እኛ ማነን

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የምንገኝ ሲታውያን መነኮሳን በአገራችን በአዲስ አበባ፣ በመንዲዳ፣ በሆሣዕናና በጎንደር ገዳማት ሲኖሩን፤ ዓላማችንም በወንጌል ላይ የተመሠረተውን የቅዱስ አቡነ ቡሩክ ደንብን (The Rule of St. Benedict) በመከተል ክርሰቲያናዊ የጥምቀት ጸጋችንን በምልአት በሲታዊ ትውፊት መኖር ነው።.....

ይህም በምንኩስና ሕይወታችን፤ በግላዊም ሆነ ማኅበራዊ ጸሎትና ሥራ በቀጣይነት እግዚአብሔርን የመፈለግና የማመስገን ሕይወት ነው። በአጭር ቃላት ሕይወታችን “ጸሎትና ሥራ” (Ora et Labora) በሚለው ዘመን ጠገብ ትውፊታችን ይገለጻል።

ለዚህም ግብ መሳካት “ከክርስቶስ ፍቅር ምንም ነገር ያለማስበለጥ” የሚለውን ደንባችንን በማሰላሰል ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትና ምስክርነት በጸጋው ተማምነን ለመኖር የወሰንን ነን።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት መንፈሳዊ ትምህርቶች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ታሪክ፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ጸሎቶችና መንፈሳዊነትን ወደ ምንካፈልበት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ዜና ወደ ሚነገርበት፣ እንዲሁም በተቀደሰ ጋብቻም ሆነ በምንኩስና ሕይወት ወደ ቅድስና ጥሪ ለመጓዝ የሚያግዙ እውነታዎች ወደሚጋሩበት፣ የቅዱሳን ሕይወት፣ ሀብትና ትሩፋት ወደ ሚነገርበት፣ ባጠቃላይ የአምላካችን መልካም ዜና ወደሚታወጅበት ይህ ድረ ገጽ እንኳን በደህና መጡ!!

ከመ በኲሉ ይሴባሕ እግዚአብሔር!- እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።1ጴጥ.4:11

Map St Joseph Cistercians

Top Panel

የቅዱስ አቡነ ያቆዕብ ዩስጢኖስ ታሪክ

justin de jacobisቅዱስ አቡነ ያቆዕብ ዩስጢኖስ ታሪክ


ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ ዩስጥኖስ በ1800 እ.ኤ.አ በኢጣልያ ሳምፍል በተባለ መንደር ተወለዱ። በ1818 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. ወደ ላዛሪስት /ማኅበረ ልኡካን/ ገዳም ገቡ። እ.ኤ.አ. በ1824 ዓ.ም. ሢመተ ክህነት ተቀበሉ። በናፖሊ ከተማ ለድሆች ወንጌልን እያስተማሩም በመንፈስና በሥጋ እያገለገሉ ሳሉ በመስከረም ወር 1838 እ.ኤ.አ የፕሮፓጋንዳ ፊዴ (በቫቲካን የስብከተ ወንጌል ክፍል) ኃላፊ የነበሩ ሞሴኝር ቪቶ ጓሪኒ አቡነ ያዕቆብ ወደ ነበሩበት ገዳም በእንግድነት መጡ። አቡነ ያቆዕብ ከእንግዳው ጋር ስለ ስብከተ ወንጌል ሲነጋገሩ ቤተክርስቲያን ወደ ኢትዩጵያ የሚላኩ ሰባኪያን ትፈልጋለችና ኃላፊዎች ቢፈቅዱልዎት መሄድ ይፈቅዳሉን? ብለው ጠይቁኣቸው።አቡነ ያዕቆብም በልባችው ይመኙት የነበሩትን በግልጽ በጆሮቸው ሲሰሙ በደስታ ፈነደቁና "ኃላፊዎች ቢፈቅዱልኝ እኔ ዝግጁ ነኝ" ብለው መልስ ሰጧቸው።

