እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የጸሎት ሕይወት

የጸሎት ሕይወት

ጸሎት የአዲስ ልብ ሕይወት ነው፡፡ ጸሎት በእያንዳንዷ ቅጽበት ሊያነቃቃን ይገባል፡፡ ነገር ግን ሕይወታችንና ሁለንተናችን የሆነውን አምላክ ወደ መዘንጋት እናዘነብላለን፡፡ ስለዚህም በኦሪት ዘዳግምና በነቢያት የሚጠቀሱት የመንፈሳዊ ሕይወት አበው ጸሎት አብዛኛውን ጊዜ በልብ ትውስታ የሚንቀሳቀስ እግዚአብሔርን የማሰብ ድርጊት እንደሆነ ስለተገነዘቡ “ከአተነፋፈሳችን ድግግሞሽ በበለጠ እግዚአብሔርን ማስታወስ እንዳለብን” በጥብቅ ያሳስባሉ፡፡ ይሁንና ሆን ብሎ በፍቃዳችን በተወሰኑ ጊዜያት ካልጸለይን በቀር “በማንኛውም ጊዜ” መጸለይ አንችልም፡፡ እነዚህ በጥልቀትም ይሁን በርዝማኔ ክርስቲያናዊ ጸሎት የሚከወንባቸው የተወሰኑ ጊዜያት ናቸው፡፡

 

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ተከታታይ ጸሎትን ለማበልጸግ የታለሙ የተወሰኑ ሥርዓተ-ጸሎቶችን ያቀርባል፡፡ ከእነሱም አንዳንዶቹ የማለዳና የሠርክ ጸሎቶች፣ ከምግብ በፊትና በኋላ የሚቀርቡ ምሥጋናዎቹና ጸሎት ሰዓታት ናቸው፡፡ እሑዶች መሥዋዕተ ቅዳሴን ማዕከል በማድረግ ከሁሉም በፊት በጸሎት ይቀደሳሉ፡፡ የሊጡርጊያዊው ዓመት ዑደትና ዐበይት በዓላቱ የክርስትያናዊው ጸሎት መሠረትና ሕይወቱ  ናቸው፡፡

ጌታ ሰዎችን ሁሉ በጉዞአቸው ላይ እርሱን በሚያስደስቱበት መንገዶችና ሁኔታዎች ይመራቸዋል፣ እያንዳንዱም ምእመናንም በበኩሉ በልቡ ውሳኔና ትውፊት የቃል፣ የማሰላሰልና የጽሞና ጸሎት የሚባሉ ሦስት አበይት መግለጫዎችን አቆይቶልናል፡፡ እነርሱም የጋራቸው የሆኑ አንድ መሰረታዊ የሆነ ባህርይ አላቸው፣ ያም ባህርይ የልብ እርጋታ ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን ለመጠበቅና በእርሱ ፊት ለመኖር የሚያስፈልገው ንቃት እነዚህን ሦስት መግለጫዎች በጸሎት ሕይወት ውስጥ የከፍተኛ ተመስጦ ጊዜያት ያደርጋቸዋል፡፡

የጸሎት መገለጫዎች

1. የቃል ጸሎት

 

በቃሉ አማካኝነት እግዚአብሔር ለሰዎች ይናገራል፡፡ በቃላት፣ በሃሳብ ወይም በድምጽ የሚቀርብ ጸሎታችን መልክ ይይዛል፡፡ ይሁን እንጅ በጸሎት ለምናናግረው ለእርሱ ልብ ይቀርብለት ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ “የጸሎታችን መሰማት ወይም አለመሰማት የሚወሰነው በቃላቱ ቁጥር ሳይሆን በልባችን መንደድ ነው፡፡

 

በቃል ወይም በድምጽ የሚከናወን ጸሎት የክርስቲያናዊ ሕይወት ሁነኛ ክፍል ነው፡፡ በመምህራቸው የተመስጦ ጸሎት ተደንቀው ለነበሩ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ “አባታችን ሆይ” የተሰኘውን የቃል ጸሎት ያስተምራል፡፡ ኢየሱስ ድምጹን ከፍ አደረጐ የጸለየውን በምኩራብ ስርዓት አምልኮአዊ ጸሎቶች ላይ ብቻ አይደለም፡፡  ወንጌላት እንደሚያሳዩት እርሱ በሀሰት ከተሞላው የአብ ቡራኬ እስከ ጌተሰማኔ ስቃይ ድረስ ግላዊ ጸሎቱን በጐላ ድምጽ አሰምቷል፡፡

ስሜቶቻችን ከውስጣዊ ጸሎታችን ጋር የማዋሀድ ፍላጐት ሰብዓዊ ባህሪያችን የሚሻው ነገር ነው፡፡ እኛ ስጋና መንፈስ በመሆናችን ስሜቶቻችን በውጭ የማሳየት ፍላጐት አለን፡፡ ልመናችን የሚቻለውን ያህል ያገኝ ዘንድ በፍጹም ልባችን መጸለይ አለብን፡፡

ድርጊቱ ከመለኮታዊ ፍላጐት ጋር ይስማማል፡፡ እግዚአብሔር በመንፈስና በእምነት የሚያመልኩ ሰዎችንና ከነፍስ ውስጣዊ ጓዳ የሚፈልቅ ሕያው ጸሎትን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር አካልን ከውስጣዊ ጸሎት ጋር የሚያዛምደውን ውጫዊ መግለጫን ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የዚህ አይነት ጸሎት ለአምላክ ተገቢ የሆነ ፍጹም አክብሮትን የቀርባልና፡፡

የቃል ጸሎት ውጫአዊ ከመሆኑም በላይ ፈጽሞ ሰብአዊ ስለሆነ ቡድኖችን የሚያስማማ (ውጫዊ ውህደትን የሚፈጥር) ጸሎት ነው፡፡ ስለዚህ ውስጣዊ ጸሎትም ቢሆን የቃል ጸሎትን ችላ ሊል አይችልም፡፡ ጸሎት በውስጣችን የሚሰርጸው “ማንን እንደምናናግር” በተገነዘብነው መጠን ነው፡፡ በዚህም መሰረት የቃል ጸሎት የጽሞና ጸሎት መጀመሪያ ነው፡፡

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት