የጸሎት ውጊያ

የጸሎት ውጊያ

ጸሎት የጸጋ ስጦታ ከመሆኑም ባሻገር በእኛ በኩል የሚሰጥ ቆራጥ ምላሸ ነው፡፡ ጸሎት ሁል ጊዜ ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ከክርስቶስ በፊት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩት ታላላቅ የጸሎት ሰዎች እንዲሁም የአምላክ እናትና ቅዱሳን ራሱ ክርስቶስም ጸሎት ውጊያ መሆኑን ያስተምሩናል፡፡ ውጊያው ከማን ጋር ነው ውጊያው ከራሳችንና ሰውን ከጸሎት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ሱታፌ ለማራቅ የተቻለውን ሁሉ ከሚያደርገው ከፈታኙ ከሰይጣን መጥመዶች ጋር ነው፡፡ ስንኖር እንጸልያለን፣ ስንጸልይ እንኖራለንና፡፡ ዘወትር የክርስቶስ መንፈሰ በሚፈቅደው መሠረት መሥራት ካልፈለግን በስሙ የመጸለይ ልምድም ሊኖረን አይችልም፡፡ የክርስቲያኑ አዲስ ሕይወት “መንፈሳዊ ውጊያ” ከጸሎት ውጊያ ተነጥሎ አይታይም፡፡

በጸሎት ላይ ስለሚነሱ ተቃውሞዎች

በጸሎት ውጊያ ላይ በውስጣችንና በዙሪያተን የሚነሱ ጸሎትን የሚመለከቱ የተሳሳቱ ሐሳቦችን መዋጋት አለብን፡፡ አንዳንዶች ጸሎትን እንደ አንድ ስነ-ልቦናዊ እንቅስቃሴ አድርገው ያዩታል፤ ሌሎች ደግሞ ወደ አዕምሯዊ ባዶነት የሚወስድ አትኩሮትን የማጐልበት ጥረት አድርገው ይወስዱታለ፡፡ አሁንም ሌሎች ተግባራት ጋር የማይጣጣም አድርገው ስለሚመለከቱት ለእሱ የሚሆን “ጊዜ የላቸውም” እግዚአብሔርን በጸሎት የሚመጣው ከራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስም እንደሆነ አያውቁምና፡፡

“ከዘመኑ ዓለም” አስተሳሰብ የሚመነጩ አንዳንድ አመለካከቶች ንቁ ካለሆንን በቀር ሕይወታችን ውስጥ ዘልቀው ሊገቡ የመቻላቸውን እውነት መረዳት አለብን፡፡ ለምሳሌ፣ አንዳንዶች እውነት በአእምሮና በሣይንስ የተረጋገጠ መሆን አለበት ይላሉ፤ ነገር ግን ጸሎት ንቃት ካለውና ከሌለው ሕይወታችን አልፎ አልፎ የሚፈስ ምሰጢር ነው፡፡ ሌሎች ግለሰቦች ለምርትና ለትርፍ ከፍ ያለ ዋጋ ይሰጣል፤ በእነርሱ ዘንድ ጸሎት ምንም አያስገኝምና ጥቅም የለውም አሁንም ሌሎች ደስታንና ምቾትንና የእውነት፣ የበጐውና ውብ የሆነው ሁሉ መሥፈርት በማድረግ ከፍ ከፍ ያደርጓቸዋል፤ “የውበት ፍቅር” የሆነው ጸሎት ግን ሕያውና በእውነተኛው አምላክ ክብር የሚደረስበት ነው፡፡ በመጨረሻም አንዳንዶች ደግሞ ጸሎትን የሚመለከቱት ወከባን በመጥላት ከዓለም እንደሚደረግ ሽሽት ነው፤ ነገር ግን ክርስቲያናዊ ጸሎት ከእውነት መሸሽም ይሁን ከሕይወት መራቅ አይደለም፡፡

በመጨረሻም ውጊያችን በጸሎት እንደ ውድቀት የሚያጋጥመንን መፋለም አለበት፡፡ ፍሬ-አልባነት ባጋጠመ ወቅት ተስፋ መቁረጥ፤ “ብዙ ንብረት” እያለን ሁሉንም ለጌታ መስጠት ሲገባን ያንን ባለመፈጸማችን የሚሰማን ተስፋ መቁረጥ፤ እንደፈቃዳችን ስላልተሰማን የሚፈጠርብን ቅሬታ፣ በኃጢአተኝነታችን በደረሰብን ውርደት ይበልጥ የበረታው ትዕቢት፣ ጸሎት ነፃና የማይገባን ስጦታ የመሆኑን ሐሳብ አለመቀበልና ሌሎችም ከዚህ የሚደመሩ ናቸው፡፡ መደምደሚያው ዘወትር ያው ነው መጸለይ ምን ይሠራል? እነኚህን መሰናክሎች ለመወጣት ትህትና፣ እምነትና ጽናትን እናገኝ ዘንድ መጋደል አለብን፡፡