ከዚህም በኋላ በደንቡ መሠረት ሂደቱ ከተሟላ በኋላ ሞንትዎ ሪ ከተባሉ ጓደኛቸው ጋር አብረው ከርኣሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጎርጎርዮስ 11ኛው ምርቃትና ቡራኬን ተቀብለው ግንቦት 24 ቀን 1839 ዓ.ም. እ.ኤ.አ ቺቪታ ቬኪያ ከተባለችው ሮም አጠገብ ከምትገኘው ወደብ ተነሥተው ጥቅምት 13 ቀን 1839 እ.ኤ.አ. ምፅዋ ገቡ። እዚያ እንደደረሱ በግንባራቸው መሬትን እየሳሙ "አምላኬ ሆይ የተቀደሰ ፈቃድህ ከሆነ እዚህ አገር በቅን መንፈስ አንተን የሚያመልኩ ሕዝብ ስጠኝ" ብለው ጸለዩ።

ለጥቂት ቀናት እዚያ እንደቆዩ በመርከብ ያመጡትን ዕቃ በበቅሎ ጭነው የሰምሃርን ምድረበዳ አቋርጠው ጥቅምት 15 ቀን 1839 እ.ኤ.አ ዓድዋ ከተማ ገቡ። እዚያም የሀገራችንን አለባበስ ለብሰውመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሄደው እንደ ሃገራችን ጫማቸውን አውልቀው ቆመው መዝሙረ ዳዊት በመድገም የሕዝባችንን ዝንባሌ ሳቡ አንዳንድ ቄሶችና ደብተራዎች ይህን ያህል በጸሎት የሚጠመድ ሰው የእግዚአብሔር ሰው መሆን አለበት ብለው ገመቱ። ቅ. ያዕቆብ ወደ አገራችን እንደገቡ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሆነው ወንጌልን ለመስበክ የመጡበትን ዋናዓላማ በተግባር ለማዋል በመጀመሪያ የከፈሉት ታላቅ መሥዋዕትነት ባጭር ጊዜ ቋንቋችንን ማጥናት ነበር። በእውነትም ጥቅምት 15 ቀን 1839 እ.ኤ.አ ዓድዋ እንደገቡ አራት ወር ጥር 26ቀን 1840 እ.ኤ.አ እውነተኛ የሐበሻ ሕዝብ ወዳጅ መሆናቸውን የሚገልጥ አስር የዓድዋ ምሁራን ሰዎች በተገኙበት የሚከተለውን ስብከት አሰሙ።

የቅዱስ አቡነ ያዕቆብ የመጀመሪያ ስብከት በዓድዋ

"የልብ በር አፍ ነው። የልብ ቁልፍ ቃል ነው። አፌን ስከፍትና ስናገር የልቤን በር እከፍትላችኃለሁ፤ የልቤን ቁልፍ እሰጣችኃለሁ፤ ኑና እዩ። መንፈስ ቅዱስ በልቤ ውስጥ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ትልቅ ፍቅር አሳድሮብኛልና።" አገሬ በነበርኩ ጊዜ በኢትዮጵያ ክርስቲያን መኖራቸውን አውቅ ነበር። አባትና እናቴን "መሄድ እፈልጋለሁ ባርኩኝ" አልኳቸው። እነርሱም "የት ትሄዳለህ አሉኝ"። እኔም በኢትዮጵያ ያሉ የተወደዱ ወንድሞቼን ለማየት እሄዳለሁ። በጣም የምወዳቸው መሆኔንም እገልጥላችዋለሁ" አልኩዋቸው። እግዚአብሔርም ጸሎቴን ሰማኝ፤ በጸጋውም የተወደዱ የኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ለማየት አበቃኝ። አሁን እናንተን ስላየሁና ስላወቅኋችሁ በጣም ደስ አለኝ። ጌታ ሆይ አሁን አንተን አመሰግናለሁ ፈቃድህ ከሆነ ውሰደኝ (ጥራኝ)፤ እግዚአብሔር ለአንድ ቀን ለሁለት ቀን ወይም ለፈለገው ቀን በሕይወት ከተወኝ ሕይወቴን ለእናንተ እሰዋለሁ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእናንተ ብሎ ነው በሕይወት የጠበቀኝ። እናንተ የሕይወቴ ጌቶች ናችሁ። አምላክ ለእናንተ ብሎ ሕይወት ሰጥኝ። ደሜን ከፈለጋችሁ ኑና ደም ሥሮቼን ከፍታችሁ ሁሉንም ውሰዱ። የእናንተ ነኝ፤ ጌቶቼ ናችሁናበእጃችሁ ደስ ብሎኝ እሞታለሁ። ደስ የሚላችሁ ከሆን መላው ሕይወቴን ለእናንተ እሰጣለሁ። በኀዘናችሁ ጊዜ በኢየሱስ ስም አጽናናችኋለሁ፤ ከታረዛችሁ ልብሴን እሰጣችኃለሁ፤ ከተራባችሁ ዳቦዬን እሰጣችኃለሁ፤ ከታመማችሁእጠይቃችኃለሁ።

