እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ዘወረደ እና ዘቅድስት ሰንበትና አዘቦት ቀን ንባባት ላይ የተደርጉ አስተንትኖዎች

Tsom 1ዘወረደ - ዐብይ ጾም 1ኛ ሳምንት

ንባባት፡- ዕብ 13፡7-16፣ ያዕ 4፡6-17፣ ሐው 25፡ 13-27፣ ዮሐ 3፡10-24

መዝሙር  ‹‹እግዚአብሔርን በፍርሃት አገልግሉት፤ በመንቀጥቀጥም ተገዙለት፤ተግሳጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ

በኢትዮጵያ ሥርዐተ አምልኮ የዐቢይ ጾም የመጀመርያው ሰንበት  “ዘወረደ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ሰንበት የእግዚአብሔር ልጅ ወደ ምድር የወረደበትን፣ የሰውን ልጆች ለማዳን የመጣበትን የማዳን ስፍራ ጅማሮ የምናሰላስልበት ሰንበት ነው፡፡ በዚህ ሰንበት የሚነበቡት ንባባት በአጠቃላይ እግዚአብሔር በሰው አምሳል ወደ ምድር መውረዱን የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡

ዘወረደ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መውረድ፣ የአምላክን መገለጥ ያሳስበናል፡፡ ይህ የአምላክ መውረድ፣ የአምላክን መገለጥ ያሳስበናል፡፡ ይህ የአምላክ መውረድ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን በሁለት ሥፍራዎች ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ የመጀመርያው የአምላክ መውረድ የሚታየው የሰው ልጆች የባቢሎንን ግንብ ለመሥራት እና ወደ ሰማይ ለመድረስ በትዕቢት በተነሳሱበት ወቅት ነው፤ በዚህ ጊዜ እግዚአብሐር በታላቅ ቁጣ እንደወረደ እንመለከታለን (ዘፍ 11፡5-7)፡፡ ሁለተኛው “መውረዱ” የተገለጠው በሙሴ ፊት ይነድድ በነበረው ቁጥቋጦ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር እንደቀደመው ሳይሆን በፍቅርና በምሕረት ወረደ (ዘጸ 3፡4)፡፡

እግዚአብሔር በፍቅር እና በምሕረት የወረደበት ቁምነገር የእሥራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ነፃ በማውጣ፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወስዶ ወደ ቀደመው ክብሩ ለመመለስ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከሰማያት መውረድ ዋነኛ ዓላማ ይህ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጆችን ለማዳን መጥቷል፡፡ የዕብራውያን መጽሐፍ ምዕራፍ 10 ይህንን የእግዚአብሔር ልጅ መውረድ የበለጠ ያብራራልናል፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ይፈጸም የነበረው የእንስሳት መሥዋዕት የሰውን እና የአምላክን ግንኙነት በምልዓት ሊያድሰው እንዳልቻለ የዕብራውያን ጸሐፊ ይናገራል፤ በመቀጠልም “ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ (ክርስቶስ) እንዲህ አለ “መሥዋዕትንና መባን አልፈልግህም፤ ሰውነትን ግን አዘጋጀህልኝ፤ በሚቃጠል መሥዋዕትና ስለኃጢአት ሥርየት በሚሰዋ በመሥዋዕት አልተደሰትክም፤ በዚያን ጊዜ እኔ አምላኬ ሆይ በመጽሐፍ ስለ እኔ እንደተፃፈ ፈቃድህን ለመፈጸም መጥቻለሁ አልኩ” (ዕብ 10፡5-7፣ ንጽ መዝ 40፡7-8)፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መግባት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሰው ልጆች ሁሉ በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ይድኑ ዘንድ ነው፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለእግዚአብሔር ሲናገር “የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው” (ሮም 1፡16) ይላል፡፡

