3. ሸማኒዝም - ቅድመ ታሪክ ምንኩስና?

Category: የምንኩስና ሕይወት Written by Super User Hits: 2986
3. ሸማኒዝም - ቅድመ ታሪክ ምንኩስና?

በዓለም ታሪክ ከሚታወቁ ዓበይት ሃይማኖቶች በተሟላ መልኩ ሃይማኖት ተብለው ሊጠሩ ከሚችሉት ጥንታዊና ቀዳማዊ የሚባለው ሂንዱዊዝም ነው። በምንኩስና ሕይወት ታሪክም ጥንታዊ የምንኩስና ሕይወት የሂንዱዊዝም ምንኩስና እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል። ነገር ግን የተዋቀረና መልክ ያለው ሃይማኖት ከመኖሩ በፊት ለሂንዱዊዝምም ሆነ ለሌሎች ጥንታውያን ሃይማኖቶች ምንኩስና መሠረት የሚሆን አንደርዳሪ እውነታ ነበረ ወይ ብለን ብንጠይቅ በቅርብ የተደረጉ ጠለቅ ያሉ የታሪክ ዳሰሳዎች - አዎን ይሉናል።

ሸማኒዝም ይባላል ይህ ቢያንስ 10,000 ዓመታት ከክ.ል.በፊት እድሜ ያለው መንፈሳዊ ልምምድ። ይህ በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ ቅድመ ታሪክ ተብሎ በሚጠራበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለተወሰነ የቤተሰብ ሐረግ የተሰጠ ልዩ ጥሪ ተብሎ የሚታሰብ ነው። ይህ ጥሪ የነበረው ሰው ለልዩ አገልግሎት ከሕዝቡ የተለየ ይሆናል - በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አባባል በዓለም ይሆናል ግን የዓለም አይሆንም። ሸማን - ማለትም የዚህ ጥሪ ባለቤት የሆነ ሰው - በሕዝቡና በፈጣሪያቸው መካከል የመለኮታዊ ኃይል ክፍል ሆኖ የሚያገናኝ ሲሆን - ከካህናት ግን የተለይ ሚና ነበረ። አብዛኛውን ጊዜ ሸማን ለሕዝቡ የፈውስን ሚና ይጫወት ነበር።

አብዛኞቹ ሸማኖች ከማንኛውም ዓይነት ሥራ ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን፤ የሆነ ሙያ መሥራት ካለባቸውም ሕዝባቸው የተስማማበትና ያጸደቀው መሆን ነበረበት። በርግጥ ሸማኒዝም ማኅበራዊ ሕይወት እንደነበረው በግልፅ ታሪካዊ መረጃ ባይኖርም አኗኗራቸው ግን ማኅበራዊ ትስስር እንዳለው ግልፅ ነው። በዚህም በሰው ልጅ ውስጥ ላለው መንፈሳዊ ጥማት መልስ ለመሆን በሕዝባቸው መካከል ለሕዝባቸው ተለይተው መኖር ነበር።