"ላስተምራችሁ ከፈቀዳችሁ በላቀ ደስታ የማውቀውን ሁሉ አስተምራችኋለሁ። እኔ በዚህ መሬት አባትና እናት አገርም የለኝም፤አባቶቼ እናቶቼ ወንድሞቼና እህቶቼ እናንተ ናችሁ። በልቤ ውስጥ አምላክ እና የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ብቻ አሉ። እኔ የምትወዱትን ብቻ አደርጋለሁ፤ በሃገራችሁ እኖር ዘንድ ከፈለጋችሁ እኖራለሁ። አገራችሁን ለቅቄ እንድሄድ ከፈለጋችሁ እሄዳለሁ። በቤተ ክርስቲያናችሁ እንድናገር(እንድሰበክ) ከፈለጋችሁ እናገራለሁ፤ ዝምእንድል ከፈለጋችሁም ዝም እላለሁ። እኔ እንደ እናንተ (ቄስ) ነኝ። እንደ እናንተ አናዝዛለሁ፤ እንደ እናንተ እሰበካለሁ። እንድቀድስ ከፈለጋችሁ እቀድሳለሁ፤ ካልፈለጋችሁም አልቀድስም። ላናዝዛችሁ ከፈለጋችሁ አናዝዛችኃለሁ። እንዳትሰብክካላችሁኝ አልሰብክም። አሁን ከተናገርኋችሁ በኋላ ማን መሆኔን አውቃችሁ ልቤን በመክፈት የልቤን ቁልፍ በእጃችሁ ሰጥቼአለሁ። ማን ነህ ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ አንድ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወድ የሮም ክርስትያን መሆኔንእነግራችኋለሁ። ይህ እንግዳ ማን ነው ብለው ቢጠይቋችሁ ከእናቱና ከአባቱ ይልቅ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ብሎ ጓደኞቹን ዘመዶቹን ወንድሞቹን አባትና እናቱን ትቶ ፍቅሩን ለመግለጽ የመጣ አንድ የሮም ክርስቲያን ነው ብላችሁ መልሱ።"

በሦስት ወር ቋንቋችንን ካጠኑ በኋላ አብረዋቸው የነበሩትን ሁለት ወንድሞቻቸውን አንዱን በሰሜን ኢትዮጵያ ጎንደር አካባቢ ወንጌልን ለመስበክ ከዓድዋ እስከ አክሱም ድረስ ሸኙአቸው። "እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተውየሰማይ አባትችሁን እንዲያመሰግኑ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ"(ማቴ. 5:16) ብለው አጽናንተው በስብከተ ወንጌልና በበጎ አድራጎት ብርሃን የሚያብሩ ሁለት ካህናት ልከው ራሳቸውን በጸሎ{jcomments on}ትና በጾም ወንጌልን ለመስበክ አዘጋጁ።ዓድዋ ተመልሰው ትንሸ ቤት ተከራይተው ሲኖሩ በጸሎታቸውና በአኗኗራቸው ምሁራን አዛውንቶችና ወጣቶቸ እነደብተራ አማረ፣ ክንፉ፣ ደብተራ ኃይሉ፣ አባ ተክለሃይማኖት ንኡስ፣ አባ ተክለሃይማኖት ዓቢይ፣ ብጹዕ አባ ገብረ ሚካኤል፣ ወይዘሮ ለምለም.....ወዘተ የመሳሰሉ በዕውቀታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የአገራቸው ብርሃንና ኩራት የሆኑ ታላላቅ ሰዎችንም በመንፈስ ወለዱ።