ስለ ክርስቶስ ወደ ዓለም መምጣት ወይም ስለ እግዚአብሔር መውረድ ስናሰላስል በዕብራውያን መጽሐፍ የቀረበው ሐሳብ በመዝሙር 40፡1-10 ከተዘመረው መዝሙር ጋር ተጣጥሞ እናገኘዋለን፡፡ ዘማሪው የዕብራውያን መጽሓፍ ትረካን በመድገም ‹‹አንተ መሥዋዕትንና መባን አትፈልግም፤እንሰሶች በመሠዊያ ላይ እንዲቃጠሉ ወይም ለኃጥአት ሥርየት የሚሆን መሥዋዕት እንዲቀርብልህ አትጠይቅም›› (መዝ 40፡6) ካለ በኋላ በዚሁ የመዝሙር ቁጥር ላይ አምላክ ወደ እኛ ሲመጣ ወይም እግዚአብሔር ሲወርድ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ ሲናገር ‹‹በዚህ ፈንታ የአንተን ትዕዛዝ በመስማት እንዳገልግልህ አደረግኸኝ ይላል››፡፡

            እግዚአብሔር በመካከላችን ሲወርድ ከእኛ የሚፈልገው እንድ ቁም ነገር እርሱን እናዳምጥ ዘንድ ነው፡፡ እንሰማው ዘንድ እግዚአብሔር ይህንን ከእያንዳንዳችን ይፈልጋል፡፡ በአዲስ ኪዳን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ተለውጦ ፊቱ እንደ ፀሐይ ባበራበት በደብረ ታቦር ተራራ ላይ የእግዚአብሔር የክብር ደመና ሲገለጥ የተነገረን መልእክት ‹‹የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው፤እርሱን ስሙት! (ሉቃ 9፡35) የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በማጠናከር ‹‹ እምነት ከመስማት ነው፤መስማትም እንደ እግዚአብሔር ቃል ነው››  (ሮም 10፡17) በማለት አንሰማ ዘንድ ይጋብዘናል፡፡ በመሥዋዕተ ቅዳሴ ውስጥ ‹‹ ለመስማት ጆሮአችሁን ክፈቱ›› እያልን እንጸልያለን፡፡ ይህ እንሰማው ዘንድ የቀረበልን ጥሪ ወደ እርሱ ልብ የሚያስጠጋን እና ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስችለን ቁም ነገር ነው፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያም ‹‹እርሱ የሚላችሁን አድርጉ›› (ዮሐ 2፡5) በማለት በመስማታችን የእግዚአብሔርን ፍቃድ ፈጽመን ፍሬአማ መሆን እንደምንችል መንገድ ታሳየናለች፡፡

            ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ ‹‹ስሙ አስተውሉም›› (ማቴ 15፡10 ፤ማር 7፡14) ይላል፡፡ ሕዝሙ እርሱን ይሰሙትና ያስተውሉት ዘንድ ይመክራቸዋል፡፡ነገር ግን በሌላ ስፍራ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ከምትሰሙት ነገር ተጠበቁ›› (ማር 4፡24) እያለ በብር ሲያስጠነቅቃቸው እንመለከታን፡፡ በየዕለቱ ስንሰማ የምንውለው ነገር የእግዚአብሔርን ድምጽ የበለጠ አጉልቶ የሚያሰማን ነገር ነው ወይም የእግዚአብሔርን ድምጽ የበለጠ አጉልቶ የሚያሰማን ነገር ነው ወይም የእግዚአብሔርን ድምጽ ከእኛ የሚያርቀውን ነገር ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆላስያስ ለሚገኙ ክርስትያኖች ይህንን ጉዳይ በግልጽ ያስተምራቸዋል፡፡ እነርሱንም ከዘመኑ ድምፆች ይጠበቁ ዘንድ እንዲህ ይላቸዋል፡‹‹እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማውዊ እንደ መጀመርያ ትምህርት ባለ ፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ››(ቆላ 2፡8) ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደ ክርስስ ትምህርት ለእግዚአብሔር ቃል ጆሮአችንን እና ልባችንን ከፍተን እናዳምጠው ዘንድ እግዚአብሔር በመካከላችን ወርዷል፤ እግዚአብሔር በመካከላችን ሲወርድ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መሥዋዕት እርሱን መሥማትና ሰምተንም የእርሱን ፈቃድ መፈጸም ነው፡፡

ዘቅድስት                                                               ዓብይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት

ንባባት 1ኛ ተሰ 4፡1-12፤ 1ኛ ጴጥ 1፡13-25 ፤ ሐ ሥ 10፡ 17-29 ፤ ማቴ፡6 16-24

መዝሙር

 ‹‹እግዚአብሔርን ሰማያትን ሠራ፤ምሥጋናና ውበት በፊቱ፤ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው›› (መዝ 95፤5-6

            የዓብይ ጾም ሁሌኛ ሳምንት ዘቅድስት በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰንበት ያስተማረውን ትምህርት የምናሰላስልበት ወቅት ነው፡፡ ኢየሱስ እንደማንኛውም አይሁዳዊ በሰንበት ወደ ቤተ መቅደስ ይሄድ ነበር፡፡ በጊዜው በነበረው ሥርዐት መሥት ሁሉን ይፈጽም ነበር፡፡ ነገር ግን የሙሴ ሕግ መምህራን እና ፈሪሳውያን ኢየሱስ ስለ ሰንበት ያለውን አመለካከት ለመፈተን በማሰብ በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲጠይቁት እንመለከታን፡፡ ኢየሱስም በሰንበት ቀን መልካም ነገር ማድረግ ተገቢ መሆኑንና ከሰንበት ግንዛቤ ጋር የማይቃረን መሆኑን በምሳሌዎች ያስተምራቸውል፡፡

            የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ክፍል ኦሪት ዘፍጥረት ስለ እግዚአብሔር ‹‹ሥራ›› እና ስለ እግዚአብሔር  ‹‹ዕረፍት›› ይናገራል፡፡  ‹‹ እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው ቀደሰውም›› (ዘፍ 2፡3) ፡፡ እግዚአብሔር ስለ ሰንበት ያለው ሐሳብ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ ለንበትን ማክበር ከአሥርቱ ትዕዛዛት አንዱ ሆኖ ለሰው ልጆች ሁሉ ተሰጥቷል፡፡ ይህ ዕለት ከሥራ የምንፍፍበት፤ከቤተሰብ ጋር የምንደሰትበት፤ በጠዋት የማንነሳበት ወ.ዘ.ተ ሳይሆን ከሁሉ በላይ ከእግዚአብሔር ጋር የምንገኝበት፤ከእርሱ ጋር ጊዜ የምንወስድበት እና ከእግዚአብሔር ኃይል ተሞልተን የምንታደስበት ዕለት ነው፡፡

            ዕለተ ሰንበት በእግዚአብሔር የተባረከ፤የተቀደሰ፤ከሌሎቹም ቀናት ተለይቶ ‹‹የጌታ ዕለት›› እየተባለ የሚጠራ ቀን ነው(ራዕይ 1፡ 10) ይህም ከመጀመርያው አንስቶ  በቤተክርስትያን ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሥፍራ  ይዞ ይገኛል፡፡ ከአሥርቱ ትዕዛዛት መካከል ሦስተኛው ትዕዛዝ ይህንን ዕለት  ‹‹ ትቀድሰው ዘንድ አስብ›› (ዘጸ 20፡8) ይላል፡፡ ይህ ዕለት የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በተለየ መልኩ የምናሰላስልበት፤ ከፍ ባለ ምሥጋና የምንወድስበት ዕለት ነው፡፡ የሰው ልጅ በሰንበት ከሥራ ሁሉ ያርፋልስ ስንል በምንም አይነት ነገር ሳይጠመድ በሙሉ ልቡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመቆየት ዝግጁ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ልቡን ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርጎ ውስጣዊ የሆነ ምሥጢራዊ ግንኙነት የሚያደርግበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ሰንበት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተማረ ሆኖ የሚያርፍበት ዕለት ስንል ከሥጋዊ መባከን እፎይ የሚልበት ዕለት ብቻ ሳይሆን በሥጋም በመንፈስም ሰላም፤እረፍት፤ እፎይታ መታደስ የሚያገኝበት ቁም ነገር አብሮት አለ፤ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማሙ፤በሞቱ እና በትንሳኤው ወደአስገኘልን ዘላለማዊ እረፍት እንድንገባ በር ይከፍትልናል፤ የሰንበት ትዕዛዝ ፍፃሜ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም፤ ሞት እና ትንሳኤ መካፈል ነው፡፡

           

ሰኞ                                                                             ዓብይ ጾም 2ኛ ሳምንት

ሰንበት የጌታ ዕለት በመሆኑ (ራዕ 1፡10) የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ በሰንበት አማካኝነት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በየሳምንቱ እናከብራለን፤እርሱ በኃጢአት እና በሞት ላይ ድል ተቀዳጅቶ ፍጥረትን ሁሉ ወደ ሙላቱ እንዳደረሰ የምንዘክርበት በዓል ነው፡፡ ዕለተ ሰንበት በክርስቶስ የዳነው ዓለም የመጀመሪያው አዲስ ዕለት ነው፡፡ በመሆኑም ዘማሪው ስለዚህ ሥጦታ ሲዘምር  ‹‹እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህቺ ናት፤ሐሴትን እናድርግ በእርሷም ደስ ይበለን›› (መዝ 118፡24) ይላል፡፡ ይህ የደስታ መዝሙር የሚፈጸምባት ዕለት መግደላዊት ማርያም መቃብሩ ባዶ ሆኖ ባገኘችበት ዕለት ነው‹‹ከሳምንቱ በፊተኛው ቀን፤ እጅግ በማለዳ›› (ማር 16፡2)፡፡

            ይህ ዕለት ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ክርስቶስ  በመካከላችን የሚገኝበት አብሮን የሚጓዝበት የትንሳኤ ዕለት ነው፡፡ በሰንበት በየሳምንቱ ፋሲካ እናከብራለን፡፡ ይህ ዕለት እንደ ኢማሁስ መንገደኞች በጉዟችን ጌታን የምናገኝበት፤ከእርሱም ሁሉን ነገር የምንማርበት፤ልባችን በፍቅሩ የሚቃጠልበት፤ ከአምላክ ጋር በአንድ ገበታ የምንቀርብበት እና በቅዱስ ቁርባን ሥጦታ ዐይኖቻችን ተከፍተው እርሱን የምናውቅበት፤ እንዲሁም ለምሥክርነት የምንወጣበት ዕለት ነው (ሉቃ 24፡13-36) ፡፡ ዕለተ ሰንበት ጌታ ሕዝቡን የሚጎበኝበት፤ የሰላም እና የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታን የሚያፈስበት የትንሳኤ ፍሬ ወራሾች የምንሆንበት ዕለት ነው (ዮሐ 20፡ 19-23)

ማክሰኞ                                                                                 ዓብይ ጾም 2ኛ ሳምንት

ቤተክርስቲያን ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ሰንበትን በቅድስና ጠበቃ በመያዝ በየእሑዱ የትንሳኤን ምሥጢር በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባዔ ይህንን በግልጽ ያስረዳናል ‹‹በየሰባተኛው ቀን ቤተ ክርስትያን የትንሳኤን ምሥጢር ታከብራለች፤ይህም ከሐዋርያት ጊዜ አንስቶ ሲተገበር የቆየ እና መነሻውን ክርስቶስ ትንሳኤ ባደረገበት ዕለት ያደረገ ተግባር ነው፤ በዚህች ቀን ክርስቶስ ትንሳኤ አድርጓልና ‹‹የጌታ ዕለት›› ተብላ ትጠራለች›› (2Vat. Sacrosanctum Conciliun; 106) የጌታ ዕለት የቀናት ሁሉ ንግስት ናት፤ሰንበት የክርስስ ትንሳኤ የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ የክርስቲያኖች ቀን ናት፤ ስለዚህ ለክርስያች ሰንበት መሠረታዊ የበዓል ዕለት ነው፡፡

