ደማስቆ፤ ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ
ምዕራፍ 2
የቅዱስ ጳውሎስ መጠራት
ሀ. ደማስቆ፤ ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ
በሐዋርያት ሥራ ላይ ጳውሎስ ራሱ እንደሚተርክልን፤ ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ ድንገታዊ ፍጻሜ፣ ከአናንያ የቀሰመው ክርስቲያናዊ ኵስኮሳና ትምህርት (የሐዋ.9፤1) ጋር ተዛምዶ ነው የሚቀርበው። በሁሉም አቅጣጫ አመዛዝነህ፤ ይህ ሁኔታ የተፈጸመው በ35ዓ.ም. እንደሆነ አስቀድሞ ተገልጾዋል።
ይህ በደማስቆ መንገድ ያጋጠመው ፍጻሜ፤ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚታይ ብቻ ሳይሆን ሰፋ ባለ ሁኔት መታወስ ያለበት፣ በሁሉ ቦታ የሚነገር፣ የቅዱስ ጳውሎስ አስተሳሰብንና አኗኗር፣ ወንጌላዊ ስብከትና ሕይወት የሚመራና የሚተረጉም ነው ሊባል ይቻላል። ይህን የደማስቆ ፍጻሜ የሚመሰክሩ በገላ.1፤12-17፣ 1ቆሮ.9፤1፣ 15፤8,10፣ 2ቆሮ.4፤6፣ ፊልጵ.3፤7-12 ላይ ይገኛል። በፍልስጤም ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች የሰጡትን ምስክርነት ከዚህ ጋር ተዛምዶ መታየት አለበት። አሳዳጅ የነበረው አሁን ያሳድዳት ለነበረችው እምነት ሐዋርያና ሰባኪና መሆኑ ለሁሉም ያስገረመ ጉዳይ ነበር (ገላ.1፤23…፣የሐዋ.9፤1-19፣22፤4-16፣26፤9-18 አንብብ)።
ሳውል ወዲያውኑ በደማስቆ የስብከት እቅድ እንዳደረገ ነው የሚገመትው፤ ብዙ ሳይቆይ ግን ብቻውን ሆኖ ማስተንተንን መረጠ። ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በአይሁዳውያን ዘንድ እንደ ከዳተኛ ተቆጥሮ ችግር ሊፈጠርበት ይችላል፤ በክርስቲያኖቹ ደግሞ በጥርጣሬ ዓይንና በስጋት እንዳይታይና የማይታመን ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ቦታ የት እንደሆነ የማይታወቅ “ወደ ዓረብ” ሄዶ ተደበቀ (ገላ.1፤7)። በድፍኑ የምድረ በዳ አካባቢ የሚያመለክት ነው የሚመስለው። ይህ ጊዜ ለሳውል መንፈሳዊ ጥንካሬውና ዕድገቱ፣ መሠረታዊና በጣም ብዙ ሥራዎች የሠራበት ሳይሆን አይቀርም። ሕይወቱን አቅጣጫዋንና መንገዷን በተነገራት አዲስ መንገድ እንድትሄድ የተዘጋጀበት፣ በክርስትና መንገድ ለመጓዝ፣ የአባቶቹን ተስፋና መንፈሳዊ ትውፊትን በክርስትና ዓይን አንብቦ አስተሳሰቡንና አኗኗሩን ከመሠረቱ ለመቀየር ታጥቆና ቆርጦ የተነሣበት ወቅት ነበር።
