የር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ጉብኝት በግብጽ

የር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ጉብኝት በግብጽ

ማንኛውም የአመፅና የጥላቻ ድርጊት በእግዚአብሔር ወይም በሃይማኖት ስም ተገንነት የሚደረግ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም ማዋረድ ነው!

pope in Egyptር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ከሚያዝያ 20-21 የቆየ የሁለት ቀናት የግብጽ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል። በብዙ መልኩ ትልቅ ትርጉም ያለውና ውጤታማው ጉብኝታቸው ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ተስፋ፣ እምነትና ፍቅር ጥልቅ መልእክትን ያስተላለፈ ነው። በቅርቡ በቅብጥ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው የሽብር ግድያ ለወትሮም በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ያለውን ውጥረት እንዲሁም ደግሞ የአሸባሪ ቡድኖች የማሸበር ስጋት በጨመረበት ወቅት ር.ሊ.ጳ. ወደ ግብጽ ያደረጉት ጉዞ ለየት ያለ ትኩረት የሚስብ ነበር፤ ለዚህም ነው ከመነሻው ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ “ወደ ግብጽ የምጓዘው የሰላም መልእክተኛ ሆኜ ነው” በማለት በቦታው ያሉ ክርስቲያኖች የተጠሙትን መልእክት አንግበው የተጓዙት።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ያደረጉት ጉብኝት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ግብጽን ከጎበኙ ከ20 ዓመታት በኋላ ሲሆን በአሁኑ ጉብኝታቸው ወቅት በነበራቸውም ቆይታ ከአገሪቱ ርእሰ ብሔር ጀምሮ ታላላቅ የክርስትናና የእስልምና እምነት አባቶች ጥሩ የሆነ አቀባበልና መስተንግዶ አድርገውላቸዋል። ር.ሊ.ጳ. በዚህ ጉብኝታችው የተለያዩ መልእክቶችን ያስተላለፉ ሲሆን በግብጽ ላሉት ቁጥራቸው 272,000 ለሆኑትና በ213ቁምስና ውስጥ ለሚገኙት ካቶሊኮች “እግዚአብሔር በሕይወታችን በምንመሰክረው እምነት ብቻ ነው የሚደሰተው፤ ምክንያቱም አማኞች ሊኖራቸው የሚገባ ብቸኛ አክራሪነት የፍቅር አክራሪነት ነው! ከዚህ ውጪ የሆነ አክራሪነት ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚመጣ አይደለም እሱንም አያስደስተውም! እውነተኛ እምነት የምንከፍለውን ዋጋ ሳናስብ ያለምንም ልዩነትና ምርጫ ሰዎችን ሁሉ ለማፍቀር የሚያንቀሳቅሰን ነው” ብለዋል።  

ጽንፈኛ ከሆኑ ሙስሊም አሸባሪዎች ክርስቲያኖች ላይ በተነጣጠረው የግድያ ወንጀል እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ስለራሳችን እምነትና የሌሎችንም በሚመለከት ረገድ ር.ሊ.ጳ. ሲናገሩ “እውነተኛ እምነት ልክ የራሱን እምነትና እውቀት በትልቅ ስሜትና ቅንዓት እንደሚከላከል ሁሉ የሌሎችንም መብት ወደ መከላከል ይመራል፤ በርግጥ ይበልጥ በእምነትና በእውቀት ባደግን መጠን በትሕትናና ትንሽ መሆናችንን በመገንዘብ እናድጋለን” ብለዋል። ግብጽ እንደደረሱም ባሰሙት የመጀመሪያ ንግግራቸው ማንኛውም የአመፅና የጥላቻ ድርጊት በእግዚአብሔር ወይም በሃይማኖት ስም ተገንነት የሚደረግ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም ማዋረድ መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። “ስለዚህ ሰላም ብቻ ነው ቅዱስ የሆነ ነገር፤ ማንኛውም ዓይነት አምፅ በእግዚአብሔር ስም መደረግ የለበትም፤ ይህ ከሆነ ስሙን ማርከስ ነው” በማለትም አብራርተዋል።

969 ዓ.ም. በተቆረቆረው በአል አዝሓር መስጊድ በተካሄደው ስለ ሰላም በሚወያይ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ር.ሊ.ጳ. የተገኙ ሲሆን በዚሁ ጉባዔ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የ1.5 ቢሊየን ሱኒ ሙስሊሞች የበላይ የሚባሉትም ሼክ አህመድ መሃመድ ኤልጣይብም ንግግር አሰምተዋል። በዚህ ጉባዔ ላይ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ “በሃይማኖት ስም የሰውን ክብርና መብት ላይ አምፅ የሚፈጽምን ድርጊት እንደ እምነት ክፍል ሳይሆን እንደጣዖት አምላኪ ቆጥረን የመቃወም ግዴታ አለብን። በሰው ላይ የሚደረጉ አካላዊ፣ ትምህርታዊና ስነልቦናዊ የኃይል እርምጃዎችን ሁሉ በመቃወም የሰውን ልጅ ሕይወት ቅዱስነት ሁላችን አንድ ላይ ሆነን እናውጅ” በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀን ላይ 15,000 ለሚሆኑ ካቶሊካውያን በአገሪቱ የመከላከያ ስታዲየም ውስጥ መስዋእተ ቅዳሴን ያሳረጉ ሲሆን ምንም እንኳ የስታዲየሙ ሰው የማስተናገድ አቅም 25,000 ቢሆንም ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምክንያት ያን ያህል ቁጥር እንዲገባ አልተደረገም። ር.ሊ.ጳ. በቆይታቸው ወቅት በሕዝብ መካከል በቅርበት የሚንቀሳቀሱባት መኪና ጥይት የማታስገባ እንድትሆን የታሰበ ቢሆንም እርሳቸው ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን በመግለጻቸው ልዩ መከላከያ በሌላት መኪና ሲንቀሳቀሱ እንደነበረም ተዘግቧል።