የአራቱ ውድ እህቶች አጭር የሕይወት ታሪክ

s. ann sisters ethiopia accident 1በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቅ. ሐና ልጆች ማኅበር እህቶች ላይ ከቀናት በፊት የሁላችንን ልብ የነካ ኀዘን ማጋጠሙ ይታወሳል። በአንዳንድ ምክንያቶች የሕይወት ታሪካቸውን በወቅቱ ሳናካፍል ምንም እንኳ ጥቂት ቀናት ያለፉ ቢሆንም አሁንም ፋይዳ ይኖረዋል ብለን ስላመንበት ከማኅበራችው ያገኘነውን አጭር የሕይወት ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

የእህቶቻችን አጭር የሕይወት ታሪክ

እህት ሐና ወይንሸት ገብሩ ከአባታቸው ከአቶ ገብሩ ተረዳ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ እታገኘሁ ማሞ በአዲስ አበባ ከተማ  በግንቦት 8/1968 ዓ/ም ተወለዱ፡፡ በምንኩስና ሕይወት እግዚአብሔርን ለማገልገል ባላቸው የጋለ ፍቅር በቅድስት ሐና ልጆች ገዳም በመግባት በ1988 ዓ/ም የመጀመሪያ መሐላቸውን በአስመራ ከተማ አደረጉ፡፡

በመቀጠልም ለአምስት ዓመት የምንኩስና ጉዞ ካደረጉ በኋላ በ1993 ዓ/ም በሮም በመሐበሩ ጠቅላይ ቤት የመጨረሻ እሽታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ እህት ሐና ወይንሸት ገብሩ በ1995 ዓ/ም እስከ 2004 ዓ/ም ድረስ የተመካሪያን አስተማሪ፤ የአውራጃው አማካሪ፤የአውራጃ አለቃ እንደራሴ በመሆን አገልግለዋል፡፡

እህት ሐና ወይንሸት ገብሩ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ  ሕይወታቸው እስካለፈበት የካቲት 28/2009 ዓ/ም ድረስ በኢትዮጵያ የቅድስት ሐና ልጆች ገዳም የበላይ አለቃ ሆነው አገልግለዋል፡፡

እህት ሐና ሞቱ ባባ አጭር የሕይወት ታሪክ

 እህት ሐና ሞቱ ባባ ከአባታቸው ከአቶ ባባ ቡስና እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ኤቢሴ ቤግና በ በነቀምት ከተማ ኮንቺ በሚባል ቦታ   በጥቅምት  20/1962 ዓ/ም ተወለዱ፡፡ በምንኩስና ሕይወት እግዚአብሔርን ለማገልገል ባላቸው የጋለ ፍቅር በቅድስት ሐና ልጆች ገዳም በመግባት በ1985 ዓ/ም የመጀመሪያ መሐላቸውን በአስመራ ከተማ አደረጉ፡፡

በመቀጠልም ለአምስት ዓመት የምንኩስና ጉዞ ካደረጉ በኋላ በ1990 ዓ/ም በአዲስ አበባ በቅድስት ሃና ልጆች ገዳም የመጨረሻ እሽታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ እህት ሐና ሞቱ ባባ  በጎንደር አርባብ ፤ በቦዲቲ በጉደር ህፃናት ማሳደጊያ በአዲስ አበባ የቤት አለቃና የአዉራጃ  አለቃ አማካሪ በመሆን  አገልግለዋል፡፡

እህት ሐና ለተ ሐና በኩቴ  ከአባታቸው ከአቶ በኩቴ ኤርናሞ  እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ኤርሞሌ ኢርጋቦ  በሳዳማ ከንባታ  በሚባል ቦታ በ1962 ጥር 5 ቀን ተወለዱ፡፡ በምንኩስና ሕይወት እግዚአብሔርን ለማገልገል ባላቸው የጋለ ፍቅር በቅድስት ሐና ልጆች ገዳም በመግባት በ1984 ዓ/ም የመጀመሪያ መሐላቸውን በአስመራ ከተማ አደረጉ፡፡

በመቀጠልም ለስድስት ዓመት የምንኩስና ጉዞ ካደረጉ በኋላ በ1990 ዓ/ም በአዲስ አበባ በቅድስት ሃና ልጆች ገዳም የመጨረሻ እሽታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡ እህት ሐና ለተ ሐና በኩቴ በአሰላ፤ በሞኮኒሳ፤ በጎንደር አርባባ፤ በጉደር፤ በዕዳጋ ሐሙስ ርእሰ መምሕርና የሞራል አስተማሪ በመሆን አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም ሕይወታቸው እስከአለፈበት ጊዜ ድረስ በካቴድራል የወንዶች ትምህርት ቤት  በሞራል  የስነ ምግባር ትምህርት አስተማሪ ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡

እህት ሐና ጊደና ወልዱ    ከአባታቸው ከአቶ ወልዱ ተስፋት  እና ከእናታቸዉ ከወ/ሮ መና ወ/ገብርኤል በትግራይ ክልል አሊቴና  በሚባል ቦታ በ1958 ቀን ተወለዱ፡፡

በምንኩስና ሕይወት እግዚአብሔርን ለማገልገል ባላቸው የጋለ ፍቅር በቅድስት ሐና ልጆች ገዳም በመግባት በ1993 ዓ/ም የመጀመሪያ መሐላቸውን በአዲስ አበባ በቅድስት ሐና ልጆች ገዳም የመጀመሪያ መሐላቸውን አደረጉ፡፡ በመቀጠልም ለአምስት ዓመት የምንኩስና ጉዞ ካደረጉ በኋላ በ1998 ዓ/ም በአዲስ አበባ በቅድስት ሃና ልጆች ገዳም የመጨረሻ እሽታቸውን ለእግዚአብሔር ሰጡ፡፡

እህት ሐና ጊደና ወልዱ    በጎንደር አዘዞ ከአይነ ስውራን ሕፃናት ጋር ፤ በአንቦ ፤  በዕዳጋ ሐሙስ በሴቶች ዕድገት ማሰልጠኛ ማዕከል፤ በአሰላ የወንዶች ሕፃናት ማሰደጊያ፤ ሕይወታቸው እስከአለፈበት ጊዜ ድረስ በቦዲቲ ወላይታ የቤት አለቃ በመሆን አገልግለዋል፡፡ እህቶቻችን ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እንደማሕበራችን መስራች እንደ ብፅዕት ሮዛ ጋቶርኖ በተሰማሩበት  ሐዋርያዊ ስራ ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመሀበሩ መንፈሳዊነት ማለትም በእናታዊ አገልግሎት ፤ በልብ ድህነትና  በቤተሰባዊ መንፈስ በቅንነትና በታማኝነት እህቶችንና ወንድሞችን አገልግለዋል፡፡

ቅዱስ ጳዉሎስ “ጦርነትን በመልካም ተዋግቻለሁ ፤ ሩጫን እስከመጨረሻዉ ሮጫለሁ ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ የፅድቅ አክሊል ተዘጋጅቶ ይጠብቀኛል፤ ይህንንም አክሊል ቅን ፈራጅ የሆነዉ ጌታ ይሰጠኛል፡፡” 2ኛ ጢሞ 4፡7-8 እንደሚለዉ እህቶቻችን በየካቲት 28/2009 ዓ.ም ለቀብር ወደ አዋሳ  እየተጓዙ እያለ በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ  ምድራዊ ጉዞአቸዉን  ፈፅመዉ ወደ አምላካቸዉ ተጠርተዉ ሄደዋል፡፡ ብፅዕ አባታችን ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን ብፁዓን ጳጳሳት፤ክቡራን ካህናትና ደናግል እንዲሁም የተወደዳችሁ የሐዘናችን ተካፋዮች ለመሆን በመሐከላችን የተገኛችሁ ምዕመናን በሙሉ ጌታቸን ኢየሱስ ክርስቶስ “ትንሳኤና ሕይወት እኔ ነኝ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳን በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ከቶ አይሞትም”” እንደሚለን ምንም እንኳን የምንወዳቸውና የምናከብራቸው የማሕበራችን እህቶች በሥጋ ቢለዩንም በመንፈስ ግን ከክርስቶስ ጋር እንዳሉ እናምናለን፡፡ በዚህም እንፅናናለን፡፡ በእህቶቻችን ላይ የደረሰው ድንገተኛ አደጋ በሰብአዊ አስተሳሰብ ለምንና እንዴት እያልን ብንጠይቅም በተሰዋ ሕይወት ለምንኖር ለእኛ መነኩሳት ግን የእግዚአብሔር ፍቃድ ይሁን ብለን ዝም ለማለት ወደናል፡፡ ስለዚህም እናንተም የጥልቅ ሐዘናችን ተካፋዮች ለመሆን እዚህ ከእኛ ጋር የተገኛችሁ በሙሉ  የውድ እህቶቻችን ነፍስ በእናታችን በቅድስት ሐናና በብፅዕት ሮዛ አማላጅነት እግዚአብሔር አምላክ ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር እንዲያኖርልን እንዲሁም በዚህ በኢትዮጵያ አውራጃ ለምንገኝ የቅድስት ሐና ልጆች በተጠራንበት የጥሪ ጎዳና ጠንክረንና ለእግዚአብሔር መንግስት አገልግሎት እንደ እህቶቻችን ታማኞች ሆነን እንገኝ ዘንድ በፀሎት ከእኛ ጋር እንድትሆኑ እንጠይቃለን ፡፡

የመፅናናት አምላክ ለቅድስት ሃና ልጆች ገዳም፤ ለመላዉ ቤተሰቦቻቸዉ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ሁሉ ፅናቱን ይስጥልን፡፡ ነፍሳቸዉን በገነት ያኑርልን፡፡