ጾም እኔነትን ለማውለቅ!
ጾም እኔነትን ለማውለቅ!
ጾም፣ ጸሎትና ምጽውት ሦስቱ በጋራ የሚሄዱ የክርስቲያን ሥርዓቶች ናቸው። ጾም ፋሲካን በሚገባ ለማክበር የእግዚአብሔርን ኃይል ለማወቅ ይረዳናል። የጾምን ዋጋና ትርጉም ቅዱስ አባታችን ቢኔዲክቶስ 16ኛው በዘንድሮው (2001 ዓ.ም.) መልእክታቸው ሲገልጹት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተልእኮውን ከመጀመሩ በፊት በበረሃ 40 ቀንና ለሊት የጾመውን ጾም ያስታውሰናል በማለት ሲቀጥሉም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም የክርስቲያኖች ልማድ እንደሚያስተምረን ጾም ኃጢአትንና ወደ ኃጢአት የሚመራን ማንኛውንም ነገር እንድናስወግድ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ላይ እግዚአብሔር ሰውን ከሁሉ ዛፎች ፍሬ መብላት ትችላለህ ካለው በኋላ ከአንድ ዛፍ ፍሬ እንዳይበላ ሲከለክለው እናያለን (ዘፍ.2:16-17)።
ሁላችንም በኃጢአት የተዘፈቅን ስለሆንን ጾም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ወዳጅነት የምናድስበት መሳሪያችን ነው። ልክ ዕዝራ ግብዞች ወደ እስራኤል ለመመለስ ሲዘጋጁ ሕዝቡን ሰብስቦ እንዲጾሙ እንዳዘዛቸው፤ ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ እናድርግ ብሎም ሲመራቸው (እዝራ 8:21) እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ጠበቃቸው ፊቱብም ወደ እነርሱ አዞረ። የነነዌ ሰዎችም ለዮናስ የንስሐ ጥሪ መልስ በመስጠት ታምኝበታቸውን ለመግለጽ ጾምን አወጁ። እንዲህም በማለት፦ “እኛ ከጥፋት እንድንድን ምናልባት እግዚአብሔር ራርቶልን ከሚያሰራው ቁጣው የተመለሰ እንድሆነ ማን ያውቃል? (ዮናስ 3:9)። በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ከቁጣው ተመልሶ አዳናቸው።
በአዲሱ ኪዳንም ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾም ውስጣዊ ትርጉም ምን እንደሆነ ያስረዳናል። ጾም ማለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ማለት ነው። እርሱም ይህንን በስውር ያያል በስውርም ዋጋውን ይከፍላል (ማቴ.4:4)። ትክክለኛ ጾም ማለት ትክክለኛውን ምብ መመገብ ማለት ነው። እርሱም የአባቱን ፈቃድ መፈጸም (ዮሐ.3:34) ነው። ክርስቲያን ሲጾም በጾሙ በእግዚአብሔር ደግነት እና መልካምነት ለምታመን ራሱን በትሕትና ለእግዚአብሔር ዝቅ አድርጎ ያስገዛል።
ቅዱስ ጴጥሮስ ቃለ ወርቅ የተባለ ጸሐፊ ሲጽፍ “ጾም የጸሎት ነፍስ ናት፤ ምሕረትም የጾም ሕያው ደሙ ነው። ስለዚህ የምትጸልዩ ከሆነና ጾምም የምትጾም ከሆነ ምሕረትን አድርግ። ልመናህ ይሰማ ዘንድ የሊሎችን ልመና ስማ፤ ጆሮህን ለሌሎች ክፍት የምታደርግ ከሆነ የእግዚአብሔርን ጆሮ ለራስህ ታስከፍታለህ” ይላል። ቅዱስ አባታችን በመልእክታቸው እንደሚገልጹት በዘመናችን ጾም መንፈሳዊ ትርጉሙን እያጣ መጥቷል፤ ሰውም በአስተሳሰቡ ቁሳዊ ደኅንነትን አጠንክሮ ያያዘበት ዘመን ላይ እንገኛለን። ለኛ ለክርስቲያኖች ግን ከምግብ ስንቆጠብ ወይም ስንጾም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር እንዳንወሃድ ከሚከለክሉን ነገሮች እንድንድን ነው። ጾም የሁሉም ክርስቲያኖች ጥሪ ነው፤ ይህም ጥሪ እኔነትን አውልቆ ለመጣልና ልባችንን ለእግዚአብሔርና ለባልንጀራ ፍቅር ክፍት ለማድረግ ነው (ማቴ.22:34፣40) ብለዋል።
ስንጾም ሌሎች ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን በምን ዓይነት ሁኔታ ኑሯቸውን እንደሚኖሩ ለማየት ዓይናችንን ይከፈታል። ደጉ ሳምራዊን የመሰለ ዝቅ ብሎ የወንድሙን ቁስል አጥቦ የመሸከምና ወደ ማደርያ እንደወሰደው ሁሉ ቅዱስ ዮሐንስ በመጀመሪያ መልእክቱ የፈቃድና የፍላጎት ጾምም እንዲሁ ለባልንጀራችን ፍቅር እንደሚያግዘን ይገልጻል።
ቅዱስ አባታችን በጾም ጊዜ በእያንዳንዱ ቁምስና ችግረኞች እንዲረዱ ልዩ ምጽዋት እንዲሰበሰብ ያሳስቡናል። 2ቆሮ.8:9/ ሮሜ 15:25-27 እንደምናነበውም ክርስቲያኖች የተቸገሩን እንዲረዱ መበረታታት ይገባቸዋል።
መደምደምያ
ጾምን ራሳንን በሙሉ በስጦታ ለእግዚአብሔር የምናቀርብበት መንገድ ስለሆነ በታላቅ መንፈሳዊነት እናደርገው ዘንድ ያስፈልጋል። ይህንንም ማድረግ የምንችለው ለጸሎት ትልቅ ቦታ በመስጠት፣ ንስሐ በመግባት፣ ቅዳሴን በማስቀደስ ነው። ስለዚህ ጾምን ለመጾም በምናስብበት ጊዜ ሁሉ ራስን በሚገባ ለእግዚአብሔር በማዘጋጀት መጾም ይገባናል።
Last Updated (Saturday, 06 March 2010 19:56)


