የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክበረ በዓል

for webየበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክበረ በዓል በዛሬው ዕለት ጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በቅድስት መንበር በሚገኘው ጳጳሳዊ የኢትዮጵያ ኮሌጅ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል። በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በሥርዓተ ዋይዜማ፣ ዛሬም በሥርዓተ ማኅሌት እና በመሥዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ውሏል። የዘንድሮው የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ ክብረ በዓል በቅድስት መንበር በቅድስት መንበር የሚገኘው ጳጳሳዊ የኢትዮጵያ ኮሌጅ 100ኛ ዓመት መዝጊያ ሆኖ በድርብ በዓል ተከብሯል። በወቅቱ የኮቪድ19 ወረርሺኝ ምክንያት ዘንድሮ እንደወትሮው በሮም የሚገኙ ገዳማት መነኮሳንና ካህናት እንዲሁም ምዕመናን መገኘት ባይችሉም በሮም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቆሞስ ክቡር አባ ተሻለ ንማኒ ቁምስናውንና ምዕመናንን በመወከል ከኮሌጁ ካህናት ጋር በመሆን መሥዋዕተ ቅዳሴውን አሳርገዋል።

በመሥዋዕተ ቅዳሴው ላይ የዕለቱን ቃለ ምዕዳን ያሰሙት ክቡር አባ ቶማስ ቅዱስ እስጢፋኖስ ዘአቢሲኒያ ገዳም  ከ500 ዓመት ያላነሰ ዕድሜ እንዳለው አስታውሰው ነጋድያን ከሀገራችን ወደ ቅድስት ሀገር ያደርጉት የነበረ ሕያው የእምነት ምስክርነት ዛሬም ድረስ የሚያፈራ የእምነት ዘር መሆኑን አስገንዝበዋል። ቅዱስ እስጢፋኖስ ዲያቆኑ የካህናት ጠባቂ ነው በማለትም ካህናት በአማላጅነቱ እንዲታመኑ እና አብነቱን እንዲከተሉ መክረዋል።

በኩረ ሰማዕት ስለሆነ እርሱን እንመስል ዘንድ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ እንደተባለ ለምሥክርነት ተጠርተናል በማለት ሰማዕትነት የሌለው ክርስትና ጨው የሌለው ምግብ መሆኑን አመላክተው፤ የበኩረ ሰማዕታት የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል የልደትን በዓል ተከትሎ መምጣኡት ክርስትና በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚኖር እውነታ መሆኑን የሚያሳየን እንደሆነም አያይዘው ጠቅሰዋል።

በኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ የምስክርነት ሕይወቱን ደብዳቤ በደሙ የፈረመ ታማኝ አገልጋይ ነው። ቅዱስ እስጢፋኖስ ዝም ብሎ በሕይወት መኖር ይችል ነበር፤ ነገር ግን ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? በማለት ምስክርነት ከወንጌል ልብ ይሚፈልቅ ክርስትያናዊ ተልዕኮ መሆኑን በአጽንዖት አስገንዝበዋል።

ክቡር አባ ቶማስ በቃለ ምዕዳናቸው “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” የሚሉትን የዘመናችንን ቀኝ ዘመም አስተሳሰቦችን ጠቅሰው ክርስትና ከእነዚህ በተቃራኒው መቆም እንዳለበት ጠቁመዋል። እውነት በእኛ ሚዛን የሚለካ ሳይሆን በተገለጠው ዘላለማዊ ቃል፣ ይኸውም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የሚለካ ሐቅ ነው፤ እውነት ለነገሮች ያለን ግትርነት ሳይሆን በእኛ ስላለው ተስፋ ለሚጠይቁን ሁሉ በፍቅርና በገርነት የምንሰጠው ምስክርነት ነው ሲሉ አሳስበዋል።

በመጨረሻም የሀገራችንና የሕዝባችንን የሰላም መሻት ጠቅሰው በከፍተኛ ሁካታ ውስጥ ብንቆምም እንኳን የእግዚአብሔርን ድምፅ ለይተን መስማት ከቅዱስ እስጢፋኖስ እንማራለን በማለት እግዚአብሔርን ተስፋ እንድናደርግ መክረዋል።

የቅዱስ እስጢፋኖስ አማላጅነትና ምስክርነት ከእኛ ጋር ይሁን።

መልካም የበኩረ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል!

ሴሞ - ከሀገረ ሮሜ - ቫቲካን፣ ቅድስት መንበር