኝልናል ብለን የምናስባቸውን ድንቅ ነገሮች ቀድመን የጨበጥን ያህን ይሰማናል፡፡

ነገር ግን አሁን “የምንራመደው በእምነት እንጂ በማየት አይደለም፤” 2ቆሮ 5፡7 እግዚአብሔርን የምናየው “በመስተዋት እንደምናየው ዓይነት ድንግዝግዝ ባለ ሁኔታና በከፊል ብቻ” ነው 1ቆሮ 13፡12 ምንም እንኳ ከሚያምነው ከእርሱ ግንዛቤን የሚያገኝ ቢሆንም፣ እምነት ብዙውን ጊዜ በጨለማ ውስጥ የሚኖር ስለሆነ ሊፈትን ይችላል፡፡ የምንኖርበት ዓለም በእምነት ተስፋ ከተገባልን ዓለም በጣም የራቀ መስሎ ብዙውን ጊዜ ይሰማናል፡፡ የክፋትና ሥቃይ፣ የግፍና ሞት ልምዶቻችን መልካሙን ዜና የሚቃረኑ ይመስላሉ፣ እምነታችንን ሊያናጉና ሊፈታተኑም ይችላሉ፡፡

በዚህም ጊዜም ወደ እምነት ምስክሮች ፊታችንን መመለስ አለብን፡፡ “ተስፋው በጨለመበት ወቅት… በተስፋ ወዳመነው፤ ሮሜ 4፡18  ወደ አብርሃም “በእምነት ጉዞዋ ላይ” የልጅዋን ሥቃይና ሞት ጨለማ በመጋራትዋ ወደ “እምነት ምሽግ” ወደገባችው ድንግል ማርያምና ወደ መሰል ሌሎችም መዞር አለብን፤ “እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ካሉልን፤ እኛ ደግሞ ሸክምንና በኛ ላይ የተጣበቀውን ኃጢአት ሁሉ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት በመፅናት እንሩጥ፡፡ የምንሮጠውም የእምነታችን ራስና ፈጻሚ የሆነው ኢየሱስን በመመልከት ነው” ዕብ 12፡1-2

ምንጭ፡- አዲሱ የካቶሊክ ቤ/ያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ.145-165

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት