ኃጢአትን መጾም!
ኃጢአትን መጾም!
በቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም በአገራችን ባጠቃላይ የሚፈጸመው ከመብልና ከመጠጥ መራቅ የጾም ስልት ነው። በርግጥ ይህን መሰሉ ጾም በጣም አስፍፈላጊ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው እንዳገኘ ከበላና ከጠጣ ፈሪሃ እግዚአብሔርና አፍቅሮተ ሰብእ በልቡ አይኖርም። የወርሰውን የእግዚአብሔር ባህርይ በማጥፋት የእንስሳን ባህርይ ይይዛል።
የሚጾም የሚጸልይ የእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያ ይሆናል። በጾም ሥጋውን ይቀጣል። የኃጢአት ኃይል ይሰብራል። ንጹሕ የሆነ አምልኮ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። ነገር ግን ጾምን እንጾማለን እያልን ከኃጢአት ያምንጾም ከሆነ ጾማችን ከንቱ ነው። እንዲያውም በረሃቡና በጾሙ ሥጋቸውን፤ በክፉ ሥራቸው ደግሞ ነፍሳቸውን ይጎዳሉ። “ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ፤ ወንትፋቀር በበይናቲነ” ማለትም “ጾምን እንጹም ወንድማችንን እንውደድ፤ እርስ በርሳችንም እንዋደድ” ብለው ጥንት አባቶቻችን ያስተማሩንን በተግባር ማዋል ይገባናል።
ነቢዩ ኢሳያስ ስለ እውነተኛው ጾም እንዲህ ብሎ ያስተምረናል፦ “ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ።” እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል “እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፥ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?” (ኢሳ.58:3-7)።
ሰው እግዚአብሔርን ማገልገል የሚችለው በጾምና በጸሎት መጠመድ ከቻለ ብቻ ነው። ጾም ራሳችንን ልንቆጣጠር የሚያስችለን መሣሪያ ነው። መዝ. 13:12-14 በክርስቲያናዊ ሕይወት የሚያጋጥሙን ፈተናዎችን በጾም ማሸነፍ እንችላለን።
Last Updated (Saturday, 06 March 2010 19:52)


