ንኡሳን ገጾች
Home (ቅድመ ገጽ) የካቶሊክ ቤ/ያን ት/ርተ ክርስቶስ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ

የሰው እግዚአብሔርን የመቀበል ችሎታ

ከአዲሱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የተወሰደ    ምዕ. 1 ቁ.27-35

1.የሰው እግዚአብሔርን መሻት

ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን መሻቱ በልቡ ተጽፎአል፤ ስለዚህ እግዚአብሔርም ሰውን ወደ ራሱ ከማቅረብ ከቶ አይቆጠብም። ሰው ያለ ማቋረጥ የሚፈልገውን እውነትና ደስታ ሊያገኝ የሚችለው በእግዚአብሔር ብቻ ነው።

የሰው ክብር ዋና መሠረቱ ከሁሉ በላይ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት እንዲኖረው መጠራቱ ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲነጋገር ለሰው የቀረበለት ጥሪ የደረሰው ሕልውናውን እንዳገኘ ወዲያውኑ ነው። ሰው ሕያው ሆኖ የሚኖረው እግዚአብሔር በፍቅር አማካይነት ስለፈጠረውና በፍቅረ አማካይነት በሕይወት ስለሚጠብቀው ነው።

በታሪክ ሂደት እስከ ዛሬ ድረስ ሰዎች እግዚአብሔርን መሻታቸውን በበርካታ ሃይማኖታዊ እምነቶቻቸውና ድርጊታቸው በጸሎታቸው፣ በመሥዋዕታቸው፣ በአምልኮአቸው፣ በአስተያየታቸው፣ ወዘተ. ሲገልጹ ኖረዋል፣ በዚህ ዓይነት ሃይማኖታዊ መግለጫዎች አንዳንዴ አሻሚነት ቢኖራቸውም በመላው ዓለም የሚስተዋሉ በመሆናቸው ሰው ሃይምኖታዊ ፍጡር ነው ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ይችላል።

(እግዚአብሔር) እርሱ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ቅመአያት ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩም አደረገ፤የሚኖሩባቸውን ዘመናትና ቦታዎች ሰጣቸው፣። ይህንንም ያደረገው ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈልጉና ምናልባትም ዳሰው እርሱ ማግኘት እንዲችሉ ነው፤ ሆኖም እርሱ ከእኛ ከእያንዳዳንቸን የራቀ አይደለም። “ሕይወት የምናገኘውና የምንቀሳቀሰው የምንኖረውም በእፉሱ ነውና።”

ነገር ግን ይህ “ቅርብና እጅግ አስፈላጊ የሆነ የሰውና የእግዚአብሔር ትስስር” ሊረሳ፣ ቸል ሊባል፣ ወይም ጭራሹኑ በግልጽ በሰው ዘንድ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል፤ የዚህ ዓይነት አመለካከቶች የተለያዩ መንስኤዎች ሊኖሯቸው ይችላል፤ እነርሱም በዓለም ላይ ባለው ክፋት ላይ ማመጽ ሃይማኖታዊ ማይምነት ወይም ግዴለሽነት፣ የዚህ ዓለም ሃብትና ምቾት፣ ከምእመናን በኩል በመጥፎ ምስላሌነት የሚመጣ እንቅፋት፣ ሃይምኖትን የሚጻረሩ አስተሳሰቦች፣ በመጨረሻም እራሱን ከፍርሃት የተነሣ ከእግዚአብሔር እንዲደብቅ እና ጥሪውን እንዲሸሽ ከሚያደርግ የኃጢአተኛ ሰው አመለካከት የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ።

“ጌታን የሚፈልጉ ልቦች ሐሴትን ያድርጉ።” ምንም እንኳን ሰው እግዚአብሔርን ሊረሳ ወይም ላይቀበለውም ቢመችልም እርሱ ግን፣ እያንዳንዱን ሰው እርሱን በመሻት ደስታን ሕይወትን ያገኝ ዘንድ መጣራቱን አያቋርጥም። ሆኖም ይህ እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረግ ፍለጋ የሰውን ልጅ ከፍተኛ ጥረት ጽኑ ፍላጎት “ንፁህ ልብ” እና እግዚአብሕIርን ስለመፈለት የሚያስተምሩ የሌሎችን ምስክርነት ይጠይቃል።

