4. ምንኩስና በሂንዱዊዝምና በቡድሂዝም

4. ምንኩስና በሂንዱዊዝምና በቡድሂዝም

ምንኩስና በሂንዱዊዝም

ከክ.ል.በፊት ከ2500 ዓመታት ጀምሮ የተዘወተረው የሂንዱዊዝም ምንኩስናዊ ሕይወት ለጥንታዊው ምንኩሳንዊ ሕይወት ዐቢይ ምስክር ነው። በዚህ ምንኩስና ወንዶችም ሴቶችም በየጎራቸው የመንፈሳዊ ሕይወት ጫፍ ላይ መድረስ በሚል ዓላም ይመነኩሱ ነበር። የአምላካቸውን ነገር ለማስተንተን ዓለምን ከመከተል ተቆጥበው ራስን በማያወሳስብ የአኗኗር ሁኔታ ነገሮችን በመመነን ያለ ጋብቻ ይኖሩ ነበር። ይህም አኗኗራቸው ራስ ወዳድ ወይ የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚፈልጉ ያለመሆናቸውን ያሳይ ስለነበር፡ በኅብረተሰባቸው ዘንድ ይከበሩ ነበር። አንዳንድ መነኮሳን የአምላካቸውን አዘጋጀነት፣ አሳቢነት ተማምነው ምንም ሳይዙ /ያለንብረት/ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ ነበር። ሕዝቡም ለመነኮሳኑ ምግብንና የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማቅረብ ታላቅ ተግባር እንደሆነ ይቆጠር ነበር። እነዚህ መነኮሳን ለምስጋና ሆነ ለመዋረድ እንዲሁም ለተድላም ሆነ ለስቃይ ግድ የለሽ ሆነው ይኖሩ ነበር። የተለየ ዓይነትም የፀጉር አቆራረጥ ነበራቸው።

መነኮሳኑ ከተወሰኑ ነገሮች ለመቆጠብ /ለመራቅ/ መሐላ ያደርጉ ነበር። መሐላቸው ከሚያካትታቸው ነገሮችም ውስጥ ለመጠጫ ከሚያገለግል ኩባያ፣ ከሁለት ልብሶችና የሕክምና መገልገያ በስተቀር ምንም የግል ንብረት እንዳይዙ፤ ተቃራኒ ጾታን ከመመልከት፣ ከማሰብና በአንድ ቦታ አብሮ ከመገኘት መከልከል፣ ምግብን ለደስታ ምንጭ አድርጎ ያለመመገብ፣ በማንኛውም ሁኔታና መልክ የገንዘብ ወይም ውድ የሆኑ ነገሮች ባለቤት ያለመሆን ብሎም ያለመንካት የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ቡድሃዊ ምንኩስና

ወንዶችና ሴቶች መነኮስንን የሚያቅፈው የቡድሂዝም የምንኩስና ሕይወት የተመሠረተው ከክ.ል. በፊት ከ500 ዓመታት አስቀድሞ ጋውታማ ቡድሃ ማለትም የቡድሂዝም መሥራች በሕይወት በነበረበት ዘመን ነው። ይህ ምንኩስና ሲጀመር ምነናዊና ብሕትውናዊ ገጽታዎች ነበሩት። በጣም ጥቂት ነገሮች ካልሆነ በስተቀርም ንብረት አይዙም። ያልመነኮሱ አማኞች ለነዚህ መነኮሳን ዕለታዊ ምግባቸውንና አስፈላጊም ከሆነ መጠለያ ያዘጋጁላቸው ነበር።

ከቡድሃ ሞት በኋላ ይህን የምንኩስና አኗኗር ከብሕትውና ወደ ማኅበራዊ ምንኩስና ተለውጦ መነኮሳን በኅብረት መኖር ጀመሩ። ለዚህም እንዲያግዛቸው የተለያዩ ደንቦችን አዘጋጁ። የቡድሂዝም መነኮሳን በመጀመርያ ደረጃ የቡድሂዝምን እምነት መመሪያና ሥርዓት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ከሌሎች አማኞች የሚለያቸው በመሆኑ ጋብቻ አይፈጽሙም። በሕይወታቸውም ለሌሎች ዓለማውያን አብነታዊ መሆን አለባቸው። በዚህም ምክንያት ለየት ያለ የአስተንትኖና ግብረገባዊ አኗኗር ይጠበቅባቸዋል፤ ምንም እንኳ ቢለያይም መነኮሳን በቀን አንድ ጊዜ የምግብ ሰዓት አላቸው። የተቀሩት አማኞች በበኩላቸው መነኮሳኑ ለነርሱ የምሕረት መመርያ እንደሆኑ ስለሚያምኑ አስፈላጊውን ነገር ለኑሮዋቸው ያሟሉላቸው ነበር።