በደብረብርሃን ቁስቋም ማርያም ዓመታዊ ንግሥ ተከበረ።

Debreberhan Catholic Churchኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ደብረብርሃን የሚገኘው ደብረ ቁስቋም ማርያም ቁምስና ዓመታዊ ንግሥ በዓል በድምቀት ተከብሮ ውሏል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምንም እንኳን እንደሌሎቹ ዓመታት በበዓሉ ላይ ከአዲስ አበባ ቁጥራቸው ብዙ የሆነ ምእመናን ባይመጡም ከመንዲዳ ደብረ መድኃኔዓለም በመጡ መዘምራንና ምእመናን፣ እንዲሁም የቁስቋም ማርያም ምእመናንና መዘምራን በተገኙበት በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ መሪነት እና ሲታውያን ካህናት አጃቢነት ሥርዓተ ቅዳሴ አርጓል። ከዚያም በመቀጠል የዑደት ሥርዓት ተደርጎ በቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ተፈጽሟል።

ብፁዕ አባታችን በመሥዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ስብከትን ሲያሰሙ በእለቱ በተነንበበው የማቴዎስ ወንጌል 2:19 ጀምሮ በሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ከግብፅ ስደት ወደ ናዝሬት መመለስ ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ቅድስት ድንግል ማርያም በእናትነቷ፣ በእሺታዋና በአድማጭነቷ ልዩ ስለመሆኗ፣ ስደትን ችግርን፣ ጭንቀትንና መንከራተትን ያወቀችና የሌሎችም ስቃይ የሚገባት ርኅርኅት እናት በመሆኗ አሁን ላይ በአገራችን ያለው የሰላም እጦት ማለትም ጦርነት፣ ስደትና ወረርሽኝ በሽታን ተመልክታ እንድትለምንልን ማርያምን መያዝ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዮሐንስ ወንጌል ላይ ምእራፍ ሁለት ላይ የተገለጸውን እመቤታችን በቃና ሠርግ ላይ የነበረውን ጭንቀት አይታ ከልጇ ዘንድ መፍትሔ እንዳስገኘች ሁሉ ዛሬም “እሱ የሚላችሁን አድርጉ” በማለት እናታዊ ምክሯን ትለግሰናለች፤ ስለዚህም ልጇ የሚለንን ሰምተን በማድረግ ሰላምና ደስታን ከሚነሳን ነገር እፎይታን እንድናገኝና ማረፍ እንዲሆንልን፣ እንደማርያምም ታዛዦች መሆን እንዳለብን መክረዋል።

በተለየ መልኩ ስለአገራችን ሰላም መስፈን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰላምን እንድታሰጠን ወደ ልጇ እንድታቀርብልንም ሁልጊዜ እርሷን መያዝ እንደሚገባን አደራ ብለዋል።

የበዓሉ ጥቂት ፎቶዎች፦ 

43125