5. የምንኩስና ሕይወት በጄይኒዝምና በእስልምና

5. የምንኩስና ሕይወት በጄይኒዝምና በእስልምና

ጄይኒዝም

በጄይኒዝም ሁለት ዓይነት የምንኩስና ቅርንጫፎች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ዲጋምባራ የሚባል ሲሆን ምንም ልብስ የማይለብሱ ናቸው። ሆኖም ግን ራሳቸውን እርቃናቸውን እንደሆኑ አድርገው አያስቡም። ምክንያቱም አካባቢን/ ተፈጥሮን ለብሰናል ይላሉ። ይህንንም በማድረጋቸው ሰውነታቸውን ከድሎትና ምቾት እንዲሁም ከግል ንብረት እንደታደጉት ያምናሉ። ሁለተኞቹ ዓይነት መነኮሳን ሽቬታምባራስ ሲባሉ፡ ባለመልበስ እንደመጀመርያዎቹ አያምኑም። ብዙ ጊዜም ፊታቸው ላይ ጭምብል መሰል ነገር በማጥለቅ ይሸፈናሉ። ይህም ወደ ውስጥ ሲተነፍሱ ጥቃቅን ነፍሳትን በድንገት እንዳይገድሉ በማሰብ ነው።

 

እስልምና እና ምንኩስና

በመሠረቱ ሙስሊሞች በምንኩስና ሕይወት አያምኑም። ለዚህም በቁራን አላህ የምንኩስናን ሕይወት እንደ ሰው ሠራሽ ልማድ ስለገለጸው ነው ይላሉ። /ሱራ 52፡27/ ሆኖም <ሱፊ> ወይም <ጣሪቃ> የሚባሉ የእስልምና ክፍሎች በሌላ እምነቶች ምንኩስናዊ የሚባሉትን የሚመስሉ ተመሳሳይ አኗኗሮችን ያበረታታሉ። ከነዚህም ውስጥ <<ዴርቪሽ>> የሚባልት በድህነት ለመኖር መሃላ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ በምነና እና በልመና ሲኖሩ አንዳንዶቹ ደግሞ ተራ የሆነ ሥራን በመመረጥ ይተዳደራሉ፤ ቤተሰብ ያላቸው ሲሆኑ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት መኖር ይጠበቅባቸዋል። ይህ <ጣሪቃ> የሚባለው ምንኩስናዊ መሰል የሆነ እስላማዊ የአኗኗር ዘይቤ በ8ኛው ክ.ዘ. የተጀመረ ሲሆን በ13ኛው ክ.ዘ. በጣም ያበበት ጊዜ ነበር። በዘመናችንም በሰሜን አፍሪካ፡ በመካከለኛው እስያ፣ በቱርክ፣ በዓረቢያና በፓኪስታን በመስፋፋት ላይ ነው።

 

የሰው ተፈጥሮና የምንኩስና ሕይወት

የሰው ልጅ ሰው መሆኑን ማወቅ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ራሱንም ሆነ በዙሪያው ያሉ ነገሮችን ተፈጥሮ ለማወቅ ጥረትን ያደርጋል። ይህ ጥረት በውስጡ ለሚነሡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስን ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን እያበዙበት ይሄዳሉ። ስለዚህም ቶሎ የሚረዳው ነገር ቢኖር ቁሳዊ ነገሮችም ሆኑ የራሱ ማንነት የሕይወት ጥያቄዎችን ለመመለስ አቅመ ቢስ መሆናቸውን ነው። አንዳንዴም ሰው የሕይወት ጥያቄው በሥጋዊ ምኞት፣ በእውቀት፣ በሃብት ወይም በሥልጣን እና በመስል ነገሮቻቸው መልስን የሚያገኝ መስሎት በእድሜው ይዳክራል፤ ማንነቱንም ያባክናል። ተስፋ አድርጎ መልስ ይሆኑኛል ብሎ የሚጓጓላቸው ነገሮች ጋር ሲደርስ ይበልጥ ባዶ ፍጡር መሆኑን ሲነግሩት፤ ሰው ርካታንና የማንነቱን ሙላት ጠለቅ ባለ ዓላማ ውስጥ እንደሚገኝ ያየዋል። ስለዚህ በዘመናት ሂደት ወይም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ሰው ሕይወቱን ይሞላልኛል ብሎ ላመነበት ዓላማ ማንነቱን መስጠቱ የተለመደ ክስተት ነው። ምክንያቱም የሰው ሕይወት ቁምነገሩ ኖሮ ማለፉ ብቻ ሳይሆን በዓላማ መኖሩ ነው። ስለዚህ ከዚህ ሰዋዊ ዝንባሌ አንጻር ስናየው ሰው ብቻውን ገለል ብሎ በሆነ ዓላማ ለመኖር መወሰኑ የምንኩስና ሕይወት በተወሰነ መልኩ ተፈጥሮአችን ውስጥ አለ ለማለት ያስደፍራል።

ሰው በኖረባቸው ዘመናት ሁሉ በተለያየ ስምና ከብዙኃኑ ሕዝብ ተለይተው በአንድ ግብ የሚጓዙ የማኅበረሰብ ክፎሎች ነበሩ። በትዳር መተሳሰርን ትተው፡ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በመራቅ ከሃብትና ንብረት ይልቅ ለአንድ ዓላማ የሚኖሩ ጥንታውያን ግሪካውያን፡ ሮማውያን . . . ነበሩ። አንዳንዶቹ በሚያጠኑት የእውቀት ዘርፍ ፍጹም የሆነ እውቀትን /ጥበብን/ ለመገብየት፣ በያዙት ሙያ ጫፍ ላይ ለመድረስ /በስፖርት፣ በፖለቲካ/ ለብቻቸው የሚኖሩ ነበሩ። በፕሌቶ /አፍላጦን/ <<ሪፐብሊክ>> በሚለው መጽሐፉ እንደተገለጸው ለፍትሐዊና ሰላማዊ የሕዝብ አስተዳደር ራሳቸውን ከብዙኃኑ ለይተው - ወላጆቻቸውን እንዳያውቁ ተደርገው፣ ለ30 ዓመታት ያህል ልዩ ትምህርት እየተሰጣቸው፣ የግል ንብረት ሳይዙ በጋራ በመኖር ሙሉ ሕይወታቸውን ለፖለትካዊ ፍልስፍና የሚሰጡ ወንዶችና ሴቶች እንደነበሩ እናነባለን። እንዲሁም ከማኅበራዊ ሕይወትና ራስን በማግለል ሁሉን ነገር በመመነን ውስጣቸው ያገኙትን እውነት /እውቀት/ ሙሉ ለማድረግ የሚጥሩ ፈላስፎች እንደነበሩ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ4ኛው ክ.ዘ. መጀመርያ ላይ የነበረው ዲዮጋን የሚባል ግሪካዊ ፈላስፋ ምሳሌያዊ ነው። ዲዮጋን ሙሉ ምርምር ለማካሄድና በነጻነት ጥልቅ ሃሳቦችን ለማሰላሰል ያግዘው ዘንድ በማሰብ ውሃ ከሚጠጣባት ጣሳ በስተቀር ሁሉን ነገር መነነ። ይጓዝ የነበረውም ባዶ እግሩን ሲሆን ቀንም ሌሊትም የሚለብሳት አንዲት ካባ ነገር ብቻ ነበረችው። ዲዮጋን ፈላስፋው በዚህ ሁኔታ ሳለ አንድ ቀን አንድ ሕፃን ልጅ በአንድ የወንዝ ዳርቻ ሆኖ በእጁ ውሃ እየጨለፈ ሲጠጣ አየው። ይህንንም ሁኔታ ፈላስፋው በማስተዋል <<ይሄ ልጅ አዲስ ጥበብ አስተማረኝ>> በማለት ለመጠጫነት ይጠቀምባት የነበረችውንም ጣሳ እንደተዋት ይነገራል።

ይህንን እና መሰል ቅድመ ክርስትና ታሪኮችን ስናስተውል ገለል ብሎ ተፈጥሯዊ ስሜቶችን በመቆጣጠር ከነርሱ ባርነት ነፃ በመሆን የሆነ ዓላማን የመከተል ሕይወት በክርስቲያናዊ ምንኩስና ያልተጀመረና ሁሉን አቀፍ መሆኑን ያስረዳናል። በዚህም ምክንያት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በኋላም የተነሡ ሃይማኖቶች ዓላማቸውና መልካቸው ቢለያይም የየራሳቸው የምንኩስና ሕይወት አላቸው። ስለዚህም የክርስቲያናዊ ምንኩስናን ልዩ ተፈጥሮ ለማየት እንችል ዘንድ አስቀድመን የሌሎች ዐበይት እምነታት ምንኩስናዊ ገጽታ በጣም አጠር አጠር ባለ መልኩ እንመልከት።

አድራሻችን

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             http://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን contact@ethiocist.org ን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።