Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የክቡር አባ ኪዳነማርያም ተስፋ ሚካኤል ሲታዊ ዜና እረፍት

የክቡር አባ ኪዳነማርያም ተስፋ ሚካኤል ሲታዊ ዜና እረፍት

አርቲክልክቡር አባ ኪዳነማርያም ተስፋሚካኤል ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ ይኖሩበት በነበረው በጣልያን አገር ቫልቪሾሎ ገዳም ሆስፒታል ውስጥ የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ማረፋቸው ታውቋል።

መስከረም 24 1930 ዓ.ም. እንገላ (መረታ ሰበነ) በሚባል ቦታ ኤርትራ ውስጥ በቃልኪዳን ከተሳሰሩት ወላጆቻቸው አቶ ተስፋሚካኤል ነጉሠ ግርሙና ከወ/ሮ ሣራ እማን የተወለዱት አባ ኪዳነማርያም አራት ወንድሞችና አንዲት እህት የነበራቸው ሲሆን ሁለቱ ወንድሞቻቸውም እንደርሳቸው ካህናት ናቸው።

የዘርአ ምንኩስና ትምህርታቸውን ለመጀመር ጳጉሜ 3 1942 ዓ.ም. ወደ አሥመራ ሲታውያን ገዳም የገቡ ሲሆን፤ ከስምንት ዓመታት የትምህርት ዝግጅት በኋላ ለቀጣዩ የምንኩስናና የትምህርት ሕንጸት ወደ ጣልያን አገር ተላኩ። በሄዱበት ዓመትም በካዛማሪ ገዳም ልብሰ ምንኩስና ተቀብለው የተመክሮ ዓመት ጀመሩ፤ በመቀጠልም በዓመቱ የመጀመሪያ የምንኩስና መሐላን ፈጽመው፤ እዚያው ጣልያን ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፤ በትሪዙልቲ ገዳም ደግሞ የፍልስፍና ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በነበራቸው የመማር ሂደት ቀዳሚ ሆነው በመገኘታቸው ለላቀ የነገረ መለኮት ትምህርት ወደ ግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲ ተላኩ፤ በ1958 ዓ.ም. ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በነገረ መለኮት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ።

እየተማሩ በነበሩበት ወቅት እንደ ሲታዊ መነኮስ ማድረግ ይጠበቅባቸው የነበውን የመጨረሻ የምንኩስና መሐላ ጥቅምት 12 ቀን 1957 ዓ.ም. በካዛማሪ፤ እንዲሁም በ1965 ዓ.ም. የዲቁና ማዕረግን በደብረ ቅ. እስጢፋኖስ ቫቲካን በብፁዕ አቡነ አብርሃ ፍራንስዋ እጅ ተቀብለዋል። በዓመቱ ማለትም መስከረም 12 ቀን 1959 ዓ.ም. ከካርዲናል ትራልያ ማዕረገ ክህነትን በካዛማሪ ገዳም ተቀበሉ።

ከክህነት በኋላ በ1960 ዓ.ም. የእንግሊዘኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን ለማሳደግ ወደ አየርላንድ ተልከው ለሦስት ዓመታት በብቃት ከተማሩ በኋላ በ1962 ዓ.ም. ወደ አገራቸው ተመለሱ። በአሥመራ የዘርአ ምንኩስና ምክትል ኃላፊና መምህር ሆነው ጀምረው፤ በከረን የሚገኘውን ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ድረስ እንዲያድግ ትልቅ ሚና በመጫወትና በዚያም የእንግሊዘኛ መምህር ሆነው ለዓመታት አገልግለዋል።

በመስከረም 1972 ዓ.ም. አባ ኪዳነማርያም ወደ አዲስ አበባ ተመድበው በሾላ ቅ. ዮሴፍ ገዳም ኃላፊ ሆኑ። የገዳሙንም የትምህርት ቤቱንም ግንባታ በማገዝ ብዙ ያገለገሉ ሲሆን፤ በ1979 ዓ.ም. ከገዳሙ ኃላፊነት ተነሥተው የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ ተመደቡ። በዚያም እስከ 1983 ዓ.ም. አገለገሉ።

በ1983 ዓ.ም. ወደ አሥመራ ገዳም  ተጠርተው የገዳሙ ምክትል ኃላፊ ሆነው ተመረጡ። በመቀጠልም በጤና ምክንያት ይሰቃዩ የነበሩት ክቡር መምህረ ገዳም አባ እስጢፋኖስ ኃላፊነታቸውን ሲለቁ የማኅበር ጉባኤ አባ ኪዳነማርያምን ተተኪ አድርጎ መረጠ። ከዚህም በኋላ ለተከታዮቹ ዘጠኝ ዓመታት የኤርትራና ኢትዮጵያ ገዳማትን አስተዳድረዋል። ከዋናው የገዳም ኃላፊነታቸው በ1995 ዓ.ም. ከተነሡ በኋላ ለረጅም ጊዜ የገዳሙ ኃላፊ አማካሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ በመቀጠልም የጤናቸውን ሁኔታ ለመከታተል አመቺ ይሆን ዘንድ በጣልያን አገር በካዛማሪና በቫልቪሾሎ ገዳማት ሆነው በቅዳሴና በምስጢረ ንስሐ አገልግሎት እየተሳተፉ፤ 62 ዓመታት በምንኩስን፣ በክህነት ደግሞ 55 ዓመታትን ኖረው በ84 ዓመታቸው በሕመም ምክንያት በቫልቪሾሎ ገዳም ዓርፈው ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በካዛማሪ ገዳም ሥርዓተ ቀብራቸው ተከናውኗል።

እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ከቅዱሳን ጋር ይደምርልን!!

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።