6. ምንኩስና እና የአይሁድ ማኅበረሰብ

6. ምንኩስና እና የአይሁድ ማኅበረሰብ

በአይሁዳዊ ታሪክ ውስጥ የምንኩስና ሕይወት ይዘወተር እንደነበር አስረጂ የሚሆን ጽሑፍ የለንም። ነገር ግን እንደፍንጭ የሚጠቆመው የናዝራውያን ሕይወት ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ግን መሰል የምንኩስና ሕይወት የነበራቸው አሴናውያን፣ ቴራፐውት እና የቁምራን ማኅበረሰብ የሚባሉ ነበሩ።

ከአይሁዳውያን ወገን አሴናውያን የሚባሉ በአዲስ ኪዳን እንዴት ሳይጠቀሱ እንደቀሩ የሚገርም ነው። ምክንያቱም የነበሩበት ጊዜ ከ2ኛ ክ.ዘ. ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ 2ኛው ክ.ዘ. ከክርስቶስ በኋላ ነው። ይኖሩ የነበሩትትም በፖለስቲና (በሙት ባሕር አካባቢ) በሶሪያ ሲሆን ቁጥራቸው እስከ አራት ሺህ ይደርስ ነበር ይባላል። አሴናውያን ተጋድሎን በበለጠ የሚያዘወትሩ በውንድማማነት የሚኖሩ ሰዎች ነበሩ። በብዙ ወገኖችም የተለያዩ /የተከፋፈሉ/ ነበሩ። አንዳንዶቹ ደጋጎች አንዳንዶቹ ዝምተኞች የድሮ ቅዱሳን ወይም ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ንጹሐን አዕምሮ አንዳንዶቹ ደናግል ሌሎች መጠነኞች ወይም ትክክለኖች የሚባሉ ነበሩ።

የእነዚህ የተለያዩ የአሴናውያንወገኖች ዋናና መሠረታዊ መምሪያቸው እግዚአብሔርን ማፍቀር፣ በጎ መንፈሳዊ ኃይላትን ማፍቀርና የሰው ልጆችን ማፍቀር የሚል ነበር። ንብረታቸው /ገንዘብ፣ ሃብት/ የጋራ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱም ለእናይዳንዱ ይሰጥ ነበር። ቅዳሜንም በጥብቅ የሚያከብሩ፣ ጽዳትን በሚመለከት ጉዳይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉ፣ በቀዝቃዛ ውሃ የሚታጠቡ፣ ነጭ ልብስ የሚለብሱ፣ የማይምሉ፣ ከማኅበሩ ውጭ የማይበሉ፣ የእንስሳን መሥዋዕት የማይቀበሉ፣ መሣርያ /ሰው ማጥቂያ/ የማይታጠቁና የማይነገዱ ሰዎች ነበሩ።

የማኅበሩ አባሎች የሚሆኑት በሕፃንነት እድሜያቸው ወይም ትልልቆች ሆነው የዓለምን ነገር ሲመንኑ ነበር። አንድ ሰው የማኅበሩ አባል ከመሆኑ በፊት ለ3 ዓመት ተመክሮ ያደርጋል። ከዚህ በኋላ መሐላ ያደርጋል። መሐላውም ታዛዥ እንዲሆንና ምሥጢርንም እንዲጠብቅ ያስገድደዋል። መሐላውንም ካፈረሰ ከማኅበሩ ይባረራል። በማኅበር ደረጃ ሰውን መሸጥ ወይም ባርነትን ለመቃወም አሴናውያን የመጀመርያዎቹ ናቸው። ባሮች የነበሩትን በገንዘብ እየገዙ ነጻ ያደርጓቸው ነበር። አሴናውያን የሚሠሩት ሥራ እርሻና የእጅ ሥራ ነበር።

ከአሴናውያን ወገን የሆኑት ቴራፐውት የሚባሉት በግብፅ በእስክንድርያ ይኖሩ እንደነበር ፊሎ የተባለ ጥንታዊ አይሁዳዊ ጸሐፊ ያስረዳል። እንደ ፊሎ አጻጻፍ በአሴናውያንና በቴራፐውት ልዩነት ነበር፤ ቴራፐውት የሳምንቱን ቀኖች በተናጥል በአስተንትኖ ያሳልፉት ነበር። ቅዳሜ ግን ባንድነት ተሰብስበው ይጸልያሉ፣ ይመገባሉ፤ እንዲሁም ፍልስፍናዊ ውይይት በማድረግ ቀኑን ይዘጉት ነበር።

አሴናውያን ምንም እንኳ ከአይሁድነት /ከአሁዳውያን/ የሚያገናኛቸው ብዙ ነገሮች ቢኖራቸውም ከምሥራቅ ሃይማኖቶችም የወሰዷቸው ነገሮችም ነበሩ። ለምሳሌ ፀሐይን እንደ መለኮታዊ ነፀብራቅ ይቆጥሯት ስለነበር ጧት ስትወጣ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አቅንተው ጸሎት ያደርጉ ነበር።

የአሴናውያን መቋረጥ ወይም መጥፋት እንዴት እንደሆነ ምክንያቱ አልታወቀም። አንዳንዶቹ እንደሚሉት ግን በመጨረሻ ብዙዎች ወደ አይሁዳዊነት ወይም ወደ ክርስትና ገብተዋል ነው።

ምንም እንኳ በአዲስ ኪዳን ባይጠቀሱና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለእርሱ ባይነገርም፤ ክካህናት ወገን ስለነበሩ <የሳዶቅ ልጆች> ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ሳዶቅ በሰሎሞን ጊዜ የነበረ ሊቀ ካህን ነው።

መጥምቁ ዮሐንስ ከካህናት ወገን እንደነበር የታወቀ ነው። ሉቃስ 1፤15 መጥምቁ ዮሐንስ ያሳለፈው ሕይወትና ይኖርበት የነበረ በረሃ ከአሴናውይና ኑሮ ሕይወት ጋር የሚመሳሰል ነው። በረሃውም የሙት ባሕር አካባቢ ነው። አሴናውያን ይኽንን ቦታ የመረጡበት <በምድረ በዳ የጌታን አንገድ አዘጋጅ> የሚለውን የኢሳይያስ ቃል እንዲፈፀም ነው 40፤3። በዚህም ምክንያት መጥምቁ ዮሐንስ ከአሴናውያን ወገን ነበር ወይም ደግሞ ከነርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው ለማለት ይችላል። ለዚሁ ማስረጃ ቅዱስ ሉቃስ <ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ ለእስራኤልም እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ> 1፤80 ያለው ነው። ሕፃኑ የት እንዳደገ ወንጌሉ ግልፅ ባያደርግም በምድረ በዳ ነው - አንድ ሕፃን በምድረ በዳ በጽሞናና በብቸንነት ይኖራል ብሎ ማሰብ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። አሴናውያን ሕፃናትን፣ ትንንሽ ልጆችን ይቀበሉና ያሳድጉ ስለነበር ያደገው ከእነርሱ ጋር ነው ሊባል ይቻላል።

አሴናውያን በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ በበለጠም በወንጌል ያልተጠቀሱበት ምክንያት አንዳንዶቹ እንደሚሉት ከሆነ ምናልባት የወንጌልን ትምህርትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስላልተቃወሙ ሊሆን ይችላል። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የጌታን ትምህርት ይቃወሙ ስለነበሩ በወንጌል ብዙ ግዜ ተጠቅሰው ይገኛሉ። አንዳንዶቹም እንደሚሉት አሴናውያን ከኅብረተሰቡ የተለዩና የተነጠሉ ስለነበሩ ኅብረተሰቡ እስከዚህም ግምት አልተሰጣቸውም ይሆናል፤ ከሕግ እንደወጡ ቆጥረው ንቀዋቸው ከግምት ሳያስገቧቸው ቀርቶ ይሆናል የሚል አስተሳሰብም አለ።

ከአይሁዳውያንና ከቅዱስ መጽሐፍ ግንኙነት ያልነበራቸው እንደክርስትያን መነኮሳን ይኖሩ የነበሩ የግሪክ ፈልስፋ የፓይታጎረስ /580-500 ከ.ል.በፊት/ ተማሪዎች ወይም ተከታዮች እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ ይቻላል። ፓይታጎረስ ምንም እንኳ የሒሳብ ሊቅና ፈላስፋ ቢሆንም የሃይማኖት መሪና ግብረገብን ብዙ ያስተማረ፤ ማኅበርንም /በአንድነት መኖርን/ የመሠረተ ነበር። በደቡባዊ ኢጣልያ በፓይታጎረስ ስም የሚጠራ ትምህርት ቤት ነበር። እነዚህ የፓይታጎረስ ደቀመዝሙሮች ወይም ተማሪዎች የተመክሮ ዓመት ነበራቸው፣ ንብረታቸውም የጋራ ነበር። የነፍስ ወህኒ ቤት ነው ብለው ከሚያስቡት ከሥጋ ወጥመድ /ማሰሪያ/ ነፍስን ነፃ ለማውጣትና ለማላቀቅ ብዙ ተጋድሎ ያደርጉ ነበር። ጥበብን ለማግኘት እንዲሁ ጠንካራ ተጋድሎን ያደርጉ ነበር።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።