በመጀመሪያ ወራት በ1847 ዓ.ም 20 የሚሆኑ ካቶሊካውያን ካህናትና ዲያቆናት ካፈሩ በኃላ በጥር 28 ቀን 1853 እ.ኤ.አ አቡነ ቢያንኬሪኒ መዓረገ ጵጵስና በሐላይ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተቀብተው እነ ብጹዕ አባ ገብረ-ሚካኤልና አባተክለሃይማኖትን ይዘው በቅድሚያ ስብከተ ወንጌልን ለማካሄድ ያሰቡትን ወደ መሃል አገር ወደ በጌምድርና ጎጃም ለመሄድ ጉዞአቸውን አቀኑ። ጎንደር እንደ ደረሱ በአፄ ቴዎድሮስና በአቡነ ሰላማ ትዕዛዝ መሠረት (በ19ኛው ክፍለ ዘመን) ተያዙ። ቤታቸውም ተበዘበዘ ከእርሳቸው ጋር የነበሩ እነ ብፁዕ አባ ገብረ ሚካኤል፣ አባ ተክለ ሃይማኖት ጐልዓ(ዓቢይ)፣ አባ ተክለ ሃይማኖት ዘዓድዋ (ንኡስ)፣ አባ ተስፋ ጽዮን፣ አባ ተክለሚካኤል፣ ዲያቆን ወልደገብርኤል፣ ደብተራ ፀጋይ፣ ደብተራ ኃይሉና ሁለት ሠራተኞች አብረው ወህኒ ቤት ገቡ። ከጥቂት ቀናት በኋላ አቡነ ያዕቆብ ሌሎቹን እንዲያጽናኑና እንዳያበረታቱ ብቻቸውን ተለይተው በወህኒ ቤት ገቡ። ከጥቂት ቀናት በኋላ በእምነታቸው ጸንተው ስለበረቱ ከባልደረቦቻቸው ለዩዋቸው። አቡነ ሰላማ ግን "ይህን ሰው አጥፉት" የሚል መልኣክት አስይዘው በበረሃ ውስጥ በበሽታ ይሞቱ ዘንድ በመተማ በኩል ከወታደሮች ጋር ላኩአቸው። ወታደሮቹም በበኩላቸው ሱዳን ድንበር እንደደረሱ ወደዚያ የሚሄዱ ነጋዴዎች አገኙና ለሡልጣኑ እንዲያስረክቧቸው መልእክቱንም ጨምረው አስረከቡዋቸው። ነጋዴዎቹም ያ በዓረብኛ የተጻፈውን መልእክት አንብበው "አባ! መልእክቱ በዛው በኩል አጥፉት" የሚል ነውና ሕይወትዎን ያድኑ ብለው ለቀቁአቸው፤ ከዚያ በድብቅ ጎንደር ተመልሰው በወህኒ ቤት ታስረው የነበሩትን ባልደረቦቻቸውን ጸፈው እዚያ መኖር ስላልቻሉ ወደ ሐላየ ተመለሱ።

ብፁዕ አባ ገብረ ሚካኤል በአፄ ቴዎድሮስ ሥር በእስር ቤት እንዳሉ በወሎ አውራጃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክብረ በዓል በሚከበርበት ዕለት ነሐሴ 23 ቀን 1855 እ.ኤ.አ በሰማዕትነት እንደሞቱ ስማቸው በሰማዕትነት መዝገብ ይገኛል።

ብፁዕ አባ ገብረ ሚካኤል በሰማዕትነት እንደሞቱ ሌሎቹም እንደተሰደዱ ቅዱስ አቡነ ያዕቆብና ባልደረቦቻቸው የተለሙትን ካቶሊካዊ ስብከተ ወንጌል ለመቀጠል ወደ ሰሜን አመሩ። በተለይ በሔቦና አካባቢውም (በኤርትራ) ስብከተ ወንጌል ሥራ ምክንያት በመንገድ እየተጓዙ መሞታቸው እየተቃረበ መሆኑን አውቀው በመንፈስ ከወለዷቸው ልጃቸው አንዱ አባ ዮሐንስ ተስፋጊዮርጊስ የተባሉን አስጠርተው ተናዘዙ። አባ ዘካርያስ ንኡስ የተባሉትም ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ፈጸሙላቸው። ልጆቻቸውን ጠርተውም "ካቶሊካዊ እምነትን አጠንክሩ ለሮም ር. ሊቀ ጳጳስት ታዘዙ፤ እርስ በርሳችሁም ከሐሜት ተጠበቁ፤ እንዲሁም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ" ብለው መከሯቸው። ተንበርክከው እያለቀሱ "የበደልኳችሁን ሁሉይቅር በሉልኝ" ብለው ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ልጆቻቸውን እየባረኩ በ60 ዓመታቸው በዓሳካራ (ዓሊገዶ ሒደለ) ድንጋይ ተንተርሰው ነሐሴ 31 ቀን 18690 ዓ.ም የደከሙለትን ሰማያዊ አክሊል ለመቀዳጀት የጻድቃን ዕረፍት አረፉ።ከመሞታቸው በፊት ለመነኮሳት ልጆቻቸው "ከሞትኩ በኋላ በሔቦ ቅበሩኝ" ብለው በተናዘዙት መሠረት በሔቦ (ኤርትራ) ተቀበሩ

የላዛሪስት ስደትና መመለስ

በጥር 22 ቀን 1895 እ.ኤ.አ ላዛሪስት ካህናት አኃው እና አኃት(ሲስተሮች) በጄኔራል ባራቲየሪ የተባለ ኢጣሊያዊ ትእዛዝ ከኤርትራ ተሰደዱ። ነገር ግን ላዛሪስት ከሀገራችን ተሰደው ከወጡ ከሁለት ዓመታት በኋላ አባ ኩልቦ፣ አባ ፒካርድ፣ አባግሩሶንና ወንድም (ኃው) ጁ ለሎንገች በሰኔ መባቻ በ1896 እ.ኤ.አ ጂቡቲ ደረሱ። በሐረር በኩል በእግርና በበቅሎ ተጉዘው አዲስ አበባ ገቡ። እዚያም እንደ ገቡም ዳግማዊ ምኒልክ ለራስ መንገሻ "እንደምን ሰነበትህ? ጌታ ይመስገን እኔ ደህናነኝ። እነዚህ የፈረንሳይ ካህናት አባ ዮሃንስ (ኩልቦ) ከነባልደረቦቻቸው ጓደኞቻችን ናቸውና ለአገራችንም ትልቅ አገልግሎት ስለሚሆን የነበራቸው ቤት ይመለስላቸው፤ በሰላም እንዲኖሩም ጠብቋቸው። በአጼ ዮሐንስ ፈቃድ የተሰጣቸውንመሬትም (ቦታም) ሰጥቻቸዋለሁ" ብለው የጻፉትን የመኖሪያ ፈቃድ ይዘው ከጅቡቲ እስከ ጎልዓ ድረስ ለስድስት ወራት 1ሺ700 ኪ.ሜ. የሚያህል ረጅም ጉዞ ተጉዘው በሚያዚያ 12 ቀን 1898 እ,ኤ.አ ጎልዓ ደረሱ። በብርቱ ግርፋትና ስቃይዓይናቸውን የታወሩ አባ ገብረማርያም "ከላዛሪስት ካህናት ጋር ደግመን እንተያያለን ብለን አልጠበቅንም ነበር። አሁን ግን ይህን ትንሣኤ ለማየት ላበቃን ቸሩ እግዚአብሔር ይመስገን" እያሉ ተቀቡሉዋቸው። በየጊዜው የሚነሣ ስደትና ችግር ባይታጣም ቅ. አቡነ ያዕቆብ የዘሩት ቃለ ወንጌል እያደገ ሄደ። ቅድስት ቤተክርስቲያንም አቡነ ያዕቆብ የደከሙለትን የወንጌል ፍሬ ተገንዝባ በ1902 እ.ኤ.አ የእግዚአብሔር አገልጋይ፣ በ1939 ዓ.ም ብፁዕ፣ በ1975 እ.ኤ.አ በብፁዕ አባታችን ርዕሰሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ ደግሞ ቅድስናቸው ለመላው ዓለም ታወጀ።

ቅዱስ አቡነ ያዕቆብ በተቀበሩበትና አጥንታቸው እስከ አሁን በክብር ተጠብቆ በሚገኝበት በሔቦ በስማቸው ታላቅ ደብር ታንጿል።

ቅዱስ አባታችን በሕይወታቸው ጊዜ የረገጡትን ሀገር ፤ የገቡበት ገዳምና ቤትን ሁሉ በየዋህነታቸውና በትሕትናቸው የሚያንጹ ነበሩ። ከዚህም በላይ የአንድነት መሠረትም ሆነውናል። "በኅብረት ኑሩ፤ እርስ በእርሳችሁ ታፋቀሩ፤ የሀገራችሁመብራት ሁኑ" ብለው የተውሉንን አደራ በበኩላችን ድርሻችንን በማበርከት አንድነታችንን እንግለጥ።

አማላጅነታቸውና ጸሎታቸው ዘወትር ከኛ ጋር ይሁን። አሜን።

ሰላማዊት የሺጥላ

ምንጭ

ፍቅርና ሰላም ወርኀዊ የካቶሊክ ጋዜጣ

ጥር 1989 ቁ(269) እና የካቲት 1989 ዓ.ም ቁ(270)

አድራሻችን

logo

                 ገዳመ ቅዱስ ዮሴፍ ዘሲታውያን

                    ፖ.ሳ.ቁ. 21902
                 አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ
             Phone: +251 (116) 461-435

              Fax +251 (116) 458-988

               contact@ethiocist.org

             https://www.ethiocist.org

 
 

ለድረ ገጻችን የሚሆን ጽሑፍ ካለዎ

1- የኢሜል አድራሻችንን webpageorganizers@gmail.comን ተጠቅመው አሊያም

2- ይህን ሲጫኑ በሚያገኙት CONTACT FORMበሚለው ቅጽ ላይ ጽሑፍዎን ለጥፈው ወይም 

3-facebook አድራሻችን https://www.facebook.com/ethiocist.org በግል መልእከት ይላኩልን

በተጨማሪም የሚያካፍሉት ጠቃሚ የድረገጽ አድራሻ ካለዎ ይላኩልን።   

መልእክት ከር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ

pope"ይቅርታን እና ምሕረትን ማድረግ የሰላማዊ ሕይወት መሠረት ነው"።

“ይቅር ማለት እና ምህረትን ማድረግ የሕይወት ዘይቤያችን ቢሆኑ ኖሮ፥ ስንት ጦርነት፣ ስቃይ እና መከራን እናስቀር ነበር! በግንኙነቶቻችን ሁሉ ይቅርታን የሚያደርግ ፍቅር ያስፈልጋል። ይኸውም በባል እና ሚስት፤ በወላጆች እና በልጆች መካከል እንዲሁም በአካባቢያችን፣ በማኅበረሰባችን እና በፖለቲካውም ማለት ነው። እንዲሁም ይቅርታን ለማድረግ ጥረት የማናደርግ ከሆነ፥ ይቅር አይባልልንም” ማለታቸው ተገልጿል።

ምንጭ - ቫቲካን ራድዮ አማርኛ ዝግጅት