ከዚህ በኋላ በደማስቆ ነው የምናገኘው (የሐዋ.9፤23)። በአይሁዳውያን መካከል ያደረገው ሁለተኛ የስብከት ሙከራ ተቃውሞ እንደገጠመው ነው የሚገመተው፤ በሚስጥርም አመለጠ። ትንሽ ቆየት ብሎ የሐዋርያት መሪ የሆነውን ኬፋን ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም (ገላ.1፤19፣ የሐዋ.9፤23-26) ሄደ። በገላትያ፤18 እንደምናነበው ይህ የመጀመርያ የሳውል ክርስትያናዊ እንስቃሴ ሦስት ዓመት የሚያክል ጊዜ ነው የወሰደው። ስለዚህ ወደ 38 ዓ.ም. አካባቢ ደረስን ማለት ነው። በኢየሩሳሌም እያለ ከጴጥሮስና ከባርናባስ የሚያስፈልገውን ሁሉ ቢያገኝም እንኳ፤ ከአይሁዳውያን በኩል ይመጣበት የነበረው ተቃውሞ ደስ ስላላለው፤ ወደ ትውልድ ሃገሩ ወደ ጠርሴስ እንዲሄድ በተደረገ ስምምነት መሠረት ከቂሳርያ ወደብ በመርከብ ተሳፍሮ ሄደ (የሐዋ.9፤29…፣ ገላ.1፤21)። ይህ ጉዞ ትርጉም ምን እንደሆነ ኢየሱስ ተገልጾ የተናገረው ይመስላል (የሐዋ.22፤17…)፣ በዚህ ዓይነት የጳውሎስ ሁለተኛው ክርስቲያናዊ ጉዞ ተጀመረ። “ወደ ሶርያና ኪልቂያ አገር ሄድኩ” ስለሚለው የሚታወቅ ነገር የለም። (ገላ.1፤21-24)
ይህ የደማስቆ ፍጻሜ በኋላ ለሚመጡት ሁኔታዎጽ ወሳኝ በመሆኑ፣ ጳውሎስ አልፎ አልፎ ከሚሰጠው ምስክርነት ጋር፣ ሊታወስ የሚገባው አስፈላጊ እንደሆነ ነው የሚያመለክተው። ምክንያቱም ሳውል በፊት ክርስቲያኖችን የሳድድ የነበረ ነው። (ገላ.1፤13,23፣ 1ቆሮ.15፤9፣ ፊልጵ.3፤6፣ የሐዋ.) ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ ምንም የሚያጠራጥር እንዳልሆነ በደማስቆ ከተማ ወይም ደግሞ በአካቢዋ ለሚኖሩ ይገልጽላቸዋል። (ገላ.1፤17፣የሐዋ.9፤3,8,10፣ 22፤5-10፤ 26፤12) ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ ዋና ይዘቱ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ መገለጽ ነው (2ቆሮ.4፤6፣ 1ቆሮ.9፤1፣15፤8፣ የሐዋ.9፤3፣ 22፤6,11፣ 26፤13)። ከደማስቆ ፍጻሜ በኋላ የጳውሎስ ሕይወት ምን እንደሚመስል ማየት አስፈላጊ ነው።
1. ብክርስቶስ ላይ የነበረው እምነት ሆነ ከክርስቶስ ጋር የነበረው አንድነት (ሱታፌ)፤ ለጳውሎስ ከዚህ የደማስቆ ፍጻሜ የሚመጣ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ በሚያንጸባርቅ ክብሩ ከተገለጸለት በኋላ በሕይወቱ ላይ የታየው ለውጥና ያደረገው እርምጃ ትልቅ ነገር ነው።
2. ጳውሎስ ፍጻሜውን በሚያስታውስበት ጊዜ “እግዚአብሔር ለልጁ ገለጸልኝ” ይላል (ገላ.1፤16)። “ገለጸልኝ” ይሚለው ቃል ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ የአምላክን ገሃዳዊና ወሳኝ ግልጸት የሚያሳይ ነው(ማቴ.10፤26፣ ሉቃ.17፤30፣ ሮሜ 8፤18፣ 1ቆሮ.3፤13 ተመልከት)። የጋረደውና ያሸነፈው ነጸብራቅ ምን ያመለክታል? ካልክ አዲሱና ልዩው መለኮታዊ ዓለም ወይም ሁኔታ በሕይወቱ እንደፈሰሰ፤ ሙሉ በሙሉ ውስጡ እንደሚገባ እንዳደረገው ያመለክታል።