ጌታ ሆይ አንተ ታላቅ ነህ ከፍ ከፍም ልትል ይገባሃል፣ ኃይልህን ታላቅ ጥበብህም ወሰን የለውም። የፍጥረትህ ትንሹ አካል ሰው ሊያስመሰግንህ ይሻል። በርግጥም ይህ ሰው ፈራሽ ነው። የኃጢያትን ምልክትና አንተ ትዕቢተኛውን የምታቃወም መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም የተሸከመ ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ሰው ምንም እንኳ የፍጥረትህ ትንሹ አካል ቢሆንም ሊያመሰግንህ ይሻል። አንተው ራስህ በምስጋና ሐሴት እንዲያገኝ ታበረታታዋለህ። እኛን ለራስህ ሠርተኸናልና ልባች ባንተ እስኪያርፍ ድረስ ዕረፍት የለውም።

2. እግዚአብሔርን የምናውቅባቸው መንገዶች

በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሮ እርሱን ለማወና ለመውደድ የተጠራ፣ እግዚአብሔርን የሚሻ ሰው እርሱን የሚያውቅባቸው አንዳንድ መንገዶችን ያገኛል። እኒህ መንገዶች የእግዚአብሔር ህላዌ ማረጋገጫዎች ተብለው ይጠራሉ፤ ይህም በተፈጥሮ ሳይንሶች እንደሚታወቀው አይነት ሳይሆን “በሚጣጣሙና በአሳማኝ ክርክሮች” ላይ ተመስርቶ ስለ እውነታው እርግጠኛ እንድንሆን የሚያስችለን ነው።

እነኝህ እግዚአብሒርን ከፍጥረት አንጻር የመመርመር “ዘዴዎች” ሁለት አቅጣጫዎች ኣሏቸው። ቁሳዊው ዓለምና ሰብአዊው ፍጡር።

ዓለም ከእንቅስቃሴ፣ ከመሆን ፣ ከአጋጣሚና ከዓለም ሥርዓትና ውበት በመነሣት ማንም ሰው እግዚአብሔር የዓለም መነሻና መድረሻ የመሆኑን ዕውቀት መጨበጥ ይችላል።

ቅዱስ ጳውሎስ ስለ አሕዛብ እንዳለው፤ ስለ እግዚአብሒር ማወቅ የሚቻለው ሁሉ ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኣሳይቷቸውዋልና። ዓለም ከተፈጠረ ጀመሮ የርሱ ስውር ባሕርይ፣ ማለትም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ በፍጥረታቱ ሁሉ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታያል።

ስለዚህ ቅዱስ አውግስጢኖስም ይህን መጠይቅ ያቀርባል፤ እስቲ የመሬትን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የባሕርን ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ ራሱን በራሱ የሚያሠራጨውንና የሚሰበስበውን የአየር ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ የሰማዩንም ውበት ተጠራጠሩ፣ እስቲ እነዚን ሁሉ እውነቶች ተጠራጠሩ፣ ሁሉም “እኛ ውብ ነን” ይላሉ። ውብታቸውን ምስክርንተ ነው። እነዚህ ውበቶች ለለውጥ ተገዥዎች ናቸው። ለለውጥ ተገዢ ካልሆነው ከአንዱ ውብ አምላክ በቀር ማን ሊሠራቸው ይችላል?

ሰብአዊ ፍጡር። ለእውነትና ለውበት ካለው ግልጽነት፣ ለበጐ ምግባር ካለው ስሜት፣ ከነጻነቱና ከሕሊናው ድምፅ በሚመነጭ ለዘለላለማዊነትና ደስታን ለመላበስ ካለው ጉጉት የተነሣ ሰው ራሱን ስለ እግዚአብሔር ህልውና ይጠይቃል። በእነዚህ ሁሉ የራሱን ረቂቅ ነፍስ ምልክቶች ይረዳል። “ቁሳዊ ወደ ሆነው ብቻ የማይሸነሸነውና በውስጣችን ያለው የዘላለማዊት ዘር” ነፋስ ምንጩ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ዓለምና ሰው በውስጣቸው የመጀመሪያው ጥንስስም ሆነ መጨረሻ እንደሌላቸው፤ ነገር ግን መጀመርያና መጨረሻ በሌለው ራሱ በህላዌ እንደሚሳተፉ ይመሰክራሉ። ስለዚህ የፍጥረታት ሁሉ መጀመርያና መጨረሻ የሆነ ሰው ሁሉ “ ‘እግዚአብሔር’ ብሎ የሚጠራው” አንድ እውነት እንዳለ ሰብአዊ ፍጡር በብዙ መንገዶች መገንዘብ ይችላል።

