ር. ሊ. ጳ ፍራንቼስኮስ በሃንጋሪና በስሎቫኪያ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በስሎቫኪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ
pope europe hungaryርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለቱን የመካከለኛው አውሮፓ አገሮች፣ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት እሁድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም ጀምረዋል። በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ያደረጉትን የሰባት ሰዓት ጉብኝት ፈጽመው በተመሳሳይ ዕለት ወደ ስሎቫኪያ ተጉዘዋል። ወደ ስሎቫኪያ መዲና ብራቲስላቫ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ከአገሪቱ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከሐይማኖት መሪዎች ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ በባሕል ልብስ የተዋቡ ሁለት ሕጻናት በአገሩ ባሕል መሠረት የዳቦ፣ የጨው እና የአበባ ስጦታ አቅርበውላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ ውስጥ በሚቆዩባቸው አራት ቀናት ውስጥ በርካታ ሐዋርያዊ ተግባራትን የሚያከናውኑ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለቱ፣ በፕረሶቭ ከተማ ውስጥ  በባይዛንታይን ሥርዓተ አምልኮ የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚካፈሉ እና በአገሪቱ ወደሚገኝ የሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ንግደት እንደሚያደርጉ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል። ከዚህም በተጨማሪ መጠለያ አልባ ሰዎች የሚስተናገዱበትን ማዕከል እንደሚጎበኙ እና ቀጥሎም ከወጣቶች ጋር የሚገናኙ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከስሎቫኪያ ካህናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያት ጋርም እንደሚገናኙ ታውቋል።
ከዚህ በፊት እ. አ. አ 2003 ዓ. ም የቀድሞ ር. ሊ. ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በስሎቫኪያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከእርሳቸው በኋላ አንድ ር. ሊ. ጳጳሳት ስሎቫኪያን ሲጎበኙ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሁለተኛ መሆናቸው ታውቋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ሁለቱ አገሮች ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከጣሊያን ውጭ የደረጉት 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሆነ ታውቋል።   

ምንጭ፦ ራድዮ ቫቲካን