6 - አታመንዝር

ስድስተኛይቱ ትእዛዝ

“አታመንዝር” ዘጸ. 2ዐ፡14፤ ዘዳ. 5፡18

“አታመንዝር” እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም፣ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሯል፡፡ ማቴ. 5፡ 27-28

“ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠረው …”

“እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በራሱም የአንድነትና የፍቅር ምስጢር ሆኖ ይኖራል፡፡ እግዚአብሔር በአምሳያው የሰውን ዘር ሲፈጥር … በወንድና በሴት ባሕርይ ላይ ጥሪን ቀረጸ፤ በዚያም መሠረት የፍቅርና፣ የአንድነት አቅምና ኃላፊነት ሰጣቸው፡፡”

“እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረ… ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፡፡” ዘፍ.1፡27 “ብዙ ተባዙ ምድርን ሙሏት” ዘፍ. 1፡28 ብሎ ባረካቸው፡፡ “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፣ ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው፤ ባረካቸው፣ ስማቸውንም በፈጠረበት ቀን አዳም ብሎ ጠራቸው፡፡”

ጾታዊ ባህርይ በሰው አጠቃላይ ገጽታ፤ በሰው አካልና ነፍስ ባለው አንድነት ላይ በሁሉ አንፃር ከፍ ያለ ተጽእኖ አለው፡፡ ጾታዊ ባህርይ በተለይ የፍቅር ስሜትን፣ የመዋደድና የመውለድ ችሎታን፣ እንደሁም በጠቅላላ ሲታይ ደግሞ ከሌሎች ጋር ትስስር የመፍጠርን ተሰጥዎ ያመለክታል፡፡

ወንድም ይሁን ሴት ማንኛውም ሰው ፆታዊ ማንነቱን ማወቅና መቀበል አለበት፡፡ አካላዊ፣ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ልዩነት እንዲሁም መደጋገፍ የተቃኙት የጋብቻን ስኬታማነት እና የቤተሰብን ሕይወት ማበብ እንዲያስገኙ ነው፡፡ የባልና የሚስት እንደሁም የሕብረተሰብ ስምምነት (መግባባት) በከፊል የሚመሠረተው የሁለቱ ጾታዎች መደጋገፍ፣ ፍላጐቶችና መተባበር በሚተገበሩባቸው ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡

“እግዚአብሔር ሰዎችን ወንድና ሴት አድርጐ ስለፈጠራቸው፤ ለመንድና ለሴት እኩል የሆነ ግላዊ ክብርን ይሰጣል፡፡” “ወንድና ሴት በእግዚአብሔር መልክና አምሳያ የተፈጠሩ ስለሆኑ ወንድ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሴት ከወንድ ጋር እኩል የሆነች ሰው ናት፡፡”

ዓይነቱ አንድ ባይሆንም እኩል የሆነ ሰብአዊ ክብር ያላቸው ሁለቱም ጾታዎች የእግዚአብሔር ኃይልና ርኀራኄ አምሳሎች ናቸው፡፡ በጋብቻ አማካይነት የሚፈጸመው የወንድና የሴት አንድነት የፈጣሪ ልግስናና ፍሬያማነት በሥጋ መፈጸም ነው፡፡ “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡”ዘፍ. 2፡24 የሰው ትውልዶች ሁሉ ምንጭም ይኸው አንድነት ነው፡፡

“ኢየሱስ የመጣው ፍጥረትን ወደ መጀመሪያ ንጽሕናው ለመመለስ ነው፡፡ በተራራው ስብከት ላይ “አታመንዝር” እንደተባለ ሰምታችኋል፡፡ እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሯል” ማቴ. 5፡ 27-28 ሲል የእግዚብሔርን ሕግ በሚገባ ይተረጉመዋል፡፡ “እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው ሊለያየው አይችልም፡፡” ማቴ.19፡6 ስድስተኛው ትእዛዝ የሰውን ፆታዊ ባህርይ በሙሉ እንደሚያካት በቤተ ክርስቲያን ትውፋት ዘንድ በሚገባ ግንዛቤ ተወስዶበታል፡፡