የሰው ልጅ አእምሮ አካላዊ አምላክን ሊያሳውቀው የሚያስችል ብቃት አለው። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመፍጠር እንዲችል እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ለመግለጥና ሰውም በእምነት እንዲቀበለው የሚያስችል ጸጋውን ለመስጠት ፈቀደ። የእግዚአብሔር ሕልውና ማረጋገጫዎች አንድን ሰው ከእምነት እንዲደርስና እምነት ከአመክንዮ ጋር እንደማይፃረር እንዲያይ ያግዙታል።

ምዕራፍ ሁለት

ምስጢረ ንስሐ

የመዳን ምስጢራት


ክርስትያንነትን በሚያስገኙ ምስጢራት አማካይነት ሰው የክርስቶስን አዲስ ሕይወት ይቀበላል። ይህንንም ሕይወት “በሸክላ ዕቃ ውስጥ” ይዘነዋል፤ “በእግዚአብሔር ዘንድ ከክርስቶስ ጋር እንደተሰውረም” (2 ቆሮ.4፤7፣ ቆላ.3፤3) ይቆያል። ለመከራ፣ ለበሽታና ሞት ተዳርገን አሁንም በ “ምድራዊ ድንኳናችን” ውስጥ እንገኛለን።(2ቆሮ.5፤1) ይህ በእግዚአብሔር ልጅነት በሚመሰለው አዲስ ሕይወት ሊዳከምና እንዲያውም በኃጢአት ሳቢያ ሊጠፋ ይችላል።

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የነፍሳችን የሥጋችን ሐኪም ሽባውን ከኃጢአቱ ይቅር ብሎት አካላዊ ጤንነቱን እንደመለሰለት ሁሉ፣(ማር.2፤1-12) ቤተ ክርስቲያኑም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የመፈውስና የማዳን ሥራዎቹን በራስዋ አባለትም መካከል ቢሆን እንድትቀጥል ፈቃዱ ሆኗል። የሁለቱ ምሥጢራት ማለትም ምስጢረ ንስሐና ምስጢረ ቀንዲል ዓላምም ይኸው ነው።

ንስሐ የእርቅ ምስጢር

ወደ ምስጢረ ንስሐ የሚቀርቡ ሰዎች ስለፈጸሙት ኃጢአት ከእግዚአብሔር ምሕረትን ያገኛሉ። እንዲሁም ወደቅዱስ ሕይወት ይመጡ ዘንድ በፍቅር፣ በመልካም አርአያነት በጸሎት ስለእነርሱ ከምትተጋውና ኃጢአታቸው ካቆሶሏት ቤተክርስቲያን ጋር ይታረቃሉ።

ምስጢረ ንስሐ

·         እምነትን የመቀበል ምሥጢር ፤- ወደ እምነት የሚመራውን የኢየሱስን ጥሪ፤ በኃጢአት ሳቢያ ከአብ (ማር.1፤5፣ ሉቃ.15፤18) የራቀውን እንደገና ለመመለስ የሚያበቃውን የመጀመሪያ እርምጃ ያስገኛልና። የንስሐ ምስጢር ተብሎም ይጠራል፤ የኃጢአተኛውን ክርስቲያን ግላዊና እምነትን የመቀበል ሃይማኖታዊ እርምጃዎችን፣ ንስሓውን እርካታውን ይቀድሳልና።

·         ኃጢአትን የመናዘዝ ምሥጢር ፤ - ኃጢአትን ለካህን መግለጽ ወይም መናዘዝ የዚህ ምሥጢር  ዋነኛ ባሕርይ ነውና። በጥልቀት ሲታይ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቅድስናና ለኃጢአትናው ሰው የሚሰጠን ምሕረት ማወቅና ማወደስ - “መናዘዝ”ም ይሆናል።

· የይቅርታ ምሥጢር ፤ - በካህኑ የመፍታት ምሥጢር አማካይነት፣ እግዚአብሔር ለተነሳሒው “ምሕረትና ሰላም” ይሰጠዋል።

· የእርቅ ምስጢር ፤ - የሚታረቀውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለኃጢአተኛው ይሰጠዋል፤ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ”(2ቆሮ.5፤20) ይላልና። መሐሪ በሆነው በእግዚአብሔር ፍቅር የሚኖር “አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ ለሚለው።”(ማቴ.5፤24) ለጌታ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ነው።

ከጥምቀት በኋላ የእርቅ ምስጢር ለምን አስፈለገ?

“በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም።” “ክርስቶስን ከለበሰው” ዘንድ ኃጢአት ምን ያህል እንደተወገደ ለመገንዘብ ማንም ቢሆን ክርስቲያንነትን በሚያስገኙት ምሥጢራት አማካይነት እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ መጠን መረዳት መቻል አለበት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ይላል “ኃጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናታልላለን፤ እውነትም በውስጣችን የለም”(1ዮሐ. 1፤8)፤ “እርስ በራሳችን ስለኃጢአታችን ይቅር መባባላችንን እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ከሚያደርግልን ይቅርታ ጋር በማያያዝ፣ ጌታ ራሱ” “በደላችንን ይቅር በለን”(ሉቃ.11፤4, ማቴ.6፤12) በማለት እንድንጸልይ አስተምሮናል።

በክርስቶስ ማመን፣ የጥምቀት አዲሱ ልደት፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና የምንመገበው የክርስቶስ ሥጋና ደም፣ ልክ ራሷ ቤተክርስቲያን፣ የክርስቶስ ሙሽራ፣ “ቅድስትና አለነውር” እንደሆነች ሁሉ እኛንም (ኤፌ.1፤4, 5፤27) “ቅዱሳንና ነውር የሌለን” አድርገውናል። ይሁን እንጂ ክርስትናን በመቀበል ያገኘነው አዲስ ሕይወት የሰውን ተፈጥሮ ልዕልነትና ድክመት፣ በዘልማድ ፍትወተ ሥጋ (ጽነት) በመባል ወደሚታወቀው ኃጢአት ማዘንበልን አላስወገደም። ከክርስቶስ የጸጋ ድጋፍ ጋር በክርስቲያናዊ ሕይወት ትግል ራሳቸውን ብቁ እስካላደረጉ ድረስ፣ በተጠመቁም ዘንድ ይኖራልና። ጌታ ከቶውንም ሳያቋርጥ ወደሚጠራን ቅድስናና ዘላለማዊ ሕይወት የሚመራን የእምነት ትግል ይህ ነው።

ምሥጢረ ንስሐ - ለተጠመቁት የመመለስ ጥሪ

“የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማር.1፤15) እያለ ኢየሱስ ሰዎች እንዲመለሱ ይጣራል። ይሄ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ዋነኛ ክፍል ነው። በቤተክርስቲያን ስብከት ውስጥ ይህ ጥሪ በመጀመሪያ ደረጃ የሚተላለፈው ክርስቶስንና ወንጌልን ገና ላላወቁ ነው። እንዲሁም ጥምቀት ለቀዳሚና መሠረታዊ እምነት ሁነኛው ሥፍራ ነው። አንድ ሰው ክፋትን በማውገዝ ድኅነትን፣ ማለትም ለኃጢአቱ ምሕረትንና አዲስ ሕይወትን የሚያገኘው፣ ወንጌልን በማመንና በጥምቀት ነው። (ሐዋ.ሥራ 2፤38)

ይህ ሁለተኛው መለወጥ “ኃጢአተኞቹን በጉያዋ የያዘችውና፣ ቅድስትና በዚያው መጠን ሁልግዜም መንጻት የሚያሻት፣ እንዲሁም የንስሐና የተሃድሶን ጐዳና የምትከተለው፣ የመላዋ ቤተክርስቲያን የማያቋርጥ ተግባር ነው።” ይህ ንስሐ የመግባት የመአለስ ጥረት ሰብአዊ ክንውን ብቻም አይደለም። አስቀድሞ ለወደደን ለእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር ምላሽ ለመስጠት በጸጋ የተሳበና የተመሰጠ “የሚጸጸት ልብ” ትርታም ነው። (መዝ.51፤17, ዮሐ.6፤44,12፤32, 1ዮሐ. 4፤10)

ጌታውን ሦስት ጊዜ ከካደ በኋላ የጴጥሮስ ንስሐ /መመለስ/ ለዚህ ምስክር ነው። የኢየሱስ ማለቂያ የሌለው የመሐሪነት ገጽታ ከጴጥሮስ ዐይኖች የንስሐ እንባና፣ ከጌታ እርገት በኋላም፣ ለእርሱ ስላለው ፍቅር የሦስት ጊዜ እጥፍ ማረጋገጫ አፍልቋል። ሁለተኛው መመለስ “ንስሐ ግቡ!” በማለት ለመላዋ ቤተክርስቲያን የቀረበው የጌታ ጥሪ እንደሚያሳየው ማኅበራዊ ገጽታ አለው።

