የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ - ትምህርት ሁለት
ትምህርት ሁለት - የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ
►የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር እንዴት ይገለጻል? ወይም ቅዱሳት መጻሕፍት በመባል የሚታወቁት የትኞቹ ናቸው?
በትምህርት አንድ ላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር በግሪክና በእንግሊዝኛ “ካኖን” ተብሎ ይጠራል ፡፡ “በካኖን” ውስጥ የተዘረዘሩት የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሙሉ (ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ) እግዚአብሔር ያስጻፋቸው ወይም ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተሞልተውና ተመርተው የጻፏቸው ናቸው ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አለባቸው ፤ ዋና የክርስቲያን መመሪያ ናቸው (ሮሜ 15, 4 ፣ 2ጢሞ 3, 16-17) ፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱሳት መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ዝርዝራቸውና ተቀባይነታቸው በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ አንድ አይደለም (አንድ ዓይነት ወይም ወጥ የሆነ ተቀባይነት የላቸውም) ፡፡
► ቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝራቸውና ተቀባይነታቸው በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ አንድ ዓይነት ከልሆነ ይህ የቁጥርና የአቀባበል ልዩነት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የካቶሊክ ፣ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዘንድ ያለው የቅዱሳት መጻሕፍት አቀባበልና የቁጥሮቹ መብዛትና ማነስ ማየቱ ግድ ነው ፡፡
ሁሉም አብያተ ክርስትያናት በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተካተቱትን 27 መጻሕፍት ይቀበላሉ ፡፡ ልዩነታቸው ብሉይ ኪዳን ውስጥ በተካተቱትና አንዳንዶች (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ) አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ በተጨማሪ በሚያካትቱአቸው መጻሕፍት ላይ ነው ፡፡ የሚቀበሉአቸውም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው ፡፡
ሀ) ወንጌላት ፦ ማቴዎስ ፣ ማርቆስ ፣ ሉቃስ ፣ ዮሐንስ
ለ) የሐዋርያት ሥራ
ሐ) የጳውሎስ መልእክቶች
መ) የጴጥሮስ ፣ የዮሐንስ ፣ የያዕቆብና የይሁዳ መልእክቶች
ሠ) የዮሐንስ ራእይ ናቸው ፡፡
1)ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፦ ከ27ቱ የአዲስ ኪዳንና ከ39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍቶች ባጠቃለይ ከ66ቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የምትቀበላቸው ሰባት ሌሎች መጻሕፍት አሉ ፡፡ እነርሱም ድኅረ ቀኖና (ዲዮትሮ ካኖኒካል) ተብለው ሲጠሩ 66ቱ ደግሞ “ፕሮቶ ካኖኒካል” ይባላሉ ፡፡ በጠቅላላው 73 መጻሕፍት ሲሆኑ ሁሉም እኩል ተቀባይነት አላቸው ፡፡ ሰባቱ መጻሕፍት በ1989 ዓ.ም በአማርኛ ታትመው ወጥተዋል ፡፡ እነዚህ ሰባት መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው ፦
1)መጽሐፈ ጦቢት
2)መጽሐፈ ዮዲት
3)መቃብያን 1
4)መቃብያን 2
5)መጽሐፈ ጥበብ
6)መጽሐፈ ሲራክ
7)መጽሐፈ ባሮክ
አስተውል ፦ ሁለቱ የመቃብያን መጻሕፍት በኦርቶዶክስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሦስቱ የመቃብያን መጻሕፍት ጋር በስም እንጂ በይዘት አይገናኙም፡፡
2)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፦ 81 መጻሕፍትን ትቀበላለች ፡፡ በመጽሐፈ ፍትሐ ነገሥት በግእዝ የተዘረዘሩት መጻሕፍት አቆጣጠራቸው እንደሚከተለው ነው ፤
ሀ) ብሉይ ኪዳን
1)ኦሪት (ኦሪት ማለት አምስቱ የኦሪት ወይም የሙሴ መጻሕፍት) እና ፣ ኢያሱ ፣ መሳፍንት ፣ ሩት
2)ዮዲት
3)1ኛና 2ኛሳሙኤል ፣ 1ኛና 2ኛ ነገሥት እና ዜና መዋዕል
4)ዕዝራ ካልዕ ፣ ዕዝራ ሱቱኤል
5)አስቴር ፣ ጦቢት
6)መቃብያን (ሦስት መጻሕፍት)
7)ኢዮብ ፣ መዝሙረ ዳዊት
8)የሰሎሞን መጻሕፍት (እነዚህም መጻፈ ምሳሌ ፣ ተግሣጽ ፣ ጥበብ ፣ መክብብ ፣ መኃልይ ናቸው)9)ነብያት (4 ዐብይት ወይም ታላላቅ ነብያት እና 12 ደቂቀ ወይም ታናናሽ ነብያት)
የብሉይ ኪዳን ድምር 46 ነው ፡፡
ለ) አዲስ ኪዳን
1)ከማቴዎስ ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ፦ በአጠቃላይ 27 መጻሕፍት
2)ሲኖዶስ (ሲኖዶስ በመባል የሚታወቁት ሥርዐተ ጽዮን ፣ ትእዛዝ ፣ ግጽው ፣ አብጥሊስ) ፦ 4 መጻሕፍት
3)መጽሐፈ ኪዳን ፦ በአጠቃላይ 2 መጻሕፍት
4)ቀሌምንጦስና ዲድስቅልያ ፦ በአጠቃላይ 2 መጻሕፍት
ጠቅላላ አዲስ ኪዳን 35 ሲሆኑ ጠቅላላ ብሉይ ኪዳን 46 ናቸው፤ ጠቅላላ ድምራቸው 81 ነው ፡፡
3)የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ፦ የመጀመሪያዎቹ 39ኙ የብሉይና 27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ባጠቃላይ 66ት መጻሕፍት ይቀበላሉ ፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተዘረዘሩት ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት (ካቶሊክ ፣ ኦርቶዶክስና ፕሮቴስታንት) በጋራ ወይም በተመሳሳይ መልኩ የተቀበሏቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር እንደሚከተለው ይቀርባል ፦
|
1 |
ኦሪት ዘፍጥረት |
14 |
ሁለተኛው መጽሐፈ ዜና መዋዕል |
27 |
ትንቢተ ዳንኤል |
|
2 |
ኦሪት ዘጸአት |
15 |
መጽሐፈ ዕዝራ |
28 |
ትንቢተ ሆሴዕ |
|
3 |
ኦሪት ዘሌዋውያን |
16 |
መጽሐፈ ነህምያ |
29 |
ትንቢተ አሞጽ |
|
4 |
ኦሪት ዘኁልቅ |
17 |
መጽሐፈ አስቴር |
30 |
ትንቢተ ምክያስ |
|
5 |
ኦሪት ዘዳግም |
18 |
መጽሐፈ ኢዮብ |
31 |
ትንቢተ ኢዩኤል |
|
6 |
መጽሐፈ ኢያሱ |
19 |
መዝሙረ ዳዊት |
32 |
ትንቢተ አብድዩ |
|
7 |
መጽሐፈ መሳፍንት |
20 |
መጽሐፈ ምሳሌ |
33 |
ትንቢተ ዮናስ |
|
8 |
መጽሐፈ ሩት |
21 |
መጽሐፈ መክብብ |
34 |
ትንቢተ ናሆም |
|
9 |
አንደኛው መጽሐፈ ሳሙኤል |
22 |
መኃልየ መኃልየ ዘሰሎሞን |
35 |
ትንቢተ ዕንባቆም |
|
10 |
ሁለተኛው መጽሐፍ ሳሙኤል |
23 |
ትንቢተ ኢሳይያስ |
36 |
ትንቢተ ሶፎንያስ |
|
11 |
አንደኛው መጽሐፈ ነገሥት |
24 |
ትንቢተ ኤርምያስ |
37 |
ትንቢተ ሐጌ |
|
12 |
ሁለተኛው መጽሐፈ ነገሥት |
25 |
ሰቆቃው ኤርምያስ |
38 |
ትንቢተ ዘካርያስ |
|
13 |
አንደኛው መጽሐፈ ዜና መዋዕል |
26 |
ትንቢተ ሕዝቅኤል |
39 |
ትንቢተ ሚልክያስ |
እነዚህ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን መጻሕፍት በአራት ክፍሎች ይመደባሉ ፦
|
ብሉይ ኪዳን |
|||
|
፩ - የሕግ መጻሕፍት (የኦሪት ወይም የሙሴ መጻሕፍት)
ዘፍጥረት
ዘጸአት
ዘሌዋውያን
ዘኁልቅ
ዘዳግም |
፪ - የታሪክ መጻሕፍት
መጽሐፈኢያሱ
መጽሐፈመሳፍንት
መጽሐፈሩት
1ኛመጽሐፈሳሙኤል
2ኛመጽሐፈሳሙኤል
1ኛመጽሐፈነገሥት
2ኛመጽሐፈነገሥት
1ኛዜናመዋዕል
2ኛዜናመዋዕል
መጽሐፈዕዝራ
መጽሐፈነህምያ
መጽሐፈአስቴር
|
፫ - የመዝሙርና የጥበብ መጻሕፍት
መጽሐፈኢዮብ
መዝሙረዳዊት
መጽሐፈምሳሌ
መጽሐፈመክብብ
መኃልየ መኃልየ
|
፬ - የትንቢት መጻሕፍት
ትንቢተኢሳያስ ትንቢተኤርምያስ ሰቆቃው ኤርምያስ ትንቢተሕዝቅኤል ትንቢተ ዳንኤል ትንቢተሆሴዕ ትንቢተኢዩኤል ትንቢተአሞጽ ትንቢተአብድዩ ትንቢተዮናስ ትንቢተሚኪያስ ትንቢተናሆም ትንቢተእንባቆም ትንቢተሶፎንያስ ትንቢተሐጌ ትንቢተዘካርያስ ትንቢተሚልኪያስ |
► መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መጻሕፍትን ያካተተ (የያዘ) ትልቅ ቅዱስ መዝገብ ከሆነ በምን ዓይነት መልኩ ሊከፋፈል ይችላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ከኦሪት ዘፍጥረትጀምሮበዮሐንስራእይእንደሚጨርስ ይታወቃል ፡፡ ይህ ቅዱስ መጽሐፍ ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በመባል የሚጠሩ ሁለት ትልልቅ ክፍሎች አሉት ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ኪዳኖች ከላይ እንደተገለጸው በውስጣቸው የራሳቸው የሆነ አከፋፈል አላቸው ፡፡
► ኪዳን ማለት ምን ማለት ነው?
ኪዳን ማለት በተለያዩ ወገኖች መካከል የሚደረግ ውል ፤ ቁም ነገር ፤ የፍቅርና የአንድነት መሐላ ፤ ሰላማዊ ሕግ ፤ ሁለቱን ወገን አንድ የሚያደርግ ፤ ስለ ረብና ጥቅም በተስፋ የቆመ የተጻፈ ሥርዐት ፤ ቢያፈርሱት ጉዳትና ጠብ የሚያመጣና ጥቅም የሚያሳጣ የሚለውን ትርጉም እንደሚሰጥ ከሊቃውንቶች መዝገበ ቃላት እንረዳለን ፡፡ በአጠቃላይ ኪዳን በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ወገናት መካከል የሚፈጸም ውል ነው ፡፡
► ብሉይ ኪዳን ማለት ምን ያመለክታል?
ብሉይ ኪዳን ፦ ብሉይ ማለት ያረጀ ፣ ጥንታዊ ፣ ቀዳማዊ ፣ የድሮ ፣ የቀድሞ ፣ የፊት ማለት ነው ፡፡ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ብሉይ ኪዳን የሚያመለክተው እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ በሙሴ አማካኝነት የሰጣቸው ቃል ኪዳን ነው (ዘጸ 20, 1-17 ፣ 34, 28 ፣ ዘዳ 4, 13) ፡፡ ሕዝቡ እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ ሙሴ መሥዋዕትን ሠውቶ ደሙን በሕዝቡ ላይ በመርጨት ቃል ኪዳኑን አጸና (ዘጸ 24, 1-8) ፡፡ ቃል ኪዳኑም እንዲፈጸም ትእዛዝ ፣ ሥርዓትና ፍርድ ተሰጡ (ዘዳ 5, 31) ፡፡ ይህም ቃል ኪዳን ከመጀመሪያው ጀምሮ ጊዜያዊ መሆኑን ታወቀ (ዘዳ 18, 15 ኤር 31, 31) ፤ አዲስ ኪዳንም ስለገባ ብሉይ ኪዳን አሮጌ ተባለ ፡፡ ባጠቃላይ ብሉይ ኪዳን ከመጀመሪያው ፍጥረት መፈጠር ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ የነበረው የሰዎችንና የእግዚአብሔርን ግንኙነት የሚናገር ነው ፡፡ የብሉይ ኪዳን አከፋፈል በተመለከተ ከላይ “ቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝራቸውና ተቀባይነታቸው በሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ” የሚገልጸውን ይመልከቱ ፡፡
► ብሉይ ኪዳን ምን ያህል ዓመታትን ወይም ዘመናት የሚሸፍን ታሪክ እንደሚገልጽ ይታወቃልን? የታሪኩ መነሻውና መጨረሻው ዘመን ይታወቃልን? በታሪክ ሂደት ውስጥ ብሉይ ኪዳን የሚተርካቸው ነገሮች በዓመታት ከፋፍሎ ማየት ይቻላልን?
በእርግጥ ከዘጠኝ መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የሆኑትን የድርጊቶች ዓመት ወይም ወቅት በትክክል ለመወሰን አንችልም ፡፡ በእስራኤል የዓመት አቆጣጠር እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበት የኒሳን ወር የመጀመርያ ሆኖ ይቆጠራል (ዘጸ 12, 2) ፡፡ ሆኖም ፡ ሕዝቡ በግብርና ስለሚኖሩ አጨዳ ሲጨርሱ የዓመት መለወጫ በዓልን ያከብሩ ነበር (ዘጸ 23, 16 ፣ 34, 22) ፡፡ ብዙ ጊዜ በወሩ ሳይሆን በግብርና ሥራ ጊዜው ይገለጣል (ዘኁ 13, 20 ፣ ሩት 1, 22) ፡፡ በጥንት ዘመን እንደ ከተማ መቈርቈር፣ እንደ ምድር መናወጥ ከመሳሰሉ ከታወቁ ሁኔታዎች በመነሣት ዓመታት ይቈጠሩ ነበር (አሞ 1, 1) ፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የተፈጸሙት ድርጊቶች ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ካለው አቈጣጠር ጋር ማዛመድ ያዳግታል ፡፡
ነገር ግን በተለይ ከዘጠኝ መቶ ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት የሆኑትን የድርጊቶች የተከናወኑበትን ትክክለኛ ዓመት ወይም ወቅት በትክክል ለመወሰን ባንችልም ተቀራራቢ ሊሆን ይችላል ተብለው በሊቃውንቶች ዘንድ የሚገመቱ ዓመታት መግለጽ ይቻላል ፡፡ በዚህም መሠረት ለምሳሌ የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ አገር የወጡበት ዓመቱ አንዳንዶች ከክርስቶስ ልደት በፊት 1445 ሌሎች 1280 መሆኑን ይገምታሉ ፡፡ አብርሃም ከ2ሺህ-1850 ገደማ ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደኖረ ይታሰባል ፡፡ ከአብረሃም በፊት የኖሩትን ሰዎች ምን ያህል ጊዜ እንደኖሩ አይታወቅም ፡፡ አቆጣጠሩ የተለያየ በመሆኑ ፡ አንዳንድ ሊቃውንቶች ከአዳም እስከ ክርስቶስ ድረስ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ይሆናል ይላሉ ፡፡ ነገር ግን ይህ የተረጋገጠ አቆጣጠር አይደለም ፡፡
ከአዳም ጀምሮ ያለው የብሉይ ኪዳን አከፋፈል ፡ ልዩ ልዩ ቢሆንም በሊቃውንቶች ጥናት መሠረት በስምንት ክፍለ ዘመን ይመደባል ፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩ ዋና ዋና ሰዎች ፣ አምልኮና ድርጊቶች በቅደም ተከተል እንደሚከተለው ይቀርባሉ ፡፡
|
ዘመን |
ዋና ዋና ድርጊቶች |
ዓመት ከ.ክ.ል በፊት |
ታላላቅ ሰዎች |
የአምልኮና የሃይማኖት ሁኔታዎች |
|
መጀመሪያ |
- ፍጥረት በኃጢአት መውደቅ - የጥፋት ውሃ
- የባቢሎን ግንብ |
- 10000 - 5500?)
- 5000?
- 3500? |
- አዳም
- ኖኀ |
በገነት የነበሩ ሁለቱ ዘፎች
- ቀስተ ደመና |
|
አባቶች |
ከዑር ወደ ከነዓን
ከከነዓን ወደ ግብጽ |
1900-2085?
1710-1870? |
- አብርሃም
- ይስሐቅ
- ያዕቆብ ዮሴፍና ወንድሞቹ |
- ተስፋ ስለ ምድርና ስለ ዘር
- ቃል ኪዳን-ግዝረት |
|
ሕዝብ |
ፋሲካ (ከግብጽ መውጣት) |
1280-1445? |
ሙሴ |
- ዐሠርቱ ቃላት፣ ሕግ ፣ ታቦት ፣ መገናኛ ድንኳን |
|
አገር |
ወደ ከነዓን መግባትና አገሩን መያዝ |
1240-1400? |
- ኢያሱ - መሳፍንትና ሩት - ሳሙኤል |
- ሲታዘዙ በረከት - ሲያጠፉ ቅጣት - ታቦት በቤቴል |
|
ነገሥታት |
ኢየሩሳሌም ዋና ከተማ ሆነች |
1051-1011 1011-971 971-931 |
- ሳኦል - ዳዊት - ሰሎሞን |
- መዝሙራት
- ታቦት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት |
|
መከፋፈል- |
- የእስራኤል ዋና ከተማ ሰማርያ - ወደ አሦር መሰደድ |
931-722
- 722 |
- ኢዮርብዓም ፣ አክዓብ ፣ ኤልያስ ፣ ኤልሳዕ ፣ ሆሴዕ ፣ አሞጽ - ሰናክሬም |
- የወርቅ ጥጃዎች በቤቴልና በዳን የበዓል ጣዖታት |
|
|
- የይሁዳ ዋና ከተማ ኢየሩሳሌም ሆነች - ኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን መሰደድ |
- 931-587
- 605, 597, 587 |
- ሮብዓም ፣ ሕዝቅያስ ፣ ኢሳይያስ - ኢዮስያስ ፣ ኤርምያስ - ነቡከደነፆር |
- ባዕድ አምልኮትና ኃጢአት እየበዛ ሄደ
- ቤተ መቅደስ ፈረሰ |
|
ምርኮ |
በባቢሎን በስደት መኖር |
607-538 |
- ሕዝቅኤልና ዳንኤል |
- በምኩራብ መሰብሰብ ተጀመረ |
|
ከምርኮ መመለስ |
የፋርስ መንግሥት ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ |
539-330 |
- አስቴር (480) ዘሩባቤል ፣ ሐጌ ፣ ዘካርያስ (520) ፣ ዕዝራ (458) ፣ ነህምያ (445) ፣ ሚልክያስ (400) |
- ቤተ መቅደስ ተሠራ፣ ትምህርትና ሥነ ሥርዓት ተጠበቀ |
|
|
የግሪክ መንግሥት
- የሮም መንግሥት |
330-63
- 63 |
አንጥያኮስ ፣ መቃብያን
- ሄሮድስ |
- ፈሪሳውያን ሰዱቃውያን - ቤተ መቅደስ ታደሰ |
አስተውል ፦ ዓ. ም የሚያመለክቱት ቁጥሮች ተከትሎ ያለው የጥያቄ ምልክት ዓመተ ምህረቶቹ በእርግጠኝነት የተቀመጡ አለመሆናቸው የሚያሳይ ምልክት ነው ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከአዳም ጀምሮ ያለው ታሪክ የትውልድ ሐረግን በመጠቀም ብንከፋፍለው የሚከተለውን እናገኛለን ፦
|
|
አዳም ↓ |
|
|
ቃየል |
ሴት ↓ |
አቤል |
|
|
ሄኖክ ↓ |
|
|
|
ኖኅ ↓ |
|
|
ካም |
ሴም ↓ |
ያፌት |
|
|
አብርሃም ↓ |
|
|
እስማኤል |
ይስሐቅ ↓ |
|
|
ዔሳው |
ያዕቆብ ↓ |
|
|
ሮቤል |
ይሁዳ ↓ |
ዮሴፍ |
|
|
እሴይ ↓ |
|
|
|
ዳዊት ↓ |
