Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ጸሎታችሁ ስለሚሰማ ሳትታክቱ በትዕግስት ጸልዩ!

ር.ሊ.ጳ ፍራንቼስኮስ ጸሎታችሁ ስለሚሰማ ሳትታክቱ በትዕግስት ጸልዩ አሉ!

Popeርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው ግንቦት 18/2013 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በጸሎት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ጸሎታችሁ ስለሚሰማ ሳትታክቱ በትዕግስት ጸልዩ ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በጸሎት ላይ ሥር ነቀል የሆነ ተቃውሞ አለ ፣ እኛ ሁላችንም ከምናደርገው ምልከታ የሚመነጭ ነው፤ እንጸልያለን ፣ እንጠይቃለን ፣ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ጸሎቶቻችን የማይሰሙ ይመስላሉ -የጠየቅነው - ለራሳችን ወይም ለሌሎች - አልተፈፀመም ብለን እናስባለን። የምንጸልይበት ምክንያት ክቡር ከሆነ (ለምሳሌ ለታመመ ሰው ጤንነት ምልጃ ወይም ጦርነት እንዲያበቃ የምንጸልይ) ከሆነ ፍጻሜውን የማያገኝ ይመስላል።“አንዳንዶቹም ልመናቸው ያልተሰማ ስለመሰላቸው መጸለይን ያቆማሉ” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2734)። እግዚአብሔር አባት ከሆነ ለምን አይሰማንም? እሱ ለሚለምኑት ልጆች ጥሩ ነገሮችን እንደሚሰጠን ማረጋገጫ የሰጠን (ማቴ 7፡10) ፣ ለምን ጥያቄያችን አይመልስም? በማለት ጥያቄ እናቀርባለን።

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ስለጉዳዩ ጥሩ ማጠቃለያ ይሰጠናል። “ለሰጠን ሁሉ ባጠቃላይ እግዚአብሔርን ስናወድስ ወይም ስናመስገን ጸሎታችን በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ይኑረው ወይም አይኑረው እምብዛም አያስጨንቀንም፣ በሌላ በኩል ደግም የልመናችንን ውጤቶች ማየት እንፈልጋለን። ከእውነተኛ የእምነት ተሞክሮ ጋር አለመኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ አስማታዊ ነገር የመለወጥ አደጋን እንድንጠብቅ ያደርገናል። በእርግጥ በምንጸልይበት ጊዜ እኛ እግዚአብሔርን የምናገለግለው ሳይሆን እርሱ እኛን እንዲያገለግለን የምንጠብቅበት ስጋት ውስጥ እንገባለን” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2735)። ይህ እንግዲህ ሁል ጊዜ ጸሎት የሚጠይቀው ነገር ነው፣ ክስተቶችን በራሳችን ዲዛይን መሠረት ለመምራት መፈለግ፣ ከራሳችን ፍላጎት ውጭ ሌላ እቅዶችን ያለመቀበል ጉዳይ ነው። ኢየሱስ በተቃራኒው የጌታን ጸሎት በማስተማር ታላቅ ጥበብ እንድናገኝ አድርጎናል። እሱ እንደምናውቀው በጥያቄዎች ብቻ የተሞላ ጸሎት ነው፣ ነገር ግን የምንናገረው የመጀመሪያዎቹ በሙሉ ወደ እግዚአብሄር የሚያቀኑ ናቸው። እነሱ የሚጠይቁት እቅዳችን እንዲሳኩ ሳይሆን ነገር ግን የእርሱ ፈቃድ በዓለም ውስጥ እንዲሰፍን ነው። “ስምህ ይቀደስ ፣ መንግሥትህ ትምጣ ፣ ፈቃድህ ትሁን” (ማቴ 6፡9-10) ለእርሱ መተው ይሻላል።

ሐዋርያው ​​ቅዱስ ጳውሎስ “እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም” (ሮም 8፡26) በማለት ያስታውሰናል። በምንጸልይበት ጊዜ ቃላቶቻችን በእውነት ጸሎቶች እንዲሆኑ እና እግዚአብሔር የማይቀበለው ስራ ፈት ንግግር ብቻ ሳይሆን ትሁት መሆን አለብን። እኛም እንዲሁ ለተሳሳተ ምክንያቶች መጸለይ እንችላለን -ለምሳሌ እግዚአብሄር እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ምን እንደሚል እራሳችንን ሳንጠይቅ ጠላትን በጦርነት ለማሸነፍ በማሰብ እንጸልያለን። በአርማዎች ላይ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” ብሎ መጻፍ ቀላል ነው ፤ ብዙዎች እግዚአብሔር ከእነሱ ጋር መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ ፣ ነገር ግን በእውነት እነርሱ ከእግዚአብሄር ጋር መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚሞክሩ ግን ጥቂቶች ናቸው። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መለወጥ ያለብን እኛ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን መለወጥ አንችልም።

ሆኖም የእዚህ ዓይነቱ አሳፋሪ የሆነ ነገር በእኛ ውስጥ መኖሩ እንደቀጠለ ነው-ሰዎች በቅን ልቦና ሲጸልዩ ፣ ከእግዚአብሄር መንግስት ጋር የሚዛመዱ ነገሮችን ሲጠይቁ ፣ እናት ለታመመ ልጇ ስትፀልይ ፣ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደማያዳምጥ ሆኖ ለምን ይታያል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በወንጌሎች ላይ በእርጋታ ማሰላሰል ያስፈልገናል። የኢየሱስ ሕይወት ታሪክ በጸሎቶች የተሞሉ ናቸው-በአካል እና በመንፈስ የቆሰሉ ብዙ ሰዎች እንዲፈወሱ ይጠይቁታል፣ ከእንግዲህ ወዲህ በፍጹም በእግሩ መራመድ ለማይችል ወዳጅ የሚጸልዩ አሉ ፤ የታመሙ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይዘው የሚመጡ አባቶች እና እናቶች አሉ… ሁሉም በመከራ የተሞሉ ጸሎቶች ናቸው። ለእርሱ “ማረን!” የሚል እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ተማጽኖዎች ይቀርቡለታል።

እኛ አንዳንድ ጊዜ የኢየሱስ ምላሽ ወዲያውኑ እንደ ሚከሰት እንመለከታለን፣ በአንዳንድ ሁኔታዎች ግን ሲዘገይ እንመለከታለን። እስቲ ስለ ሴት ልጇ ኢየሱስን ስትማጸን የነበረችውን ከነዓናዊቷ ሴት እንመልከት፣ ይህች ሴት ኢየሱስ እንዲሰማት ለብዙ ጊዜ መማጸን ነበረባት (ማቴ.15፡21-28)። ወይም በአራቱ ጓደኞቹ ታጅቦ የመጣውን ሽባ የነበረውን ሰው እናስብ፣ ኢየሱስ በመጀመሪያ ኃጢአቶቹን ይቅር ይላል፣ ከእዚያም በኋላ  ሰውነቱን ይፈውሳል (ማርቆስ 2፡1-12)። ስለዚህ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የችግሩ መፍትሄ በፍጥነት ሲሰጥ አንመለከትም።

ከዚህ አንፃር የኢያኢሮስ ሴት ልጅ መፈወስ ለየት ያለ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው (ማርቆስ 5: 21-33)። በጣም የቸኮለ አባት አለ፣ ሴት ልጁ ታመመች እናም በዚህ ምክንያት የኢየሱስን እርዳታ ጠየቀ። መምህሩ ወዲያውኑ ጥያቄውን ይቀበላል ፣ ነገር ግን ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሌላ ፈውስ ይከሰታል ፣ ከዚያ በኋላ ልጅቷ እንደሞተች የሚያመለክት ወሬ ተሰማ። መጨረሻው ይህንን ይመስል የነበረ ሲሆን ነገር ግን በምትኩ ኢየሱስ ለአባቷ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው (ማርቆስ 5፡ 36)። “ማመናችሁን ቀጥሉ” - ጸሎትን የሚያፀና እምነት ነው። እናም በእርግጥ ኢየሱስ ያችን ልጅ ከሞት እንቅልፍ አነቃት። ኢያኢሮስ ግን ለተወሰነ ጊዜ በጨለማ ውስጥ በእምነት ነበልባል በመመራት መሄድ ነበረበት።

ኢየሱስ በጌቴሰማኒ ለአብ ያቀረበው ጸሎት እንዲሁ ያልተሰማ ይመስላል። ወልድ በፍላጎቱ ይህንን ጽዋ ሙሉ በሙሉ መጠጣት ነበረበት። ነገር ግን ከስቅለቱ በኋላ ያለው ቅዱስ የሆነ ቅዳሜ የመጨረሻው ምዕራፍ አልነበረም፣ ምክንያቱም በሦስተኛው ቀን ትንሳኤ አለ፣ ምክንያቱም ክፋ መንፈስ እኛን የሚቀጣበት ቀን አለ፣ ነገር ግን ይህ የመጨረሻው ቅጣት አይደለም። ምክንያቱም ያ የእግዚአብሔር ተግባር ብቻ ነው ፣ እናም የሰው ልጆች በሙሉ የመዳን ናፍቆት የሚሟላበት ቀን ነው።

ምንጭ፦ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ጸሎታችሁ ስለሚሰማ ሳትታክቱ በትዕግስት ጸልዩ አሉ! - የቫቲካን ዜና (vaticannews.va)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።