የቅዱስ በርናርዶስ ዓመታዊ ክብረ በዓል

st. Bernardየ2014 ዓ.ም. የቅዱስ በርናርዶስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ የቅዱስ ዮሴፍ ቁምስና በሲታዊያን ገዳም አባቶች እና በቁምስናው ምዕመናን ዘንድ በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል።  ቤተክርስቲያን የቅዱስ በርናርዶስን በዓል ስታከብር በተለይ በ 12ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩትን ጽሑፎቹን እና ስብከቶቹን እንዲሁም በ 1130 እ.ኤ.አ. በቤተክርስትያን መካከል ሊከሰት የነበረውን መለያየት ያስቀረበትን መንፈሳዊ ጥበብና መሠጠቱን ትዘክራለች።

እ.ኤ.አ. በ 1090 የተወለደው ቅዱስ በርናርዶስ በ 22 ዓመቱ ወደ ሲታውያን ገዳም ከመቀላቀሉ በፊት የመጀመሪያዎቹን ዓመታት በፈረንሣይ ዲጆን አቅራቢያ ይኖር ነበር። በርናርዶስ በወጣትት ዕድሜው በደንብ የተማረ፣ እንዲሁም  ስለ እምነቱ በጣም ፍቅር ስለነበረው እርሱ ወደ ሲቶ በመጣ ጊዜ ወንድሞቹን ፣ አጎቱን እና ብዙ ጓደኞቹን ለገዳም ሕይወት አሳምኗቸው ነበር። 

በርናርድ በመጀመሪያ ወደ ሲቶ ገዳም ሲገባ ለሦስት ዓመት ያህል በሲቶ ከቆየ በኋላ  በኋላ በሻምፓኝ ሀገረ ስብከት ውስጥ ሌላ ገዳም ለማቋቋም ከ 12 መነኮሳት ጋር ተላከ።  ገዳሙ ክላሪቫው (የብርሃን ሸለቆ) በመባል ይታወቃል። በዚሁ ገዳም ውስጥ ወጣቱ መነኩሴ በርናርዶስ የገዳሙ አበምኔት ሆኖ ሌሎች ታላላቅ ገዳማትን ለመትከል ችሏል። ዱስ በርናርዶስ በመላው አውሮፓ ጳጳሳት እና ፖለቲካ መሪዎች አማካሪ ነበር።

የቅዱስ በርናርዶስ መጠነ ሰፊ የነገረ መለኮት እና የመንፈሳዊ ጽሑፎቹ ትኩረት የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅር ላይ ያተኩራል።  እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ከፍቅር በመፍጠሩ የሰው ልጅ መዳን በተሰቀለው እና ከሙታን በተነሳው በክርስቶስ በኩል የተገለጠውን መለኮታዊ ፍቅር አጥብቆ በመያዝ የሚኖር እውነት መሆኑን ያስተምራል።

ቅዱስ በርናርዶስ በስብከቱ አድማጩን እንዲማርክ እና ሰውን ወደ ጸሎት እንዲመራ የእምነትን እውነት በግልፅ እና በተቀናጀ መንገድ በማቅረቡ ስኬታማ ነበር።

ቅዱስ በርናርዶስ ለእመቤታችን ጥልቅ ፍቅር ነበረው! በእመቤታችን ላይ ብዙ ስለፃፈ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም እመቤታችኝ በቤተክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያላትን ወሳኝ ሚና በመረዳቱ ፣ የገዳማዊ ሕይወት ፍፁም አምሳያ እና የክርስትና ሕይወት ሁሉ አምሳያ አድርጎ ይጠቅሳታል።

ቅዱስ በርናርዶስ እ.ኤ.አ. በ1153 ዓ.ም. ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ከተሻገረ በኋላ  እ.ኤ.አ. በ 1174 ቅድስናው በይፋ ታውጇል።

በሳምሶን ደቦጭ

1234567