|
|
|
ሰሎሞን ↓ |
|
|
|
ዘሩባቤል ↓ |
|
|
|
ማርያም ↓ |
|
|
|
ኢየሱስ
|
|
አስተውል ፦ ከይሁዳ እስከ እሴይ ፣ ከሴም እስከ አብረሃምና ከዘሩባቤል እስከ ማርያም ድረስ ባለት የትውልድ ሐረጋት ውስጥ ሌሎችም እንዳሉ ማስተዋል ይኖርብናል ፡፡
የትምህርቱ ዋና አዘጋጅ ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ
ምክትል አዘጋጅና አስተባባሪ ካህን ፦ አባ ፍቅረየሱስ ተስፋዬ
ጸሐፊ ፦ ለምለም ክፍሌ (ከሐዋሪያዊ ጽ⁄ቤት)
ጥያቄዎች
1)ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከ27ቱ የአዲስ ኪዳንና ከ39ኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍቶች ውጪ ተጨማሪ የሆኑ የምትቀበላቸው መጻሕፍት ምን በመባል ይታወቃሉ? እነዚህ መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው?
2)በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተካተቱት 27ቱ ቅዱሳን መጻሕፍት በሁሉም አብያት ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አላቸው ፤ ነገር ግን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለየት ባለ መልኩ ከ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ መጻሕፍት ታካትታለች ፡፡ ይህች ቤተ ክርስትያን የትኛዋ አብያተ ክርስቲያን ወይም ማን በመባል ትጠራለች? በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ካላቸው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተጨመማሪ ያካተተቻቸው መጻሕፍት ስንትና የትኞቹ ናቸው?
3)የካቶሊክ ፣ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት አብያተክርስቲያናት የሚቀበሉአቸው የቅዱሳን መጻሕፍት ቁጥር ግለጽ ፡፡
- ካቶሊካዊት ቤ⁄ክ_________
- ኦርቶዶክሳዊት ቤ⁄ክ_________
- የፕሮቴስታንት ቤ⁄ክ_________
ይህ የቁጥር ልዩነት ለምን የተፈጠረ ይመስልሃል?
4)ኪዳን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከላይ በትምህርቱ ውስጥ በተብራራ መልኩ ቀርቧል ፤ ዘሬም በዕለታዊ ሕይወታችን ከኪዳን ጋር በተያያዘ መልኩ ስሞች ለምሳሌ ኪዳነ ወልድ ፣ ኪዳነ ማርያምና ኪዳኔ የመሳሰሉት ይሰየማሉ ፤ ሰዎችም በተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ኪዳን አደረጉ ፤ ቃል ኪዳን ገቡ ፤ ኪዳን አቆሙ ወይም በመካከላቸው ኪዳን አጸኑ ይባላል ፤ ለመሆኑ ሰዎች ቃል ኪዳን ተገባቡ ወይም ቃል ኪዳን መሠረቱ ወይም ቃል ኪዳን በመካከላቸው አቆሙ ሲባል ምን ያመለክታል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት 


