ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲወርድ ጸሎት አደረሱ።

በግጭት ምክንያት ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንበሰሜን ኢትዮጵያ፣ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ያስከተለው የዜጎች ሕይወት መጥፋት እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀል እንዲያበቃ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጽኑ መማጸናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተቀሰቀሰው ደም አፋሳሽ ግጭት አብቅቶ ዘላቂ ሰላም እንዲወርድ፣ በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በአገር ውስጥ እና ወደ አጎራባች አገር ሱዳን የተሰደዱ በአርባ ሺህ የሚገመቱ የቤተሰብ አባላትን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጸሎት ማድረጋቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊው ጨምሮ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእርስ በእርስ ግጭት፣ መፈናቀል እና የሕይወት መጥፋት

ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሠራዊት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሠራዊት መካከል የሚካሄደውን ግጭት አስመልክቶ የሚወጡ ዘገባዎችን ቅዱስነታቸው በቅርብ የሚከታተሉ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊው አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውቀዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንቸስኮስ፣ ጥቅምት 29/2013 ዓ. ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልዕክታቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በጦር መሣሪያዎች የታገዘ ግጭት ቆሞ፣ ሁለቱም ወገኖች በወንድማዊ መከባበር በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ፣ በዜጎች ላይ የሚደርስ የሕይወት መጥፋት ተወግዶ በአገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ በማለት ጥሪ ማቅረባቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሃላፊው አቶ ማቴዎ ብሩኒ አስታውሰዋል። 

የግጭቱ መንስኤ ሲፈተሽ

በሰሜን ኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው ግጭት ዋና ምክንያቱ በአገሪቱ ውስጥ ነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም. ይካሄል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ለሌላ ጊዜ መራዘሙ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ድንበር በማስከበር ተልዕኮ ላይ በነበረው የፌደራል መከላከያ ሠራዊት ላይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሠራዊት ያደረሰው ጥቃት መሆኑን፣ የአፍሪቃ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት ወ/ሮ አና ቦኖ ከቫቲካን ሬዲዮ ጣሊያንኛ ቋንቋ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አስረድተዋል።

ግጭቱ በአካባቢው ነዋሪ ላይ ያስከተለው ቀውስ

የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ ልዩ የልዑካን ቡድንን ተቀብለው ያነጋገሩት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ለልዑካኑ እንዳስረዱት፣ ግጭቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሚገኙት የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ መንግሥታቸው ከፍተኛ ጥንቃቄን እንደሚያደርግ፣ በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው ወደ አጎራባች አገር ሱዳን የተሰደዱ ቤተሰቦች ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው በሰላም እንዲመለሱ፣ ከተመለሱ በኋላም ሰብዓዊ ዕርዳታን በበቂ ሁኔታ የሚያገኙበት መንገድ የሚመቻችላቸው መሆኑንም ለልዑካኑ ጨምረው አረጋግጠውላቸዋል።

በሁለቱ ወገኖች ማለትም በፌደራል መንግሥት ሠራዊት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ሊያበቃ መቃረቡ በሚነገርበት ሦስተኛው እና የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ፣ የመቐለ ከተማ በማዕከላዊ መንግሥት የመከላከያ ኃይል ሠራዊት መከበቧ ተሰምቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ባወጣው ዘገባ መሠረት ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ በግጭቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ አጎራባች አገር ሱዳን የተሰደዱትን ጨምሮ ከኤርትራ ጋር ወደሚያዋስኑ አካባቢዎች የተሰደዱት ሰዎች ቁጥር ወደ አርባ ሽህ የሚጠጋ መሆኑን ገልጾ፣ ባሁኑ ጊዜ ይህን ለሚያህል ሕዝብ በቂ ምግብ እና መጠለያ ለማቅረብ ድርጅቱ ውስን አቅም ያለው መሆኑን አስታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት እና የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ፕሬዝደንት፣ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ. ም. ባወጡት መግለጫቸው “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው፣ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” (ማቴ. 5 ፥9) የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ በማስቀደም እንደገለጹት “በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የዘለቀውን አለመግባባት ለማርገብ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሃይማኖት አባቶች፣ በሃገር ሽማግሌዎች እና በሚመለከተቸው ወገኖች የተደረገው ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ በመካከላቸው እየተባባሰ የመጣው አለመግባባት ወደ ግጭት ደረጃ ላይ መድረሱ እጅጉን እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ግጭት በቀላሉ እንዳይመለከተው፣ ይልቁንም በአንክሮ በመመልከት እና ለመንግሥታት ብቻ የማይተው መሆኑን በመገንዘብ ዕርቅ እንዲሰፍን፣ ሕዝባዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ሰላም እና ጸጥታም እንዲረጋገጥ ሁሉም በባለቤትነት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅበታል” ማለታቸው ይታወሳል።