            ይህ በዓል የሚፈጸመው በመሥዋዕተ ቅዳሴ ነው፡፡ የሰንበት መሥዋዕተ ቅዳሴ ምዕመናን የጌታ ቃል ለመሥማትና በመሥዋዕተ ቅዳሴ ለመሳተፍ በዚህም አኳኋን ሕማሙን፤ሞቱንና ትንሳኤውን ለማክበር፤ ወደ ሕያው ተስፋ ይመልሳቸው ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ዳግም የወላዳቸውን እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚሰበሰቡበት ከቀናት ሁሉ የላቀ የምሥጋና ቀን ነው (ካ.ት.ክ.ቁ.1167)አዳምን ልጆቹም ሁሉ ያለ ፍርሃት ይገቡበት ዘንድ የመንግሥተ ሰማይ በሮች የተከፈቱበት ዕለት በመሆኑ፤እሑድ የተቀደሰ ቀን ነው፡፡

ረቡዕ - የቃል ገበታ                                                              ዐብይ ጾም 2ኛ ሳምንት

በቅዱስ ቊርባናዊ የአምልኮ ሥርዐት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለት ገበታ ከሕዝቡ ጋር ይገናኛል፡፡ የመጀመርያው ገበታ የቃል ገበታ ሲሆን ሁለተኛው ገበታ የቊርባን ገበታ ነው፡፡ የቃል ገበታ ልባችን የቅዱስ ቊርባን ገበታ ላይ እንዲቀርብ ያዘጋጀዋል፡፡ የቃል ገበታ አገልጋይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶ በዘላለማዊ የሕይወት ቃል ያዘጋጀናል፡፡ በመሥዋዕተ ቅዳሴ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነበበው የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለሥጋ ወደሙ ለማዘጋጀት ነው፡፡ በቤተክርስትያን መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብበት ጊዜ ሁሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ ያናግረናል፡፡ (II Vati, coun. Sacrosanctum Concilum 7: cf 33)

ይህ የቃል ገበታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባደረገው መልኩ የሚፈጸም ነው፡፡ በሉቃስ 24፡ 13-36 ባለው ታሪክ ስንመለከት ኢየሱስ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ ከነበሩት ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት ጋር ሲጓዝ መጀመርያ በእግዚአብሔር ቃል እንዳዘጋጃቸው እንመለከታለን፡፡ እነርሱም ራሳቸው “ከሕግ እና ከነብያት መጽሐፍት እየጠቀሰ ሲናገረን ልባች ይቃጠልንበን አልነበረምን” (ሉቃ 24፡35) በማለት ይመሰክራሉ፡፡ ልባቸው በእግዚአብሔር ቃል ገበታ በሚገባ ስለተዘጋጀ ለሁለተኛው ገበታ ከአምላክ ጋር በማዕድ ተቀመጡ፡፡ በመሥዋዕተ ቅዳሴ እንዲህ በሁለት ገበታ ኢየሱስን እንመገባለን፤ የቃል ገበታ በቊርባን ገበታ ፍፃሜውን ያገኛል ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስትያን በመሥዋዕተ ቅዳሴ በእግዚአብሔር ቃል ገበታ እና በቅዱስ ቊርባን ገበታ ይበለጽግ ዘንድ በሰንበት ያለ በቂ ከባድ ምክንያት ከመሥዋዕተ ቅዳሴ መጉደል ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡

ሐሙስ - የቊርባን ገበታ                                                                 ዓብይ ጾም 2ኛ ሳምንት

የቃል ገበታ ወደ ቊርባን ገበታ ይመራናል፡፡ ይህም ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች ባቀረቡት ጥያቄ በግልጽ ይታያል፡፡ እነርሱ ኢየሱስ ከሕግ እና ከነብያት መጽሐፍት እየጠቀሰ ካስረዳቸው በኋላ በራቸውን ከፍተው “ከእኛ ጋር እደር” (24፡29) ብለው ለመኑት፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ገበታ ያቀርበናል፡፡

መሥዋዕተ ቅዳሴ የመጨረሻውን የፍቅር ሥጦታ የምንቀበልበት ገበታ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ እጅግ ስለወደደ ራሱን ሰጠ፤ ሥጋውን ቆርሶ፣ ደሙን አፍስሶ የሕይወት እጀራ ሆኖ ወደ እኛ መጥቷል፡፡ በኅብስት እና በወይን መልክ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ኢየሱስ በመሥዋዕተ ቅዳሴ መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል፤ የሕይወት ምግብ ሆኖ ይሰጣል፡፡
በመስዋዕተ ቅዳሴ የእያንዳንዳችን ምኞት፣ ሥራ፣ ስቃይ፣ ደስታ፣ ኀዘን፣ ተስፋ፣ ምስጋና ወ.ዘ.ተ. ፍጹ ከሆነው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቊርባናዊ መስዋዕት ጋር አንድ በመሆን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የተቀደሰ መስዋዕት ሆኖ ይቀርባል፡፡ ከመስዋእተ ቅዳሴ የሚገኘውን ፍጹም መለኮታዊ ስጦታ፣ የጌታች የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም በመቀበል በየዕለቱ እንታደሳለን፡፡ በመሥዋዕተ ቅዳሴ ተሳትፎ ቅዱስ ቊርባን የማይቀበል ክርስትያን በሰርጉ ቀን ሙሽራይቱ እንደቀረችበት ሙሽራ ነው፤ ዘወትር በመሥዋዕተ ቅዳሴ ቅዱስ ቊርባን በተገቢ ዝግጅት በመቀበል ክርስቶስን በመምሰል እናድጋለን፡፡

ዐርብ - ተልዕኮ                                                                 ዐቢይ ጾም 2ኛ ሳምንት

የሕይወት እንጀራ ከተቀበሉ በኋላ የኢየሱስ ደቀመዛሙርት ከሙታን በተነሳው በክርስቶስ ኃይል ለምሥክርነት ይወጣሉ፡፡ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩት ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ጋር ተገናኝተው ከቃል እና ከቁርባን ገበታ ከተመገቡ በኋላ ‹‹በዚያች ሰዓት ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ….እነርሱም በመንገድ የሆነውን እንጀራውንም በቆረሰ ጊዜ እንዴት እንደታወቀላቸው ተረኩላቸው›› (ሉቃ 24፡ 33-35)፡፡

የቅዱስ ቁርባን በዓል በቤተክርስትያን ሕንፃ ውስጥ ተጀምሮ እዚያው የሚያበቃ ጉዳይ አይደለም፤የትንሳኤው ምስክሮች እንደነበሩት ልክ እንደ መጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት በየእሑዱ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስን የሚያከብሩ ክርስቲያኖች ሁሉ በዕለት ተዕለት የሕይወት ምሥክርነታቸው የስብከተ ወንጌል ልዑካን ይሆኑ ዘንድ ተጠርተዋል፡፡ ቅዱስ ቁርባን ከተቀበልን በኋላ በጸጥታ ሆነን የምንሳርገው አጭር የምሥጋና ጸሎት በታላቅ ጸጋ የሚሞላን በመሆኑ በፍጹም ምሥጋና ሳናቀርብ መውጣት የለብንም፡፡ ‹‹በሰላም ሒዱ›› የሚለው የመሥዋዕተ ቅዳሴው የማሳረጊያ ቃል ‹‹እንግዲህ ወደ ዓለም ሁሉ ሒዱ፤ አሕዛብንም ሁሉ በአብ፤በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፤ያዘዝኋችሁምን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ›› (ማቴ 28፡19) የሚለውን የጌታችንን ትዕዛዝ ያስታውሰናል፡፡