ውስጣዊ ንስሐ

እንድንለወጥና ንስሐ እንድንገባ የቀረበው የኢየሱስ ጥሪ፣ ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ነቢያት ጥሪ፣ በመጀመሪያ ደረጃ “ማቅ በመልበስ አመድ በመነስነስ”፣ እንዲሁም በጾምና ተጋድሎ ላይ የሚያተኩር ውጫዊ ሳይሆን፣ ልባዊ ወይም ውስጣዊ መለወጥን የሚጠይቅ ነው። ያለ ንስሐ ፍሬ ቢስና ከንቱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ውስጣዊ መለወጥ ገሃድ በሆኑ ምልክቶች እንቅስቃሴዎችና የንስሐ ሥራዎች መገለጽ ያሻዋል። (ኢዩኤል 2፤12-13፣ ኢሳ.1፤16-17፣ ማቴ.6፤1-6፣16-18)

ውስጣዊ ንስሐ የመላ ሕይወታችን ሥርነቀል ለውጥ፣ ፀፀት፣ በሙሉ ልባችን ወደ እግዚአብሔር መመለስ፣ የኃጢአት ማክተሚያ፣ የፈጸምናቸውን መጥፎ ተግባራት በመጥላት ከክፋት መራቅ ነው። ይህ ሁኔታ በእግዚአብሔር ምሕረት ተስፋ በማድረግና በጸጋው ድጋፍ በመተማመን፣ ሕይወትን የመለውጥ ምኞትና ውሳኔም ያስከትላል። ይህ ልባዊ መለወጥ አበው የመንፈስ ስብራትና ልባዊ ፀፀት በሚሏቸው ውጤታማ ሕመምና ሐዘን የታጀበ ነው።

የሰው ልብ ከባድና ደንዳና ስለሆነ እግዚአብሔር ለሰው ዘር አዲስ ልብ መስጠት አለበት። (ሕዝ.36፤26-27) መለወጥ/መመለስ ከሁሉም በፊት ልባችንን ወደ እርሱ የሚመልስልን የእግዚአብሔር ጸጋ ሥራ ነው። “አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን” (ሰቆቃወ ኤርሚያስ 5፤21) እንደ አዲስ እንጀምር ዘንድ እግዚአብሔር ብርታትን ይሰጠናል። የእግዚአብሔርን ፍቅር ታላቅነት ባወቀ ጊዜ ነው ልባችን በኃጢአት አስፈሪነትና ክብደት ተንቀጥቅጦ በኃጢአት የተነሳ እግዚአብሔርን ላለማስቀየምና ከእርሱም ለመለየት መፍራት የሚጀምረው። ልባችን የሚለወጠው በኃጢአታችን የወጋነውን እርሱን በማየት ነው። (ዮሐ.19፤37, ዘካ.12፤10)

ከዕለተ ፋሲካ ጀምሮ፣ መንፈስ ቅዱስ “ዓለም ስለ ኃጢአት መሳሳቱን” (ዮሐ.16፤8-9) ማለትም ዓለም እግዝአብሔር አብ የላከውን አለማመኑን አረጋግጧል። ነገር ግን ኃጢአትን ቁልጭ አድርጎ በማሳየት የሰው ልብ ለንስሐና ለመመለስ የሚያበቃውን ጸጋ የሚሰጠው አጽናኝ ይኸው መንፈስ ቅዱስ ነው። (ዮሐ.15፤26, ሐዋ.ሥራ 2፤36-38)

Last Updated (Monday, 30 August 2010 20:22)

 
የሳምንቱ መልእክት
"ለሰው ይኽን ያህል ታላቅ ክብር ለመስጠት ያነሳሳህ ምን ይሆን?...ወደር የሌለው ፍቅርህ እንደሆነ አይጠረጠርም! በፍቅሩ ተማርከሃል፤ በአውነትም በፍቅር ፈጥረኸዋል፤ በፍቅርም ዘላለማዊ መልካምነትህን የሚያጣጥም ስብእናን ለግሰኸዋል።" ቅድስት ካተሪና ዘሲየና
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤ/ያን መዝሙሮች (ብዛት 110!)
ባለፉት 12 ሰዓታት የጎብኚዎች አገር
Top 6:
United States flag 33%United States (4)
Ethiopia flag 25%Ethiopia (3)
Russian Federation flag 17%Russian Federation (2)
Canada flag 8%Canada (1)
Moldova, Republic of flag 8%Moldova, Republic of (1)
Switzerland flag 8%Switzerland (1)
12 visits from 6 countries