Map St Joseph Cistercians

Top Panel

ልጇን ሁለት ጊዜ የወለደች እናት - ቅድስት ሞኒካ

CASTEL GANDOLFO, Italy, AUG. 30, 2009 (Zenit.org) - ር.ሊ.ጳ. ቤኔዲክቶስ 16ኛው የተለመደውን የሰንበት እኩለ ቀን መልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲያደርሱ ባለፈው ኀሙስ የተከበረችውን የቅዱስ አውጎስጢኖስ እናትን ማለትም የቅድስት ሞኒካን አብነታዊ ሕይወት በመንተራስ አስተምህሯቸውን አድርገዋል። ይህች ቅድስት የክርስቲያን ወላጆች ባልደረባ እንደመሆኗ መጠን ልጆች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማግኘት በሚያደርጉ ጥረት የክርስቲያን ወላጆች ለሚጫወቱት ሚና አመስግነዋል።

 

ወጣቱ አውጎስጢኖስ ክርስቶስን የተማረው ከእናቱ መሆኑን ር.ሊ.ጳ. ሲገልጹ "በመንፈሳዊነቱና በሞራላዊ ሕይወቱ ዘቅጦ በነበረበት ጊዜም ቢሆን እንኳ የእሷ የሕይወት መመሪያ ከርሱ ጋር ነበር" ካሉ በኋላ "ሞኒካ የልጇ ሕይወት እንዲለወጥ ጸሎት ማድረጉን አቋርጣ አታውቅም፤ ይህንንም ታዝበው በወቅቱ የታጋስተ ጳጳስ የነበሩት እናቱ የምታነባለት ልጅ በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊጠፋ አይችልም ብለዋት ነበር" በለዋል።

አውጎስጢኖስ ሕይወቱን ወደ ክርስትና መለወጥ ብቻ ሳይሆን ወደ አፍሪካ (አህጉሩ) ተመልሶ ለመመንኮስና ገዳማዊ ማኅበር መመሥረት መቻሉን በመግለጽ ራሱ ቅ. አውጎስጢኖስ ስለ እናቱ ሲናገር "ሁለት ጊዜ ነው የወለደችኝ" የሚለውን ሃሳብ አስታውሰዋል።

"የክርስትና ታሪክ በብዙ ቅዱሳኖችና ለጋስ የሆኑ ካህናትንና የነፍሳት እረኞችን ባበረከቱ ክርስቲያን ቤተሰቦች ያሸበረቀ ነው፤ እዚህ ላይ ሁለቱም ከቅዱሳን ቤተሰብ የሆኑትን ታላቁ ቅ. ባሲልዮስንና የናዚያንዜኑን ቅ. ጎርጎርዮስ ማስታወስ ይቻላል።" በማለት ለዚህ ዘመናችን ቅርብ የሆኑ ተመሳሳይ ቅዱሳን ቤተሰቦችን ጠቅሰዋል።

የአባትና እናትን ሚና በማስመልከት "ባልና ሚስት ራሳቸውን ለልጆቻቸው ትምህርት፣ ልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያገኙም አቅጣጫ በመጠቆም ለክህነትና ለምንኩስና ሕይወት መብቀያ የሚሆን የለማ መሬት ያዘጋጃሉ።" በማለት ገልጸዋል።

በመጨረሻም በክርስቲያናዊ የቃል ኪዳን ጋብቻና በድንግልና ሕይወት ምርጫ መካከል ያለውን ትስስር "በክርስቶስ ሙሽራዊ ፍቅር ውስጥ የጋራ ሥር አላቸውና ሁለቱም በጥብቅ የተቆራኙና አንዱ ሌላውን የሚያፈካ ነው" በማለት የዕለቱ አስተምህሯቸውን  ቡራኬ በመስጠት ደምድመዋል።


አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።