3. በክርስቶስ የተፈጸመውን የአምላክ የድኅነት እቅድ ጳውሎስ ሊገባው የቻለው በደማስቆ ፍጻሜ ነው። ይህ ግንዛቤና የድኅነት መልእክት ደግሞ በጳውሎስ መልእክቶች (ትምህርት) ውስጥ ዋነኛና አስፈላጊ ነጥብ ነው። ይህ እንደዚህ ከሆነ ከገላ.3፤13 መጀመር ያስፈልጋል። “በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው” የሚለው ጥቅስ፤ ክርስቶስ ስለኛ እርግማን ሆኖ ከእግማን ሕግ አዳነን። ይህ ጥቅስ ከዘዳግም 21፤23 የተወሰደ ነው። ምናልባት ጳውሎስን ክርስቲያኖችን እንዲያሳድድ ከገፋፉት ምክንያቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም። የናዝሬቱ ኢየሱስ የውሸት መሢህ ነው ለሚለው ግምቱ፣ የውርደት ምልክት የሆነው መስቀል እንደ አንድ ማረጋገጫ ሆኖ ታየው። በደማስቆ መንገድ ላይ ግን፣ የተዋረደውና “የተረገመው” ክርስቶስ በክብርና በሚያንጸባርቅ ብርሃን ደምቆና አንጸባርቆ ታየው። አምላክ ይህንን እንደሚያይ አደረገው። የክርስቶስ ሞት እርግማን ሳይሆን፤ ልክ ክርስቲያኖች እንደሚረዱት እኛን የሚያድን፣ እርግማናችንን የሚደመስስ መሆኑ ለሳውልም ሳይቀር ተገለጸለት። ይህንን ግልጸት በገላ.2፤20 ለግላዊ ሕይወቱ በሚነካ ሁኔታ አድርጎ ያቀርበዋል፤ “በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው” በማለት በሕይወቱ ውስጥ የፈሰሰውን የአምላክ ፍቅር፤ ያገኘውን መበዠት (ቤዛ) ይታመናል።
4. በደማስቆ ፍጻሜ ከተገለጸልትና ከተረጋገጠለት ትልልቅ ነገሮች አንዱ፤ የአምላክ ጸጋ ትልቅነትና ችሎታ ነው። “እኔ አሁን የሆንሁትን የሆንሁት በእግዚአብሔር ጸጋ ነው።” (1ቆሮ.15፤10) በማለት ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል። እንደዚህ በማለት ደግሞ የጥሪው ምንጭና አቅጣጫ ምን እንደሆነ ያመልክታል።
· በክርስቲያኖች የሚፈራ የነበረ ልዩ ምንገድ ያዘ።
· የአምላክን ቤተክርስቲያን ማፍረስ የፈለገ (ገላ.1፤13) አሁን ከትንሣኤ ምስክሮች ጋር ቢቆጠር፣ አምላክ ራሱ የክርስቶስ መልእክተኛ ካደረገው (2ቆሮ.15፤10)፣ በከባዱ የስብከተ ወንጌል ሥራ ከሌሎቹ ለየት ብሎ ቢገኝ (1ቆሮ.15፤10)፣ የዚህ ሁሉ ዋና መሠረቱ ጸጋ፣ በግሪክ “ካሪስ” የሚለው ነው። “ካሪስ” በጥንታዊ ግሪክ ቋንቋ “ስጦታ፣ ተወዳጅነት፣ ሞገስ፣ ጥሩ ምኞት፣ ምስጋና” ያመለክታል። በአይሁድም ከሞላ ጎደል አንድ ነው። ጳውሎስ ከዚህ በመነሳት ነው ሊጠቀምበት የፈለገው።
5. ከሁሉም የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ጳውሎስ የሚያተኩርበት “የአምላክ ሥራ” የሚለውን ነው። እሱ የተቀበለው ምርጫ ከሁሉ በላይ ሰብአዊ ተግባር ነው። (ሮሜ 9-11) በሰው ፍላጎት ወይም ድካም የሚገኝ ሳይሆን፤ በምሕረት አምላክ የሚገኝ ነው። ስለዚህ ጳውሎስ የአምላክን የበላይነት መጀመርያ ደረጃ ይሰጠዋል። “ሊምረው የፈለገውን ይምረዋል” (ሮሜ 9፤18፣ ዘጸ.33፤14 አንብብ)። ጳውሎስ ወደ ክርስትና