            በመሥዋዕተ ቅዳሴ የተቀበልነው የሥጋ ወደሙ ሥጦታ ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን፤ለሰው ልጆች በሙሉ እናካፍለው ዘንድ ኃላፊነት አለብን፡፡ በለጋሥነት እና ሕይወታችንን ለሰው ልጆች ቅድስና አሳልፈን በመስጠት የምንከፍለው የፍቅር ዕዳ አለብን፡፡ ኢየሱስን በቅዱስ ቁርባን ያገኘ ክርስያን ዘወትር በተልዕኮ ውስጥ ይጓዛል፡፡

ቅዳሜ - ሰንበትን ማክበር                                                               ዓብይ ጾም 2ኛ ሳምንት

            እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ክርስትያን በሆኑ ሀገሮች ዘንድ ሰንበትን የማክበር ግንዛቤ የጎላ ስፍራ ነበረው፤ በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ሰዎችን ተቋማት እሑድ የእረፍት ቀን መሆኑ በሳምንቱ የሥራ ዕቅድ ውስጥ በግልጽ የማስቀመጥ ባሕል ነበራቸው፡፡ አሁን አሁን ግን ሀገራችን ኢትጵያን ጨምሮ ለሰንበት ቅድስና ያለው ክቡር እየተሸረሸረ መጥቶ በሰንበት ቀን መሥርያ ቤቶች ክፍት ይሆናሉ፤የትምህርት ተቋማት ወጣቱን በዚህ ዕለት ለፈተና ይጠራሉ፤መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ስብሰባዎችም መሥዋዕተ ቅዳሴ በሚፈጸምበት እኩል ሰዐት ይሰበሰባሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የማኀበረሰቡን ክርትያናዊ እሴቶች በማቀጨጭ ሰው ከአምላኩ ጋር እንዳይገናኝ በምሥጢር የሚሠሩ የዲያብሎስ ዘመናዊ መሣሪያዎች ናቸው፡፡

በየእሑዱ ማኀበረሰቡን ከቤተክርስትያን እና ከቅዳሴ መሥዋዕት በሚያጎድሉ ሓሳቦች ጠምዶ መያዝ እግዚአብሔርን ከመካከላችን ለማራቅ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ መንግሥትም ይሁን የግለሰቦች ተቋማት የሰው ልጆችን የአምልኮ ተግባር በሚያውክ መልኩ ከመንቀሳቀስ መቆጠብ አለባቸው፡፡ የሰው ልጆች  ከኃጢአት ባርነት እና ከጭቆና ቀንበር ነፃ የወጡትና በውድ የደም ዋጋ የተገዙት ለአምልኮ ተግባር መሆኑን በፍጹም መዘንጋት የለብንም፡፡ እግዚአብሔርን ከማኀበረሰቡ መካከል ባጠፋነው መጠን ማኅበረሰቡ ኢ-ሰብዓዊ ማኅበረሰብ እየሆነ ይመጣል፡፡ የማኅበረሰቡን እሴቶች በሙሉ ኢ-ክርስቲያናዊ ባደረግናቸው መጠን ትውልድ መረን ይሆናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በራሱ ለይቶ የቀደሰውን ቀን በማክበር የእግዚአብሔር ሕልውና ከማኅበረሰቡ ዘንድ እንዳይጠፋ ዘወትር በንቃት መጠበቅ ይገባናል፡፡

በወጣት ሳምሶን ደቦጭ - ከቅ. ዮሴፍ ቁምስና ዘሲታውያን አ.አ.

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት