የምንኩስና መሐላ በደብረ መድኃኔዓለም መንዲዳ

የምንኩስና መሐላ በደብረ መድኃኔዓለም መንዲዳ

Temporal vowሐምሌ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. አራት ሲታውያን ተመካርያንና ሁለት የመለኮታዊ ጥበቃ ተመካርያት የመጀመሪያ የምንኩስና መሐላቸውን፣ እንዲሁም ተመካሪ ሩፋኤል የተመክሮ ዓመት ለመጀመር ልብሰ ምንኩስና የመልበስ ሥርዓትን በመንዲዳ መድኃኔዓለም ቁምስና ዘሲታውያን ፈጽመዋል።

ብዙ ካህናት በተገኙበት መሥዋዕተ ቅዳሴ የመሐላቸውን ሥርዓት የፈጸሙት ወንድም ተመስገን፣ ወንድም ሙሉቀን፣ ወንድም በረከት እና ወንድም ኤርሚያስ ሲሆኑ ከመለኮታዊ ጥበቃ እህቶች ደግሞ እህት ቤተልሔም ማቴዎስና እህት ብርሃኔ ወልደመስቀል ናቸው። በመሥዋዕተ ቅዳሴ ስብከት ጊዜ ክቡር አባ ገብረመስቀል ሽኩር ባሰሙት ቃለ እግዚአብሔር፣ ከማቴ 11:25-11 ላይ ተመርኩዘው፤ በተለይም ቁ. 26 ላይ “አዎ! አባት ሆይ! ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗል” የሚለውን በመውሰድ፤ እለቱ እግዚአብሔር በመካከላችን ስለ መኖሩ የሚያሳየን ሥርዓት መሆኑንና በቤተ ክርስቲያናችንም እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚወስኑ ወጣቶችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገኙ የመሆን እውነታ ታላቅ ደስታ መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም የክርስትና ሕይወት የጥምቀትን ሕይወት በመኖር ፍጹም ድኻ፣ ታዛዥና ንጹሕ የክርስቶስን አብነት መከተል መሆኑንና ይህን ለመኖር መሐላ የሚያደርጉ ወጣቶችን ስናይ ለሁላችንም ለክርስትና ጥሪያችን ታምኞች እንድንሆን ግብዣነቱን አስታውሰዋል። ይህን መሰል የመሰጠት ጥሪ ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት ህልውና ታላቅ ተግባር በመሆኑ መንፈስ ቅዱስ ራሱ የዚህ ሁሉ አድራጊነትን አስረድተዋል።

የአቪላዋ ቅ. ቴሬዛ “ለእኔ እግዚአብሔር ብቻ በቂ ነው” የምትለውን እውነታ በመጥቀስ በብዙ ፈተና መካከልም ቢሆን ከዘረኝነት፣ ከጎሰኝነት እንዲሁም ከመከፋፈል ተለይተን ታማኝ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን እንድንኖር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በእለቱ ሥርዓት ላይ ክቡር አባ ባዘዘው በኢትዮጵያ የሲታውያን መነኮሳን ኃላፊ፣ ክብርት ሲስተር እልፍነሽ በኢትዮጵያ የመለኮታዊ ጥበቃ እህቶች ኃላፊ፣ ከሲታውያን ገዳማትና ከሀገረ ስብከትም የመጡ አባቶች፣ ከየገዳማቱ የተሰባሰቡ የመለኮታዊ ጥበቃ እህቶች፣ እንዲሁም የደብሩ ምእመናን የተገኙ ሲሆን፤ የደመቀና እግዚአብሔር የከበረበት እለት ሆኖ አልፏል።

photo2021-08-1310-28-30photo2021-08-1312-28-32photo2021-08-1311-36-06 photo2021-08-1312-28-39 photo2021-08-1310-28-28photo2021-08-1310-33-01