እምነት መግባቱ የአምላክ ሥራ እንደሆነ ነው የሚመለከትው። ኣሳቢው ሆነ ፈጻሚው ራሱ አምላክ እንደሆነ ነው የሚታመነው። እኛ ደግሞ “መመለስ” ወይም “ንስሐ” እንለዋለን። ጳውሎስ ይህንን የሚቀበለው አይመስልም፤ ምክንያቱም የሰው ስራ የሚያመልክት ስለሚመስል። ክርስቶስ ግን “ብጸጋው ስለሚጠራ” (ገላ.1፤15) በተለይ ደግሞ አሳዳጅ የነበረውን “ስለጠራው”፤ እዚህ ላይ ማንኛውም የሰው ስራ ቦታ የለውም። ጳውሎስ ከመወለዱ በፊት አምላክ በእቅዱ ውስጥ የነበረውን ነው አሁን በተግባር የሚያውለው ያለው (ሮሜ 1፤15)። ስለዚህ ፍጻሜው “የመመለስ” ወይም “የንሰሐ” ቢሆንም እንኳ ለጳውሎስ ግን ጥሪ ነው (ሮሜ 1፤15)።
6. በደማስቆ መንገድ ለጳውሎስ ገሃድ የሆነለት፣ በደንብ የተሰማውና የተረዳው ነገር ቢኖር ውድቀትና ኃጢአት ነው። እንደ ፈሪሳዊ እስራኤላዊ መጠን በአምላክ ቅድስናና በሰው ልጅ ኃጢአት ፍጹም ጥርጣሬ አልነበረውም። ሁለቱም እስራኤልዊ ውርሻው ነው። ቢሆንም ግን የኃጢአት ክብደትና ውጤት በደንብ አድርጎ የተገነዘበው አይመስልም ሊባል ይቻላል። ሕግን በመፈጸም ጽድቅ የሚገኝ ይመስለው ነበር እንጂ (ፊልጵ.3፤6)። በደማስቆ መንገድ ላይ ግን በጥልቅ የኃጢአት ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ እንደነበረ ተረዳው። የአምላክን መሢህ ተሳድቦና ደፍሮ፣ ማኅበሩን ሊደመስስ ሞክሮአል። ስለዚህ እነዚያ ቅኑና እርግጠኞች የሚመስሉት የነበሩ ሕሊናና ዝንባሌ፤ ወደ ትልቅ በደልና ተንኮል እንደሚያደርሱ ሊገነዘብ ቻለ። ይህ ደግሞ በሕይወቱ ሙሉ እንደ ከባድ ቀንበር ከሱ ጋር የሚሆን ነው። ሁልጊዜ በራስ መተማመንና መደገፍ እንደማይችል፣ ራሱን እንደ ትልቅ አድርጎ እንዳያስብ፣ “እኔ” የሚለው የተፈረካከሰበትና የፈረሰበት ፍጻሜ ነው። በአምላክ ፊት መመካትና መታበይ እንደማይችል ነው።
7. ሕግን በመፈጸም ብቻ የሚመረኮስ መንፈሳውነት በጳውሎስ ተቀባይነት እንድሌለው ማየቱ፤ እኛ ልናስተውልበት ይገባል። ይህ ደግሞ በደማስቆ መንገድ ያጋጠመውን ፍጻሜ በማሰብ ብቻ ነው። ያቺ ሰዓት የጳውሎስ ሁሉ ነገሩ የተለዋወጠበት ጊዜ ነው፤ ሐሳቡ፣ ዓላማው፣ ወዘተ . . .። እስከዛን ጊዜ ድረስ እንደ “ዋና አስፈላጊ ነገር” ይቆጥረው የነበረውን ወዲያውኑ “ዋጋ እንደሌለው” ተገነዘበ። ይህ ደግሞ “ጌታ ኢየሱስን ከማወቅ የበለጠ” ነገረ ስለሌለ ነው (ፊልጵ.3፤6)። ከደማስቆ ፍጻሜ በፊት፤ ሕይወቱ ድካም ላይ የተመሰረተች ነበረች፤ ሕግን ለመፈፀም ብዙ ይጥር ነበር። በዚህ ደግሞ በአምላክ ፊት ነቀፋ የሌለበት መስሎ እንዲገኝ ሞከረ፤ (ሮሜ 3፤6) አሁን ግን በሕግ ፈንታ ሌላ አዲስ ነገር ተተክቷል፤ ይህ ደግሞ ጳውሎስ “ጌታዬ” ብሎ የሚጠራው ክርስቶስ ነው።