የመላእክት ህላዌ

1. መላእክት

የመላእክት ህላዌ የእምነት ሐቅ

የመንፈሳዊያን፣ መጽሐፍ ቅድስ ብዙውን ጊዜ "መላእክት" ሲል የሚጠራቸው ፈቂቃን ፍጡራን ሕላዌ የእምነት ሐቅ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት እንደማያሻማው የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ግልጽ ነው፡፡

እነርሱ ማን ናቸው?

ቅዱስ አውጉስጢኖስ ስለነርሱ ሲናገር "መልአክ" የተግባራቸው እንጂ የባህርያቸው ስያሜ አይደለም፡፡ የባህሪያቸውን ስም ከፈለጋችሁ "መንፈስ" ነው፤ የተግባራቸውን ስም ከፈለጋችሁ "መልአክ" ነው፡፡ ከማንነታቸው "መንፈስ"፣ ከተግባራቸው "መልአክ" የሚለውን ስም አግኝተዋል ይላል፡፡ መላእክት በሁለንተናቸው የእግዚአብሔር መልዕክተኞች ናቸው፡፡ "በሰማይ የሚኖረውን አባቴን ፊት ሁል ጊዜ ስለሚያዩ" "ቃሉን የሚፈጽሙ፣ የቃሉን ጽምፅ የሚሰሙ ኃያላን" ናቸው፡፡ ማቴ 18፡1ዐ መዝ. 1ዐ3፡2ዐ

ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ ፍጥረታት እንደ መሆናቸው መላእክት ዕውቀትና ፈቃድ አላቸው፡፡ የክብራቸው ሞገስ እንደሚመሰክረው፣ ከሚታዩ ፍጥረታት ሁሉ በፍጽምና የሚልቁ አካላዊና ሞት የሌለባቸው ፍጥረታት ናቸው፡፡

ክርስቶስ "ከመላእክቱ ሁሉ ጋር"

ክርስቶስ የመላእክት ዓለም ማዕከል ነው፡፡ መላእክቱም የእርሱ ናቸው፡፡ "የሰው ልጅ በመላእክቱ ሁሉ ታጅቦ በክብር ሲመጣ ..." ማቴ 25፡31 የእርሱ ናቸው ምክንያቱም በእርሱ ለእርሱ የተፈጠሩ ናቸውና፡፡ "የሰማይና በምድር ያሉት፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት የሆኑ ወይም ጌትነት፣ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው፡፡" ቆላ 1፡16 የማዳን ዕቅዱ መልክተኞች ስላደረጋቸውም ይበልጥ የእርሱ ናቸው፡፡ "ታዲያ መላእክት የሚድኑትን ለማገልገል የሚላኩ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሆኑ መንፈሶች አይደሉምን? ዕብ 1፡14

መላእክት ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮና በድኅነት ታሪክ ዘመን በሙሉ ነበሩ፤ ይህን ድኅነት ከቅርብ ወይም ከሩቅ አያበሠሩ የመለኮታዊውን ዕቅድ ፍጻሜ እያገለገሉ ኖረዋል፤ ጥቂት ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፣ ምድራዊውን ገነት ዘግተዋል፤ ሎጥን ጠብቀዋል፤ ሐጋርንና ልጅዋን አትርፈዋል፤ የአብርሃምን እጅ አቆይተዋል፤ በአገልግሎታቸው የእግዚአብሔርን ሕግ አስተምረዋል፤ ሕዝበ እግዚአብሔርን መርተዋል፤ የብዙዎችን መወለድና መጠራትን አብሥረዋል፤ ነቢያትን ረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ገብርኤል /የመንገድ ጠራጊውን/ የዮሐንስ መጥምቁንና የራሱን የኢየሱስን ልደት አበሰረ፡፡

ከትስብእት እስከ ዕርገት፣ ሥጋ የሆነውን ቃለ ሕይወት በመላእክት ስግደትና አገልግሎት የታጀበ ነው፡፡ እግዚአብሔር "የበኩር ልጁን ልኮ ወደ አለም ሲያስገባ፣ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት ይላል፡፡ "በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን" ሉቃ 2፡14 እያሉ በክርስቶስ ልደት ያዜሙት መዝሙር እስከ ዛሬ በቤተክርስቲያን ውዳሴ ማስተጋባቱን አላቋረጠም፡፡ ኢየሱስን በሕፃንነቱ ጠብቀውታል፤ በምድረ በዳ አገልግለውታል፤ ከጠላቶቹ እጆች ሊያተርፉት ሲችሉ፣ በእሥራኤል እንደደረሰው ሁሉ በአትክልቱ ውስጥ በመከራው ጊዜ አጽናንተውታል፡፡ እንደገና የክርስቶስን ትስብእትና ትንሣኤ መልካም ዜና በማብሰር "ወንጌልን ያስተማሩ" መላእክት ናቸው፡፡ በሚያበሥሩት ክርስቶስ ደግሞ በሚመጣበት እለት፣ በፍርዱ ላይ ሊያገለግሉት ይገኛሉ፡፡

መላእክት በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውሰጥ

እስከዚያው ድረስ መላው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከመላእክት ምስጢራዊና ኃያል እርዳታ ትጠቀማለች፡፡ በሥርዓተ አምልኮዋ ቤተ ክርስቲያን ከመላእክት ጋር በመተባበር ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ በማለት /ሦስት ጊዜ/ ለእግዚአብሔር ትሰግዳለች፡፡ እርዳታቸውንም /በላቲን ሥርዓት "ሁሉን የምትችል አምላክ ሆይ መልአክህ ... እንጸልያለን"፤ በቀብር ሥርዓተ አምልኮ "መላእክት ወደ ገነት ይመሩህ ዘንድ ..." እያለች ትለምናለች፡፡ በተጨማሪም በሲዛንቲናዊ ሥርዓተ አምልኮ በ "ኪሩቤላዊ ውዳሴ" የአንዳንድ መላእክትን፣ በይበልጥም /የቅዱስ ሚካኤልን፣ የቅዱስ ገብርኤልን፣ የቅዱስ ሩፋኤልን የጠባቂ መላእክትን/ መታሰቢያ ታከብራለች፡፡

የሰው ልጅ ሕይወት ከልደት እስከ ሞት በእነርሱ የቅርብ እንክብካቤና አማላጅነት የተከበበ ነው፡፡ "በእያንዳንዱ አማኝ ጐን አንድ መልአክ እንደ ጠባቂና እረኛ ይቆማል" በዚህች ምድር ላይም ክርስተያናዊ ሕይወት በአምላክ አንድ የሆኑትን የመላእክትና የሰው የተቀደሰ ወዳጅነትን ይካፈላል፡፡