ያለፈው ሕይወቱ የተሳሳተና መታረም የሚገባው መሆኑን አውቆ፤ ስለዚህ የበፊት ሕይወቱን እርግፍ አድርጎ ተወው። እሱ በአዲስ መንፈስ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ አንድ መመለስ የነበረበት ጥያቄ ነበረ። ማለት ክርስትና ልክ የአይሁድ እምነት አንድ ክፍል ሆኖ ሊቀጥል ነው? ወይስ ሰፋ ያለ አድማስ አለው? በዚህ ምክንያት አይሁዳዊ ዝንባሌ ያለው የክርስትያን ሕግ አጠባበቅና በክርስቶስ ማመን - እነዚህን ሁለት ነገሮች እኩል ሊያደርግና ሊያዛምድ ሲሞክር፤ ለጳውሎስ ግን ይህ እኩል ሊሆንና ሊዛመድ የማይችል ነው። ሕግን በመፈጸም ይገኛል የሚባለው ጽድቅና የክርስቶስ የጽድቅ ሥራ በአንድ ላይ የማይሄድ ነው። “ሰው የሚጸድቀው የሙሴን ሕግ በመፈጸውም ከሆነማ፤ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው ማለት ነው።”(ገላ.2፤21)
8. ጳውሎስ የሚመካባት ተስፋ መሠረቷና ምንጯ የደማስቆ መንገድ ፍጻሜ ናት። በትንሣኤ ሙታን፤ እንዲሁም በአዲሲቷ ዓለም የነበረው ተስፋና ምኞት ፈሪሳዊ እያለ የወረሰውና የቆየው ትውፊት ሲሆን ሳለ (የሐዋ.23፤6-8)፤ አሁን ግን የአዲስ ዘመን (eone) ብርሃን በዓይኑ አየ። “በክርስቶስ ፊት ላይ ያንጸባረቀው የአምላክ ክብር”(2ቆሮ.4፤6) ተገልጾለታል። ይህ ግልጸት ማለት አንጸባራቂ የአምላክ ክብር ራእይ፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮ የተስፋው ቀብድ ሆነው። “. . . አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያህል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል።” (1ቆሮ.13፤12)
9. የጳውሎስ የሐዋርያዊ ተልእኮው መሠረት የደማስቆ መንገድ ነው። ስለ ጳውሎስ ጥሪ በሚመለከት መጀመርያ የተሰጠን ምስክርነት በገላትያ 1፤23 ይገኛል። ከላይ እንደተተረከልን፤ የጳውሎስ መጠራት በመጀመርያዎቹ ዓመቶች ውስጥ በአማኞች ዘንድ የታወቀ እንዳልነበረ፣ የክርስቲያን ማኅበሮችም እንደማያውቁት ይናገራል። “. . . ያ ቀድሞ ያሳድድ የነበረ ሰው፤ ያን ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን ይሰብካል” የሚል ወሬ ብቻ ይሰማ ነበር (ገላ.1፤23)። ስለዚህ የደማስቆ ፍጻሜ በክርስቲያን ማኅበሮች በተሰማ ጊዜ አምላክን እንደሚያመስግኑ እንደገፋፋቸው ያመለከታል (ገላ.1፤24)። አዎ! ያ ያሳድድ የነበረው፤ አሁን የዚህች እምነት ተካይዋ ብቻ ሳይሆን፤ ሰባኪዋም ሆነ። “ከተወሰነ ዓመቶች በኋላ” መስበክ እንደጀመረ ይነገራል (የሐዋ.9፤19)። ቀጥሎ ደግሞ “የምሥራቹን ቃል ማብሠር ግዴታዬ ስለሆነ የምመካበት ነገር አይደልም። እንዲያውም የምሥራቹን ቃል ሳላበስር ብቀር ወዮልኝ!” (1ቆሮ.9፤16) በማለት ግዴታ እንዳለበት ያመለክታል።
10. ጳውሎስ ስለ ቤተክርስቲያን የነበረው ግንዛቤና ትምህርትያሻሻለው፤ በደማስቆ መንገድ ላይ ከክርስቶስ ጋር ካደረገው ግንኙነት የሚመነጭ ነው። “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለው ቃል፤ ኢየሱስ ይሰደዱ ከነበሩት ማኅበረ-ክርስትያን ጋር አንድነቱን ስምምነቱን ይገልጻል። በክርስቶስና በተከታዮቹ መካከል ያለው አንድነት ለጳውሎስ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ስለ ማኅበረ-ክርስትና፤ ስለቤተክርስቲያን የነበረውን ግንዛቤ የሚያደለድል ነው። ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር አንድነትን ትፈጥራለች። ክርስቶስ ራስ ነው፤ እያንዳንዱ ክርስቲያን ደግሞ የአካሉ አባል ነው።
ስለዚህ ትምህርቱ፣ መልእክቱ፣ ሕይወቱ ሁሉ በድንገት በአምላክ የተጠራ ሰው ነው። የጳውሎስን ማንነት ለመረዳት ወደ ጠርሴው ወይም ኢየሩሳሌም መሄድ አያስፈልግም። የደማስቆን መንገድ ብቻ መመልከት በቂ ነው። ሌሎቹ መመዘኛዎች ማለት ግርካዊ ትምህርቱ፣ አስተዳደጉ፣ ባህሉ፣ አይሁዳዊ ውርሻው፣ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ትውፊቱ ሁሉ፣ ለአገልግሎቱና ለተልእኮው ዋና መሳሪያ ነው። ወሳኟና ዋናዋ ግን ሐዋርያው ራሱ “ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ ስላደረገኝ/ስለማረከኝ” (ፊልጵ.3፤12) ያለላት የደማስቆ መንገድ ናት።
ከዚህ በኋላ ያለውን ኃይልና ችሎታ በወንጌል አገልግሎት ላይ ሲያውለው ተገኘ። ኃይለኛ ቁጡ የሆነው ጠባዩ (1ቆሮ.4፤19-21፣ ፊልጵ.3፤2)፣ አንዳንድ ጊዜ ከሚያሳየው ከነበረው ቀዝቃዛና ሰላማዊ ጠባዩ (1ተሰ.2፤7-9) ጋር የሚቃረን አልነበረም (ገላ.4፤18-19)። ይህ ደግሞ ክርስትና ሰብአዊነትህን የሚያፍንና የሚጨቁን እንዳልሆነ የሚያሳይ ግሁድ ማስረጃ ነው። ሕይወቱና ሰብአዊነቱ ደግሞ ከኃይለኛ ስሜትና ግንዛቤ የተነሣ፣ “ስለ ሁሉም፣ ሁሉን” ሊሆን ራሱን የሰጠ የሐዋርያ ሕይወት ነው (1ቆሮ.9፤22)። ለመጀመርያ ከጴጥሮስ ጋር ያደረገው ግንኙነትም ልዩ ትርጉም ያለው ነበር (ገላ.1፤1)። ለጳውሎስ በኢየሩሳሌም ትገኝ የነበረችው የማኅበረ ክርስቲያን ሁኔታ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በውስጧ የነበረው አካሄድ የተረጋጋ ሳይሆን፤ ተጋድሮ የሞላበት፣ ወደ አዲስ አድማስ ያመለከተ ነበር። በዚህ ምክንያት ጉባኤ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ይህ ደግሞ ለጳውሎስ ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት፤ ሐዋርያዊ ሐላፊነቱ ታወቀለት፤ እንዲሁም በአሕዛብ መካከል የሚሰራው ስራ እንቅስቃሴ ተቀባይነት አገኘ። (ገላ.2፤1-10፣ የሐዋ.15) ይህ ደግሞ በ48/49 ዓ.ም. ነው የሆነው።
Last Updated (Friday, 10 July 2009 19:34)








Comments
የጌታ ምህረት ይብዛላችሁ Quote
RSS feed for comments to this post.